Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከመንግሥት መተማመኛ የተሰጠው የቱሉ ካፒ ወርቅ ፕሮጀክት ሥራ ለመጀመር መዘጋጀቱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን በከፊ ሚነራልስ ፒኤልሲ አማካይነት ለሚተገበረው የቱሉ ካፒ ወርቅ ልማት ፕሮጀክት፣ መንግሥት የፀጥታ ማስተማማኛ በመስጠቱ፣ ኩባንያው ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

ወደ ሥራ ለመግባት ‹‹ተፈላጊውን ፋይናንስ አላሟላም›› በሚል ከመንግሥት ጋር በውዝግብ የቆየውና ባለፈው ዓመት የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች ሲደርሱት የቆየው የእንግሊዝ ኩባንያ ካፊ ሚነራልስ ባለፉት ስድስት ወራት ወሳኝ የሚባሉ ለውጦች በራሱ፣ እንዲሁም በመንግሥት በኩል በመደረጋቸው ምክንያት፣ ፕሮጀክቱን በይፋ ለመጀመር የሚችልበት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

የከፊ ሚነራልስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ሃሪ አናግኖስታረስ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት በቅድመ ሁኔታ ሲጠይቀው የነበረው የፕሮጀክት ፋይናንስ ጉዳይ በአሁኑ ወቅት እልባት አግኝቷል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. የአፍሪካ ፋይናንስ ትብብር ተቋም አባል ከሆነች በኋላ፣ ሁለት ዋነኛ የፕሮጀክት አበዳሪ ባንኮች መተማመኛ በማግኘታቸው ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡

ባለፈው ወር ለቱሉ ካፒ ወርቅ ልማት አስፈላጊ የሆነውን የፋይናንስ ስምምነት እንደተፈራረመ ይፋ ያደረገው ከፊ ሚነራልስ፣ ይህም ስምምነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፖሊሲና መርህ መሠረት የተከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

ኩባንያው ባለፈው ወር ለሦስት ቀናት የቆየ ዓውደ ጥናት በማካሄድ፣ ከመንግሥት ተወካዮች ጋር በመሆን የድርጊት ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በቀጣይ ወራት ውስጥ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚያስችል ፈጣን እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ከመቼውም ጊዜ በላይ በላይ ፕሮጀክቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን አጠናቀቅን ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከማስተባበርና ከማቋቋም ጀምሮ፣ የአዳዲስ ሠራተኞችን ቅጥር በመፈጸም በመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

የእንግሊዙ ኩባንያ የቱሉ ካፒ የወርቅ ክምችት ለማልማት ፈቃድ የወሰደው እ.ኤ.አ. በ2015 ቢሆንም፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን መጀመር ባለመቻሉ፣ የማዕድን ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጠው እንደነበር ይታወሳል።

ኩባንያው በፊናው የቱሉ ካፒ ፕሮጀክት የሚኝበት የምዕራብ ወለጋ ዞን የፀጥታ ሁኔታ ፋይናንስ ለማግኘት እንደሚያስቸግረው ገልጾ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማበደር ይሁንታ የሰጡት አበዳሪዎች፣ የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ በውጭ ገለልተኛ ባለሙያዎች ካልተገመገመ ብድሩን እንደማይለቁ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡  

ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ ለውጦች በመደረጋቸው ፕሮጀክቱ እንዲጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ይፋ ያደረገው የአንግሊዙ ኩባንያ፣ ከእነዚህም መሀል ኢትዮጵያ ባለፈው መጋቢት ወር የአፍሪካ ፋይናንስ ትብብር ተቋም አባል መሆኗን ተከትሎ፣ ፕሮጀክቱን በፋይናንስ የሚደግፉት የአፍሪካ ንግድና ልማት ባንክ (Trade and Development Bank – TDB) እና የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (Africa Finance Corporation – AFC) ይሁንታ መስጠታቸው አንደኛው ነው፡፡

በሌላ በኩል ከሚያዚያ ወር ጀምሮ መንግሥት በማዕድን ማውጫ አካባቢው ቋሚ የፀጥታ ኃይል ማስፈሩ፣ ኩባንያው በልበ ሙሉነት ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ መተማመኛ እንደሰጠው ሚስተር ሃሪ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የነበራችሁን አለመግባባት እንዴት ፈታችሁት? እናንተ እንደምትገልጹት ፕሮጀክቱ የሚከናወንበት አካባቢ የፀጥታ ሁኔታ የተስተካከለና የተረጋጋ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ሪፖርተር ያቀረበላቸው ሚስተር ሃሪ፣ መንግሥት ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ እንዲገባ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ማሳየቱን፣ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአካባቢው የፀጥታ ኃይል ማስፈሩንና ወደ አካባቢው የሚወስደው መንገድ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው የፋይናንስ አቅርቦትንና የኮንስትራክሽን ሥራን በተመለከተ ካልሆነ በስተቀር የፀጥታ ችግሮችን የመፍታትና የማረጋገጥና ኃላፊነት የመንግሥት ዋነኛ ተግባር በመሆኑ፣ ከመንግሥት የሚሰጥ ማረጋገጫን መሠረት በማድረግ ሥራውን ደረጃ በደረጃ እንደሚያካሂድ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

‹‹ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የነበሩ አለመግባበቶች አሁን ታሪክ ሆነዋል፤›› ያሉት ሚስተር ሃሪ፣ ኩባንያው ቀድሞም ቢሆን ፕሮጀክቱን ለመጀመር ዳተኛ እንዳልነበረ፣ እስካሁን 80 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ የወጣበትን ፕሮጀክት የማያለማበት ምክንያት እንደሌለና አልምቶ መጥቀምንና መጠቀምን እንደሚሻ ገልጸዋል፡፡

የቱሉ ካፒ ወርቅ ፕሮጀክት ሥራ ጀምሮ ወርቅ ለገበያ ያቀርባል ተብሎ በሚጠበቅበት እ.ኤ.አ. በ2025፣ አገሪቱ ወደ ውጭ ልካ ከፍተኛ ገቢ ከምታገኝባቸው የገቢ ምንጮች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጠቀሰው ዓመት ብቻ ከሚቀርበው ወርቅ 250 ሚሊዮን ዶላር ከመገኘቱ ባሻገር አንድ ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ፣ ከአምስት እስከ አስር ሺሕ ለሚሆኑ ቋሚ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጠር የቱሉ ካፒ ወርቅ ማዕድን አክሲዮን ማኅበር መረጃ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች