Tuesday, October 3, 2023

አደገኛው የጋምቤላ ግጭት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፈው ዓመት መገባደጃ  በጋምቤላ ከተማ፣ በጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና ኦነግ ሸኔ እየተባለ በሚጠራው (የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት) አማካይነት ከባድ ጥቃት መከፈቱ የጋምቤላ ክልልን አለመረጋጋት ውስጥ እንደጣለው ይነገራል፡፡ በጊዜው ለታጣቂዎቹ አፀፋ የሰጠው የጋምቤላ ፖሊስና ልዩ ኃይል ግን በስተኋላ ሰለማዊ ሰዎችን ጭምር አደጋ ላይ የጣለ ያልተመጣጠነ የኃይል ዕርምጃ በመውሰድ በሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ሲወነጀል ነበር፡፡

ከዚያ ወዲህ ከባድ የሚባል ግጭት ዳግም ያገረሸው ደግሞ በግንቦት 2015 ዓ.ም. በተፈጠረው ግጭት ወቅት ነው፡፡ ይህ ግጭት ደግሞ ከሁለት ወራት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ ከፍተኛ ደም መፋሰስ በክልሉ ማድረሱ ነው የሚነገረው፡፡

ጋምቤላ ‹‹በግጭት አዙሪት የተዋጠ ክልል›› ለምን ሆነ? የሚለው ጉዳይ ለረዥም ጊዜ መልስ ሳያገኝ የዘለቀ ነው፡፡ መንግሥት ‹‹በክልሉ ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍን ዕርምጃ መውሰድ ለምን አቃተው?›› የሚለውም ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ እየተነሳ ይገኛል፡፡

በጋምቤላ ክልል ከሰሞኑ የተነሳው ደም አፋሳሽ ግጭት የብሔር መልክ እየያዘ መምጣቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በጋምቤላ ያለው የግጭት አዙሪት ግን የብሔር ወይም የጎሳ መልክ ያለው ብቻ ሆኖ እንደማያውቅ ክልሉን የሚያውቁ ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የድንበር (የመሬት) ጉዳይን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች በክልሉ ተነስተው ያውቃሉ፡፡

በአንዳንድ አጋጣሚዎች ከስደተኞች በተለይም ከደቡብ ሱዳን ከሚገቡ ፍልሰተኞች አሰፋፈርና እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ ችግሮች ተፈጥረው ያውቃሉ፡፡

ለግጭትና አለመረጋጋት እጅግ ተጋላጭ የሚባለው ጋምቤላ፣ ከውጭ ለሚመጣ ችግር ብቻ ሳይሆን ከመሀል አገር ለሚሄድ ቀውስም የተዳረገበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡

በአንድ ወቅት አንድ አንጋፋ የጋምቤላ ነዋሪ ‹‹ዓይናችንን ስንገልጥ ደኑም በቆሎውም የለም›› ብለው እንደተናገሩት ሁሉ፣ ጋምቤላ ክልል በብልሹ የልማት ፖሊሲና ፕሮግራሞች ትግበራ ለጉዳት የተዳረገበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡

እንደ ካራቱሪ ላሉና ለሌሎች የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች በሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት ስም የጋምቤላ ክልል መሬት ሲታደል መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ብዙዎቹ ድርጅቶች በተባለው ሁኔታ ወደ ሥራ ሳይገቡ መቅረታቸው፣ ለእርሻ ኢንቨስትመንት ይውላል የተባለው መሬት ደኑ ተመንጥሮ ያለ ጥቅም ባዶውን መቅረቱ የቀደመውን መንግሥት ክፉኛ ሲያስተቸው ቆይቷል፡፡

በዚህ መሰሉ አስቸጋሪ ሁኔታ አልፎ የሚያውቀው ጋምቤላ ክልል በየጊዜው በትጥቅ የተደገፈ ደም አፋሳሽ ግጭት ሲያገረሽበት መታየቱ ተደጋግሞ የሚከሰት አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡

ይህን በሚመለከት የክልሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች የሚሰጡት አስተያየት ፍፁም የተራራቀና ለማስታረቅም የሚቸግር ሲሆን ይታያል፡፡

በአውስትራሊያ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኡጁሉ ቻም በጋምቤላ ለውጥ እንዳልገባ ይናገራሉ፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በጋምቤላ ስለመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ የተጠየቁት አቶ ኡጁሉ ‹‹የምን ለውጥ ሽግሽግ ነው የተደረገው፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ ‹‹ጋምቤላ ከለውጡ በኋላ የበለጠ የግጭት ቀጣና ሆኗል፤›› ሲሉ ነው አቶ ኡጁሉ ሐሳባቸውን ያከሉት፡፡

ጋዜጠኛ የሆኑት የካናዳ ነዋሪ አጉዋ ጊሎ በበኩላቸው፣ የጋምቤላ ችግር በቀጥታ ከስደተኞች ጋር የተገናኘ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ስደተኞች ከነዋሪዎች በላይ ሆኗል ቁጥራቸው፡፡ ጋምቤላን ቆርሰው የደቡብ ሱዳን አካል የማድረግ ዕቅድ አላቸው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በጋምቤላ ወደ ሰባት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች ከ350 ሺሕ በላይ ስደተኞች መኖራቸውም ይነሳል፡፡ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅቶች ለእነዚህ ስደተኞች ድጋፍ ቢያደርጉም የስደተኞች ቁጥር መብዛት ክልሉ ላይ ጫና መፍጠሩ በተለያዩ ወገኖች ይነሳል፡፡

መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ለስደተኞቹ አመቺ ዕድሎችን መፍጠሩ ዓለም አቀፍ አድናቆት ጭምር ሲቸረው ታይቷል፡፡ ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ ድጋፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በማስፋፋት ለስደተኞቹ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ አንድ ሰሞን ተደጋግሞ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ዜግነት ጨምሮ የመማርና የመሥራት ዕድሎችን መንግሥት እያመቻቸ ስለመሆኑ በሰፊው ሲነገር ቆይቷል፡፡

ይህ ሁሉ አልፎ ግን በጋምቤላ ግጭትና ሁከት በተፈጠረ ቁጥር ስደተኞችን ማዕከል ያደረገ ችግር ስለመኖሩ ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ በተፈጠረው ግጭት ከደቡብ ሱዳን የተነሱ ታጣቂዎች ጭምር ተሳትፈዋል መባሉ ተጨማሪ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በጋምቤላ ምሁራንና ፖለቲከኞች በኩል አኙዋና ኙዌር በሚል የብሔር ልዩነትን መሠረት ያደረገ በዋናነት በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚራመድ ውዝግብ ችግሩ መስመሩን እንዲስት ሊያደርግ እንደሚችል እየተሠጋ ይገኛል፡፡

በጋምቤላ የማዘጋጃ ቤት አመራር የሆኑት ኡሞድ ሳሙኤል ከግንቦት ጀምሮ በጋምቤላ ግድያና ጦርነት መስፈኑን ተናግረዋል፡፡ በኡጋክ በኩል ከደቡብ ሱዳን የገቡ ታጣቂዎች በግጭቶቹ መሳተፋቸውን ይናገራሉ፡፡ ግጭቱና ሞቱ እንዲቆም የፀጥታ አካላት በቂ ጥረት አለማድረጋቸውን ያነሳሉ፡፡

‹‹አሁን ላይ የጋምቤላ ልዩ ኃይል ፈርሷል፡፡ መከላከያ ነው አካባቢውን የሚቆጣጠረው፡፡ በክልሉ ይህ ሁሉ ግጭት ሲደርስ መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ሊጠየቅ ይገባል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ የክልሉ ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ መጠራታቸውንና ከብልፅግና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸውን አመልክተዋል፡፡ ሆኖም መፍትሔ የሚሆን ውሳኔ አለመተላለፉን አመልክተዋል፡፡

‹‹በጋምቤላ የፌዴራል መንግሥቱ ለስደተኞች ነው ለነዋሪዎች የቆመው? የሚል ቅሬታ በሕዝቡ ውስጥ ተፈጥሯል፤›› የሚሉት ኦሞድ፣ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት መንግሥት በቂ የፀጥታ ሽፋን ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትሕ ለሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሳይመን ቱት በበኩላቸው፣ የሰሞኑን ግጭት ችግር ምንጩ የክልሉ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ራሳቸው የጋምቤላ ብልፅግና አመራሮች ናቸው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጦርነት የከፈቱት፤›› በማለት ኃላፊነቱን የክልሉ ባለሥልጣናት እንደሚወስዱ የተናገሩት፡፡

የክልሉ ባለሥልጣናት ስለተፈጠረውና ስለቀጠለው ሰሞነኛ  ግጭት መረጃ እንዲሰጡ ሪፖርተር ተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል፡፡ የክልሉ ፕሬስ ቢሮ (ኮሙዩኒኬሽን) ጉዳዩ ገና እየተገመገመ ስለመሆኑ ቢናገርም፣ ከዚያ የተለየ የተብራራ ዝርዝር መረጃ ለጊዜው ማግኘት አልተቻለም፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ያልተቋጨ የቤት ሥራ›› በሚል ርዕስ በ2014 ዓ.ም. የታተመው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ የሰነደው የበለጠ በላቸው (ዶ/ር) መጽሐፍ፣ ዛሬ ጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ስለሚባለው ክልል ጠቃሚ ነጥቦችን ይዟል፡፡ በምዕራፍ አምስት ላይ የኢትዮጵያና ሱዳን ወሰን አሰማመርና የወሰን ንግግሮችን ሒደት መጽሐፉ በሰፊው ዳሶታል፡፡

በኢትዮጵያና እንግሊዝ በምታስተዳድረው ሱዳን መካከል የመጀመሪያው የወሰን ኮሚቴ ንግግር እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 29 ቀን 1947 ነው የተጀመረው ይላል መጽሐፉ፡፡ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ በለንደን ከሚስተር ሆው ጋር እ.ኤ.አ. 1946 በባሮ፣ ፒቦርና በአኮቦ ወንዞች ትይዩ ያለውን የግንቦት 1894 (እ.ኤ.አ. ግንቦት 15 ቀን 1902) ወሰን ስለማሻሻል ያደረጉት ውይይት ለወሰን ኮሚቴው መሰብሰብ ምክንያት ሆነ፡፡ በኮሚቴው አባልነት በኢትዮጵያ በኩል አቶ አበበ ገብሬ (የቡድን መሪ)፣ ሜጀር ዮሐንስ አብዱ እና ብላታ መርስሄ ሐዘን ተወከሉ፡፡ በእንግሊዝ ሱዳኖችን በመወከል ደግሞ ጂኢአር ሳንደርስ (ኃላፊ) እና ኢኤች አልባን ተመደቡ፡፡ በመጀመሪያው ዙር ግንኙነት ኢትዮጵያ የሱዳንን አቋም ማድመጥና ማጤን እንደመረጠች በዚህ መጽሐፍ ተቀምጧል፡፡

የባሮ ሸለቆ አካባቢ የሁለቱን አገሮች የውስጥ አከላከል በሰፊው ወደ መተረክ የሚገባው መጽሐፉ፣ ሻለቃ ጉዌን የተባለው ሰው ጋምቤላ ድረስ መጥቶ በ1894 (እ.ኤ.አ 1902) ሁለቱንም አገሮች በመወከል እንዳካለለው ይጠቅሳል፡፡ በዚህ ስምምነት ውስጥ አባሪ ሆኖ በገባው ካርታ ውስጥ በቀይ ቀለም ከኮም ኡመሃጀር ጀምሮ ጥቁር ዓባይን፣ ባሮን፣ ፒቦርንና የአኮበን ወንዞች ይዞ ወደ ሄሊል (ኢሌሚ ትሪያንግል ተብሎ እስከሚጠራው ቦታ) ድረስ ተሰምሯል፡፡ ሆኖም ሻለቃ ጉዌን ከአኮቦ በስተደቡብ ወደሚገኙ ቦታዎች ስላልሄደ ከጃካኦ በስተደቡብ ያለውን ድንበር በአግባቡ የመከለሉ ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑን መጽሐፉ ያስነብባል፡፡

በወሰኑ አሰማመር ላይ ግን ሱዳኖቹ ያነሱት ቅሬታ ወሰኑ ሲሰመር ወንዞችን ብቻ ተከትሎ መሆኑ አግባብ አይደለም የሚል ነበር፡፡ ሱዳኖቹ ሻለቃ ጉዌን የሱዳን የኒሎቲክ ጎሳዎች የሆኑትን የኙዌርና አኙዋ ሕዝቦችን በኢትዮጵያው ውስጥ እንዲካለሉ አድርጓል የሚል ስሞታ አቅርበዋል፡፡

በዚህ የተነሳም አንደኛ ከሰሜን በጂካኦ አቅራቢያ ካለው ካጂጀኒ ተነስቶ እስከ በስተደቡብ እስካለው የኢለሚ መንደር ድረስ የጎሳ አሰፋፈርን መሠረት ያደረገ የወሰን ማካለል እንዲደረግ ኢትዮጵያ ልትስማማ እንደሚገባ ሱዳኖቹ ጠየቁ፡፡

