ከአራት ኪሎ ወደ ቦሌ አራብሳ ጉዞ ሊጀመር ነው፡፡ የዶልፊን ታክሲ ወያላ፣ ‹‹እህቴ ጠጋ… ጠጋ… በይ፣ የዘንድሮ ኑሮ ካልተጠጋጉ አይቻልም…›› እያለ ሲያግባባ ተቃውሞ ተነሳበት፡፡ ‹‹አልጠጋም፣ ለምንድነው የምጠጋው? ሒሳቤን ከፍዬ እንጂ በነፃ አይደለም የተሳፈርኩት…›› ተጠጊ የተባለችው ወይዘሮ ብልጭ ብሎባታል። ከዓመት ዓመት ባርቆብን እንዴት ልንሆን ነው? ‹‹ምናለበት በሁለቱም መቀመጫችን ተዘፍዝፈን ወያላና መንግሥትን ከማማት እርስ በርስ ብንተባበር? አይ የእኛ ሰው ተቀምጦ ሰማይ ቀዶ መስፋት ብቻ…›› ወያላው አጋዥ ለማግኘት አሳባሪ መንገዶችን በሙሉ በመጠቀም ላይ ነው። ‹‹ያስለመዱህ ይጠጋጉልህ፣ እኔ ግን መብቴን ለማንም አሳልፌ የማልሰጥ ኩሩ ዜጋ ነኝ…›› ወይዘሮዋ እንደ አራስ ነብር እየሆነች ነው፡፡ ‹‹ምናለበት ብትጠጋና ብንቀሳቀስ? ዘና ብሎ ከመደህየት ተጨናንቆ ማደግ አይሻልም? ይገርማል እኮ…›› ይላል መሀል ወንበር የተቀመጠ ወጣት። ከሦስተኛው ረድፍ ላይ ደግሞ፣ ‹‹የእኔ እህት ይህንን ጅል እንዳትሰሚው በርቺ…›› እያለ ኑሮ ጀምሮት መጠጥ የጨረሰው ጎስቋላ ጎልማሳ ያጉተመትማል። አጠገቡ ‘ማች በማች’ የለበሰች ዝንጥ ያለች ወጣት፣ ቦርሳዋን እንቅ አድርጋ ታቅፋ በአልሰማሁም በአላየሁም ዝም ብላለች። ከመጨረሻ ወንበር አንድ አዛውንት፣ አንድ ጎልማሳና ዕድሜያቸው በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገመቱ ወጣቶች ጎን ለጎን ተሰይመዋል። ታዳሚዎቻችን ናቸው!
ወያላው እልህ ይዞት አጠጋግቶ ሊያስቀምጣቸው የነበሩትን ተሳፋሪዎች አንዱን ጎማ ላይ አንዱን ከጋቢና ወንበር ጀርባ፣ ሌላውን ሞተር ላይ አደላድሎ አስቀምጦ ‹‹ሳበው!›› ብሎ በሩን ከረቸመ። ወይዘሮዋ በድል አድራጊነት ስሜት ፈገግ ብላ፣ ‹‹እኛን የሰለቸን ከእናንተ ጀምሮ ጉድለታችንና ክፍተታችንን ምክንያት አድርጎ ሙሴያችሁ ነኝ ተቀበሉኝ፣ ተከተሉኝ፣ እመኑኝ የሚለን ሐሰተኛ ነብይ ብዛት ነው። ራሳችን ለራሳችን መብት ብንቆም ከመጀመሪያው መቼ በየአቅጣጫው ነጂ ይልክብን ነበር…›› ብላ በራሷ ዓለም ጠፋች። ነገሩ ከምኔው የነጂና ተነጂ አተካራ ውስጥ እንደገባ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ወያላው ሁላችንንም ተራ በተራ ሲያየን ቆይቶ፣ ‹‹አሁን እናንተ አይደለም ተሠልፋችሁ መዋል፣ ምንስ ብትሆኑ ይታዘንላችኋል?›› እያለ ፊቱን ሲያዞር፣ ‹‹ምን ያበሳጨዋል ይኼ፣ ይኼው ዙሪያችንን የሌለ መመርያና ነቀፌታ፣ ሕግና ትዕዛዝ ያለጠፍክበት ቦታ የለም። አትትፉ የሚል ግን አለ? ንገረኛ፣ ከየትኛው ሕግ ነው ጠቅሰህ የምትከሰኝ? ማታ በዜና ተመርቆ ተከፈተ ተብሎ በቲቪ የታየ ፕሮጀክት ለማየት ስንሄድ፣ ‹ፊኒሺንግ› ይቀረዋል ተብሎ ስንመለስ ተጠያቂው ማነው ብለህ ጠይቀሃል? ወይስ ስንቱ በዕድሜያችንና በህልማችን ተጫውቶ ሲያላግጥብን ተመሥገን ማለታችን ኃጢያት ሆኖ ነው?›› ብለው አዛውንቱ ባሱ። ስንት ጉድ አለ እኮ ጎበዝ!
ወያላው ሞተር ላይ ያስቀመጠው ተሳፋሪ ስልኩ ትጮሃለች። በስንት ሥቃይ በስንት አሳር ካለችበት ታስሳ ወጣች። ‹‹ይኼ ሰውዬ ነዳጅና የከበሩ የተፈጥሮ ማዕድናት ላይ ቢሠራ ያው መጀመሪያ ራሱን፣ ከዚያ ምናልባት ራርቶ አገሩን ሊጠቅም የሚችል ይመስላል…›› ይላል ያ ወጣት። ባለስልኩ፣ ‹‹ሃሎ!›› የጆሯችን ታንቡር እስኪበሳ መጮህ ጀመረ። ‹‹ይሰማኛል፣ ቅድም እኮ ተቋረጠ። ምን ይታወቃል ሚሊዮን እያልኩ ሳወራ ቴሌ ትን ብሎት ይሆናላ… ሃ…ሃ…ሃ…›› ገልመጥ እያለ ያየናል፣ ቀጥሏል። ‹‹አሥራ ስድስት ሚሊዮን እጄ ላይ አለ። ቀሪው እህል እጃችን ሲገባ በባንክ ትራንስፈር ይደረግልሃል ብለውኛል። አዎ ተፈራርመናል እንጂ…›› እያለ ስለሥራው ቀጠለ። ተሳፋሪዎች እያልጎመጎሙ ወሬ ጀመሩ። ‹‹እህም ወይ ሚሊዮን እንዲህ ሳናስበው አፋችን ገብቶ ይቀርቀር…›› አለች ከወያላው ጋር የተናቆረችው ወይዘሮ። ‹‹እኛ የአፋችን ነገር መቼ ቸገረን፣ የሆዳችን እንጂ የሚያንገዋልለን። እንይዘዋለን ባዶ። ባለሁለት መቶ ብር ኖት ብን ሲል አይራራ። አብሮ በልቶ ጠጥቶ የሚንሸራተተው ወዳጅ በዛ ብለን ሳንጨርስ፣ በላባችን የምናመጣው ገንዘብ ረድዔት አጥቶ መቅኖ ቢስ ሆንን…›› ትላለች አጠገቧ የተመቀጠች ደርባባ። ሦስተኛ ረድፍ ላይ ደግሞ ያ ጎስቋላ ጎልማሳ፣ ‹‹እኔ ግን እንደ ምንም ብዬ ፌስታል ነው ማምረት ያለብኝ፣ አይመስልሽም?›› ከመነጽር እስከ አልቦ በ‘ማች’ ያበደችውን ተሳፋሪ አጨናነቃት። ዞር ብላ፣ ‹‹አልገባኝም?›› ከማለቷ፣ ‹‹በዚህ አያያዝ እንደ ዚምባቡዌ በዘንቢልና በፌስታል ገንዘብ ተሸክመን ጉልት መውጣታችን አይቀርማ፣ ዋናው ማደጋችን ነው…›› ሲላት እንሰማለን። ሰው ግን እንዴት አዙሮ ተኳሽ ሆኗል!
ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ወያላችን አንድ ሚሊየነር ሞተር ላይ አስቀምጦ እየተጓዘ መሆኑን ሲሰማ በጣም ተናደደ። ‹‹ወይ አይጠቀሙ፣ ወይ አያስጠቅሙ፣ ወይ አይጠጉ፣ ወይ አያስጠጉ…›› ይላል። ነጋዴው በስልኩ ማውራቱን እንደ ቀጠለ ነው። ጋቢና የተሰየሙት ተሳፋሪዎች ሳይቀሩ ወያላውን ሰምተውት ኖሮ፣ ‹‹እባክህ በተጠጋጋ ብቻ አይደለም ዕድል ያስፈልጋል። ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ሲሄድ የማይታይ አለመኖሩን አንተም ታውቃለህ። እንደ እኔ ያለው ደግሞ አለላችሁ በትንኝ የሚጋለጥ። ሌብነትም እኮ ‹ታለንት› ይጠይቃል…›› አለ አንደኛው። ‹‹በቃ እኛ ግን መጠቃቀም፣ መጠጋጋት ስንባል የሚታየን ሌብነት ብቻ ነው? የሥራ ዕድል ማግኘት፣ በጎ በሆነ መንገድ መረዳዳት አይታየንም?›› ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠችው አቋርጣ ገባች። ‹‹ሆ… ሆ… መጀመሪያ ያለ ‹አይዲ› የሚያስጠጋ አለ እንዴ? የለም እኮ፡፡ እንደ እኛ ዓይነቱ ከምኑም የሌለበት ወይ ግንባር የለው ወይ የሚጋጨው ‹ቻፓ› ዝርዝር ሳንቲሙን እያንቃጨለ ዕድሜው በታክሲ ሠልፍ ያልቃል። ምናልባት ከቀናን ደግሞ አገርህ በሀብት ከ184 አገሮች 171ኛ ሆነች የሚል ዜና ቢመረቅልን ነው። በማትሞቀው እሳት አገርህ ደረጃ ስትመድብ አንተም ቶሎ ብለህ ምድብህን ማስተካከል ነው…›› ከጎኔ የተሰየመ ጎልማሳ ይለፈልፍብኛል። ይኼን ሲል የሰማው ሌላ ጎልማሳ፣ ‹‹ማስተካከል ካልቻልክስ? ምድቡ የሞት ምድብ ከሆነስ?