Saturday, September 23, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከረሃብ ጋር የተፋጠጡ ወገኖችን ለመታደግ ቅድሚያ ይሰጥ!

ለበርካታ ሚሊዮኖች በቀን አንዴ ምግብ ማግኘት ከፍተኛ ችግር እየሆነ ነው፡፡ በግጭቶች፣ በድርቅ፣ እንዲሁም በተለያዩ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሳቢያ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ወገኖች ለከባድ መከራ ተዳርገዋል፡፡ በመኖሪያ ቀዬአቸው ውስጥ የሚኖሩም ሆኑ ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ 30 ሚሊዮን ያህል ወገኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ቢጠባበቁም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት በዘረፋ ምክንያት ዕርዳታ በማቆማቸው የሚቀመስ ነገር አጥተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከትግራይ ክልል የሚሰማው በረሃብ ምክንያት በርካቶች እየሞቱ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ችግር ተባብሶ በሌሎች አካባቢዎች ሊከሰት እንደሚችል ከችግሩ ፅኑነት አኳያ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች በኩል ዕርዳታ በመቋረጡ ሳቢያ ከተፈጠረው አሳሳቢ ሁኔታ በተጨማሪ፣ በተለያዩ አካባቢዎች አርሶ አደሮች በማዳበሪያ ዕጦት ምክንያት የእርሻ ወቅት እያለፈባቸው መሆኑ ሲሰማ ያስደነግጣል፡፡ በዋናው የመኸር እርሻ እንዲህ ዓይነት አስደንጋጭ ዜና ሲሠራጭ፣ የመጪው ዓመት አገራዊ የሰብል ምርት መቀነስ ይዞት ሊመጣ የሚችለው መከራ ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራል፡፡

እጅግ የከፋ ድህነት፣ ሥራ አጥነትና የፀጥታ ችግር ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ምንጮችን ማብዛት ሲገባ የምግብ እጥረት ማባባስ ጤነኝነት አይደለም፡፡ የዘር ጊዜ ካለፈ በኋላ ከጂቡቲ ወደብ ማዳበሪያ አራግፎ የማጓጓዝ እንቅስቃሴ መቀላጠፍን ትልቅ ዜና ለማድረግ ከመሞከር በፊት፣ በጊዜ ኃላፊነትን ለመወጣት መሽቀዳደም መቅደም ነበረበት፡፡ የስንዴ ምርት ክብረ ወሰን በሰበረ መጠን ተመርቶ ኤክስፖርት ማድረግ ተጀመረ በተባለ ማግሥት፣ የተጋነነ የዳቦ ዋጋ ጭማሪና የመጠን ቅናሽ ማየት ያሳቅቃል፡፡ እንደ ሽንኩርትና ቲማቲም የመሳሰሉ የምግብ ክፍሎች አስደንጋጭ የዋጋ ጭማሪ ሲያሳዩ ነገሩ ሁሉ እንቆቅልሽ ይሆናል፡፡ የአገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት በነፍስ ወከፍ ገቢ ተካፍሎ ዳጎስ ያሉ አኃዞች እየታዩ፣ የድህነቱ መጠን ቃላት ከሚገልጹት በላይ ሲሆን ምን እየተከናወነ ነው ያሰኛል፡፡ የምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት በፀጥታ ችግርና ገበያው ውስጥ ዘው ብለው በገቡ ሕገወጦች ታንቆ ተይዞ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ እንደ ዕንቁ ውድ ሲሆን ምንም እንዳልተፈጠረ ቸልተኝነት ማሳየት ያስተዛዝባል፡፡

የምግብ ዋጋ ንረት ብሔራዊ ሥጋት መደቀኑ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ለመንግሥት በተደጋጋሚ ምክረ ሐሳብ ሲቀርብ፣ በኃላፊነት ስሜት ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ የመንግሥት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በምግብ አቅርቦትና ፍላጎት መሀል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ በመሆኑ፣ መንግሥት በአገር ውስጥ ከተመረቱ የምግብ ምርቶች በተጨማሪ ከውጭ ገዝቶም ቢሆን ጉድለቱን መሸፈን ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ በቆሎና ሌሎች የጥራጥሬ ሰብሎችን የሚያመርቱ አርሶ አደሮች፣ በዓመት ውስጥ የረባ ምግብ የሚያገኙት ግፋ ቢል ለሁለት ወራት ብቻ ነው፡፡ የምግብ ዋስትና ጉዳይ ሁሌም ጭንቅና መከራ ከመሆኑም በላይ በየአሥር ዓመቱ ሳይዛነፍ ከተፍ የሚለው ድርቅና ረሃብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ደጋግሞ ስሟን ያስጠራታል፡፡ አሁን ደግሞ በተለያዩ ግጭቶች ሳቢያ ሚሊዮኖች ተፈናቅለው የለጋሾች የዕርዳታ አቅርቦት ሲቆም፣ ከአሁኑ በምግብ ዕጦት ሳቢያ መከሰት የጀመረው ሞት የት ድረስ ለዚልቅ እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ በጥናት ላይ የተመሠረተ ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የምግብ ችግር ወይም ጠኔ ጊዜ አይሰጥም፡፡ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ከተጋለጡት በተጨማሪ፣ ገቢ እያላቸው ምግብ መግዛት ያዳገታቸው ወገኖች ቁጥር በየቀኑ ሲያሻቅብ የሚያስተላልፈው መልዕክት ጥሩ አይደለም፡፡ ከበርካታ ዓመታት በፊት የነበረው ሙግት ኢትዮጵያውያን በቀን ሦስቴ ምግብ ማግኘት እንዳለባቸው፣ በተጨማሪም በፕሮቲንና በቫይታሚን የበለፀጉ ምግቦችን በቀላሉ እንዲያገኙ ምን መደረግ እንዳለበት ነበር፡፡ በተለያዩ የችግር ማዕበሎች በምትንገላታው ኢትዮጵያ ውስጥ ከበቂ በላይ ወጣት ኃይል፣ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ የውኃ አካላት፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮችና መልክዓ ምድሮች፣ በርካታ ማዕድናት፣ በአፍሪካ ወደር የሌላቸው የቱሪስት መስህቦችና ሌሎች ፀጋዎችን መጠቀም ባለመቻሉ ኢትዮጵያውያን ዛሬም በምግብ ዕጦት ይሰቃያሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድነው ሲባል በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲና ስትራቴጂ መቅረፅ አለመቻል እንደሆነ፣ ለብዙ ጊዜ ሲነገር የነበረና ትውልዶች የተቀያየሩበት አዙሪት ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ከዚህ ችግር በመውጣት እንዴት የተራቡ ወገኖችን መታደግ ይቻላል የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከበቂ በላይ ለአገር መፍትሔ ማፍለቅ የሚችሉ ባለሙያዎች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡

የሰላም ዕጦት የእርሻ ሥራዎችን ከማስተጓል በተጨማሪ፣ የተመረቱ ሰብሎች ወደ ገበያ እንዳይቀርቡ ከፍተኛ ተግዳሮት መፍጠሩ ይታወቃል፡፡ ከብልሹው የግብይት ሥርዓት ባልተናነሰ የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱ በሰላም ዕጦት ሲቆራረጥ፣ በአርሶ አደሮችም ሆነ በሸማቾች ላይ ከባድ ጫና ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት መንገዶች ሲዘጋጉ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ወደ ገበያ ባለመቅረባቸው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪዎች ታይተዋል፡፡ አጋጣሚውን ለመጠቀም የፈለጉበት ስግብግቦች የሰቀሉትን ዋጋ ማውረድ ቀርቶ በየዕለቱ ሲጨምሩ ከልካይ የለባቸውም፡፡ በዚህ መሀል አምራቾቹ አርሶ አደሮችም ሆኑ ተከላካይ የሌላቸው ሸማቾች የጉዳቱ ሰለባ ለመሆን ተገደዋል፡፡ የሰላም መታወክ ያልታሰበ ሲሳይ የሚያስገኝላቸው ደግሞ እየተናበቡ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱና እንዲስፋፉ የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከአብዛኞቹ ግጭት በስተጀርባ ያሉት ሴረኞች አገር ብትታመስና ሕዝብ በከባዱ ቢጎዳ ደንታቸው አይደለም፡፡ አገር የእነዚህ መጫወቻ መሆኗ ያንገበግባል፡፡

ለምግብ ችግር በዋነኝነት ከሚጠቀሱት መካከል በጥናት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲና ስትራቴጂ አለመኖር፣ ከኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ አለመላቀቅ፣ የኤክስፖርት አፈጻጸም ደካማ መሆን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የዕዳ ጫና፣ ሙስና አገር እየለበለበ መሆኑ፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር፣ ፍትሕ በገንዘብ መሸጡ፣ በኔትወርክ የተሳሰሩ ሌቦች አገር መዝረፋቸው፣ እሴት ሳይጨምሩ በአንድ ጀንበር ሚሊዮኖች እንደ አሜባ መባዛታቸው፣ የጠባብ ብሔርተኝነት መስፋፋት፣ እንዲሁም የመንግሥት ቢሮክራሲ በደንታ ቢሶችና በአቅም የለሾች መወረሩ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር አለመኖሩም ሌላው ችግር ነው፡፡ ከችግሮች ባሻገር ያለውን ተስፋ ማን ያምጣው? ችግሮች አገርን አንቀው ይዘው መፍትሔ እንዴት አይፈለግም? መፍትሔ የማይገኝ ይመስል ዝምታ እስከ መቼ ይቀጥላል? መንግሥትስ በመፍትሔ አልባ አመራር የት ድረስ ይዘልቃል? ሁሌም በሐሰት የተቀባቡ ሪፖርቶችን እያቀረቡ መቀጠል እንደማያዋጣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይልቁንም ከረሃብ ጋር የተፋጠጡ ወገኖችን ለመታደግ ቅድሚያ ይሰጥ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...