በሁለተኛም የኒሎቲክ ጎሳዎች የሆኑት ሁለቱ የኙዌርና የአኙዋ ሕዝቦች የጎሳ ወሰንን በመከተል ሙሉ ለሙሉ ወደ ሱዳን እንዲጠቃለሉም ሱዳኖች  ጠይቀዋል፡፡

ሁለተኛው የኢትዮ ሱዳን የወሰን ኮሚቴ እ.ኤ.አ. ግንቦት 6 ቀን 1947 ሲካሄድ ግን፣ የኢትዮጵያ ኮሚቴ አባላት በጉዳዩ ላይ ምላሽ ይዘው መቅረባቸውን መጽሐፉ ይተርካል፡፡

የኢትዮጵያ የወሰን ኮሚቴ መጀመሪያ የሻለቃ ጉዌን ወሰን አከላለል ሪፖርት ሙሉ ለሙሉ እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡ ሱዳንን የወከሉት እንግሊዛዊያኑ ተደራዳሪዎች ግን እርሱ ጊዜ እንደሚወስድ መናገርን መረጡ፡፡

የኢትዮጵያ የወሰን ኮሚቴ ጎሳን መሠረት ያደረገ የወሰን አሰማመር በባሮ ሸለቆ ቢደረግ ልክ በጂቡቲ፣ በኬንያና በሶማሌ ድንበሮች በኩል ያጋጠሙ ዓይነት ችግሮች ኢትዮጵያ እንደሚገጥማት ምላሽ ሰጠ፡፡

የሱዳኖቹ ተወካዮች ግን በባሮ ሸለቆ ያለው ሁኔታ ጎሳን መሠረት ላደረገ የወሰን አሰፋፈር የተመቸ መሆኑን አጥብቀው ተከራከሩ፡፡ የኢትዮጵያ ተወካዮች ግን ለዚህ አማራጭ ያሉትን መፍትሔ አቀረቡ፡፡

የኙዌር ጎሳ አብዛኛውን በሱዳን የሚኖር ሲሆን ጥቂቱ ግን በኢትዮጵያ በባሮ ሸለቆ መኖራቸውን አመለከቱ፡፡ አኙዋኮች ግን አብላጫዎቹ በኢትዮጵያ የሚኖሩ መሆናቸውን ገለጹ፡፡ በዚህም መሠረት ኙዌሮችን ወደ ሱዳን አኙዋኮችን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አሰፋፈራቸውን ተከትሎ መከለል እንደሚቻል የኢትዮጵያ ኮሚቴ ግልጽ አደረገ፡፡

የሱዳኖቹ ተወካዮች ግን ሁለቱንም ጎሳዎች ወደ ሱዳን እንዲጠቃለሉ የመፈለግ ነበር፡፡ ጎሳን መሠረት ያደረገ አከላለል ይደረግ መባሉ የምዕራብ ኢትዮጵያ የንግድ በር የሆነው ጋምቤላ ወደ ሱዳን እንዲሄድ መፍቀድ መሆኑ የገባቸው የኢትዮጵያ የጊዜው ተደራዳሪዎች የሱዳኖቹን ጥያቄ ውድቅ እንዳደረጉት ነው የበለጠ በላቸው (ዶ/ር) መጽሐፍ በዝርዝር የከተበው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 የቀረበው የሐጎስ ሳሙኤል ዘውዴ “Refugees and Local Power Dynamics: the case of Gambella region of Ethiopia” ጥናት የጋምቤላ ክልልን ቀውስ ምንጭ ከመነሻው ለመፈተሽ ይሞክራል፡፡ በጋምቤላ ክልል በየጊዜው የሚከሰተውን የአኙዋና ኙዌር ጎሳዎች ውጥረትን ለመረዳት በክልሉ ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን የስደተኞች ፍሰት ታሪክ ወደ ኋላ ተመልሶ መፈተሽ ይጠይቃል ሲል ነው ጥናቱ ወደ ሀተታው የሚገባው፡፡

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የኙዌር ሕዝቦች ወደ ምሥራቅ መስፋፋት እንደጀመሩ ጥናቱ ያነሳል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው በባሮ ወንዝ አቅራቢያ በአኬዶ አካባቢ በላጂክ ኮረፕታዎች መስፈር መጀመራቸውን ያወሳል፡፡