›› ብሎ መጣብን። ‹‹አሁን ይኼ ጥያቄ ነው? ልማታዊ ኑሮ ካቃተህ ልማታዊ ሞት መሞት ነዋ…›› ብሎ ወሽመጡን በጠሰው። ‹‹ልማታዊ የሚባለውን የኑሮ ውድነት እያየነው ነው፣ ልማታዊ ሞት ደግሞ እንዴት ያለ ነው?›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹ለመንግሥት ሳያሳሙ፣ ቀባሪ ሳያስቸግሩ ‹ሳይለንት› ሆኖ ማለፍ ማለት ነዋ። ሌላ ምን ይሆናል? ወይ ስም ሳያስነሱ መመንተፍ ወይ ተረስቶ ማለፍ ነው…›› ብትል ቆንጂት ሳቅ ቢጤ ተሰማ። አንዳንዴ አይቀርም!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ታክሲያችን በጉዟችን መገባደጃ መክለፍለፍ ጀምራለች። ‹‹የምን ሩጫ ነው በአትሌቶች እንጂ በታክሲ ሾፌሮች እኮ የተሰበረ ሪከርድ የለም ቀስ በል አቦ…›› ይላል አንዱ ተሳፋሪ። ሾፌሩ መልሶ፣ ‹‹ያራገፈ እንጂ ሩጫውን የጨረሰ ታክሲ የለም…›› እያለ እንደ ፍጥርጥራችሁ ይለናል። በጎን ወያላው፣ ‹‹ለአንድና ለሁለት ብር መልስ ምን ያጨቃጭቃችኋል?›› ብሎ መልሱን ዓይን በዓይን ካላስቀረሁ ይለናል። ‹‹በል አምጣ ሃምሳ ሳንቲም ይጎድለኛል ሙላና ውሰደኝ ብልህ ታሳፍረኛለህ? እንደ ራስ ማየት ነው…›› ይላሉ አዛውንቱ። ወያላው መልስ የለኝም ብሎ ድርቅ ሲል ነገር ተባባሰ። ተሳፋሪዎች ተንጫቹ። ‹‹ምን ያድርግ ብላችሁ ነው ሕግ አክብሮ የሚያስከብር ብናጣ፣ ቁስላችጩ አመርቅዞ ኢንፌክሽን ካልሆነ በቀር ዞር ብሎ የሚያየን እንደሌለ ቢያይ እኮ ነው…›› ሲል አንዱ፣ ‹‹እኮ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ብረት ማንሳትና ብረት መግፋት አለብን መብት ለማስከበር…›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ያዝ እንግዲህ ወሬኛ ቢሸፍት ከፌስቡክና ከቲክቶክ አይወጣም…›› እያለ አፍ ይካፈታል ወያላው። ‹‹እኮ በስተርጅና ከዚህ ሁሉ የደም ታሪክና የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ እንደገና መተነኳኮስ ተጀመረ?›› ሲሉ አዛውንቱ ከጎናቸው የተሰየመው ጎልማሳ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ተናግሮ ሊያናግረን ነው። ኃላፊነት የጎደለውን የሰብዕና አምልኮ ናፋቂን ፉከራና ቀረርቶ በሰማን ቁጥር ደንፍተንማ አይሆንም…›› ይላል። ‹‹ኧረ ተወኝ በዕድገት፣ በመልካም አስተዳደር መሻሻል፣ በፍሕት ሥርዓት፣ በዴሞክራሲ እንጂ በጦርነትና በብጥብጥ ማንም ሪኮርድ ያስመዘገበ የለም በለው…›› ሲል ከወደ ጋቢና ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን ከፈተው። ብር ዘርዝሮ መልስ ይዞ እስኪመጣ ንቅንቅ ያለ የለም። እያንዳንዳችን ተራ በተራ መልሳችንን እየተቀበልን ስንበታተን፣ ሌሎች የባሱብን ችግሮች ላይ ለምን ይህችን ያህል ተሰባስበን መብት እንደማናስከብር ተገርመን እንተያይ ነበር። በዚህ መሀል ነበር አንዱ ወፈፍ ያደረገው የሚመስል፣ ‹‹… ገቡ አሉ፣ በእርግጥ ገብተዋል? እግራቸውን ነው ያስገቡት? ወይስ ቃል ነው የገቡት? መግባቱንስ ገቡ መውጪያውን አውቀውታል…›› እያለ ሲለፈልፍ ግራ ተጋብተን እያየነው ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!