- ከውጭ ምንዛሪና ሌሎች አቅርቦቶች አንፃር የተፈለገውን ማቅረብ አልተቻለም
ግርብና ሚኒስቴር
- ለተገዛው ማዳበሪያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል
ለዘንድሮ የእርሻ ዘመን ክልሎች የሃያ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ፍላጎት ቢያሳዩም፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረትና ተያያዥ የአቅም እጥረት ምክንያት ሊገዛ የቻለው 13.6 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑ ተገለጸ፡፡
ክልሎቹ ፍላጎታቸውን ሰፋ አድርገው ቢያቀርቡም አገራዊ አቅም ባለመፍቀዱ የቀረበውን ፍላጎት ያህል የሚሟላ አለመሆኑን የገለጹት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
አንድ ቢሊዮን ዶላር በሆነ ወጪ 13.6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እንደተገዛ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ተመሳሳይ መጠን ያለው ማዳበሪያ ባለፈው ዓመት በ650 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መገዛቱን ተናግረዋል፡፡
‹‹ከዚህ በላይ ገዝቶ ማቅረብ ቢቻል ፍላጎቱ አለ፡፡ ነገር ግን ካለን አገራዊ አቅም አንፃር ያን ያህል ማቅረብ አልተቻለም፤›› ሲሉ ዓርብ ሐምሌ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ የተናገሩት ሚኒስቴሩ፣ ከዚህ በፊትም በክልሎች ‹‹የቀረበውን ያህል ማዳበሪያ ተገዝቶ አያውቅም›› ብለዋል፡፡
በመጀመርያ ለዓመት የታቀደው 12.8 ሚሊዮን ኩንታል ሆኖ ሳለ፣ በኋላ ለትግራይ ክልል 800,000 በመጨመሩ የዓመቱ ግዥ ወደ 13.6 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ሊል መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የናረው የማዳበሪያ ዋጋ አገሪቷ ካላት አቅም አንፃር ተመጣጥኖ ውሳኔ እንደተሰጠና የተገዛውን ያህል መጠን ብቻ ማቅረብ እንደሚቻል ተገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት ከነበሩት የማዳበሪያ አጠቃቀም ሒደቶች አንፃር ኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በላይ ፍላጎት አሳልፋ እንደማታውቅ፣ በዚህም ሥሌት መሠረት የተገዛው የ13.6 ሚሊዮን ከባለፈው ዓመት ሊያድር ከሚችለው ሁለት ሚሊዮን ጋር በአጠቃላይ የ15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እንደሚቀርብ ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡
ሆኖም ግን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የማዳበሪያ እጥረት እየገጠመ በመሆኑ አርሶ አደሮች ድምፃቸውን ሲያሰሙ እንደቆዩ ይታወቃል፡፡
ለ50 ኪሎ ማዳበሪያ ከዚህ ቀደም ከሦስት እስከ አራት ሺሕ ብር ሲያወጡ የነበሩት አርሶ አደሮች በጥቁር ገበያ ተመሳሳይ መጠን ያለውን ማዳበሪያ አሁን ከአሥር ሺሕ ብር በላይ እንደሚያወጡበት ሲነገር ቆይቷል፡፡
የማዳበሪያ አቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት እንዳለበት በሚኒስትሩ ማብራሪያም ሆነ በገበያው ላይ በሚታየው አሠራር ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
ይህ ክፍተት ትክክለኛ አሥጊ ነው ወይስ አይደለም? በሚለው ጉዳይ ማብራሪያ የሰጡት ግርማ (ዶ/ር)፣ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ያላት የማዳበሪያ አጠቃቀም ከ15 ሚሊዮን ኩንታል አልፎ የማያውቅና እንደ ትልቅ ክፍተት እንደማይቆጥሩት ተናግረዋል፡፡
ለዘንድሮው የማዳበሪያ ግዥ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ውል የታሰረ ቢሆንም፣ ‹‹ከውጭ ምንዛሪ መፍቀድ አለመፍቀድ ጋር በተያያዘና ከተፈቀደም በኋላ ኤልሲ ለመክፈት ክፍተቶች በመኖራቸው፤›› ቀደም ብሎ ግዥው እንዳልተፈጸመ ተገልጿል፡፡
ከተገዛው የማዳበሪያ መጠን 87 በመቶው ጂቡቲ እንደገባ፣ ጂቡቲ ከደረሰው 11.9 ሚሊዮን ኩንታልም 10.7 ሚሊዮኑ ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ተገልጿል፡፡
ከላይ የተገለጸው የማዳበሪያ መጠን ጂቡቲ የደረሰና ወደ አገር ውስጥ የገባ ቢሆንም፣ ለአርሶ አደሩ የደረሰው የማዳበሪያ መጠን 68 በመቶው ብቻ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የማዳበሪያ ግዥ ከዚህ በፊት በተራዘመ የጨረታ ሒደት ብቻ ይካሄድ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ግን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ግዥውን በሁሉም የግዥ አማራጮች ተጠቅመው እንደገዙት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