ኙዌሮች በደቡብ ሱዳን ባህር ጀበል ወንዝ ዳርቻ በተወሰነ አካባቢ ይኖሩ እንደነበር ታሪክ አጣቅሶ ያቀርባል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ግን ጋጃክስ፣ ጋጆክና ጋግዋንግ የተባሉ የኙዌር ንዑስ ጎሳዎች ከደቡብ ሱዳን ወደ ምሥራቅ በመፍለስ ወደ ኢትዮጵያ መግባት መጀመራቸውን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1902 የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር መሰመሩ የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት የቀየረ ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ከዚያ ወዲህም ቢሆን ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ፍልሰት አለመቆሙን ነው ያመለከተው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ወዲህም ፍልሰት መኖሩን ጥናቱ ያነሳል፡፡ በጊዜው ግን ፍልሰተኞቹን የሚቀበለው ራሱ ሕዝቡ ነበር ይላል፡፡ አኙዋዎች ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ስደተኞቹን ተቀብሎ በማስተናገድ ችግር አልነበረባቸውም፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል እስከ ጋብቻ የደረሰ አብሮ የመኖርና የመቀላቀል ባህል መፈጠሩንም ይጠቅሳል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1974 እስከ 1987 የጋምቤላ አካባቢ ኢሉባቦር እየተባለ ሲጠራ መቆየቱንና በ1987 መደበኛ የአስተዳደር ሥልጣን እንደተበጀለት ጥናቱ ይጠቅሳል፡፡ በደርግ ዘመን ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ስደት በማዕከላዊ መንግሥቱ ቁጥጥር ይደረግበት ጀመር፡፡ ከውጭ የሚገቡ ስደተኞችን የማስተናገድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወደ ጋምቤላ የሚደረገው የሰፈራ ፕሮግራም በመንግሥት ይመራ ጀመር፡፡

ይህ ሁሉ የጋምቤላ አካባቢ ሕዝቦች ስብጥርን መቀየሩ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ ደርግ ወድቆ ኢሕአደግ ሲተካ ደግሞ ጎሳና ብሔርን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ተፈጠረ፡፡ በደርግ የሰፈራ ፕሮግራም ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍል ሄደው ከሰፈሩት ደገኛ (ሐበሻ) ተብለው በተለምዶ ከሚጠሩት ማኅበረሰቦች ውጪ ያሉት ሕዝቦች ነባር ብሔር የሚል የፖለቲካ ስም ተሰጣቸው፡፡

ነባር ብሔር የሚለውን ጥቅል ስም አኙዋ፣ ኙዌር፣ ማጃንግ፣ ኦፖ፣ ከሞ የተባሉ ሕዝቦች አገኙ፡፡ ነገር ግን ነባር ብሔር የሚለው የወል ስም ምን ዓይነት አተረጓጎም ወይም የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዳለው ባልተብራራ ሁኔታ መታለፉ ትልቅ ችግር መሆኑን ያነሳል፡፡ ይህ በመሆኑ በእነዚህ ሕዝቦች መካከል የወሰን፣ የመዋቅር፣ የሀብትና የአስተዳደር ሽሚያ እንዲፈጠር ጥንስስ መፍጠሩንና በፉክክር ውጥረቶች ሁሌም እንዲኖሩ ማድረጉን ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የጎረቤት አገሮች ስደተኞችን በማስተናገድ ከቀዳሚዎቹ አንዷ መሆኗ የጋምቤላ ችግርን ካወሳሰቡ ጉዳዮች እንደ አንዱ በዚህ ጥናት ይነሳል፡፡ ከደቡብ ሱዳን 338 ሺሕ 250፣ ከሶማሊያ 198 ሺሕ 670 ከኤርትራ 171 ሺሕ 876፣ ከሱዳን 42 ሺሕ119 ስደተኞችን ተቀብላ በ26 የስደተኞች ጣቢያዎች ታስተናግዳለች፡፡

ጋምቤላ ክልል ከ321 ሺሕ በላይ ማለትም ከ94 በመቶ በላይ የደቡብ ሱዳን ፍልሰተኞችን እንደሚያስተናግድ ጥናቱ ያመለክታል፡፡ ይህ በክልሉ ያለውን የሀብት፣ የአስተዳደርና የወሰን ክፍፍል የበለጠ ውጥረት ውስጥ የከተተ ጉዳይ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ በተለይ በሁለቱ የአኙዋና ኙዌር ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ያሻከረው ይኼው መሆኑ በጥናቱ ተነስቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ የተፈጠሩ ግጭቶች በ2018 እና በ2019 እየደጋገሙ የማገርሸታቸው ሚስጥር የስደተኛ ቁጥር መጨመሩ የፈጠረው ውጥረት ውጤቶች መሆናቸውንም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጉዳዮች ላይ ሰፊ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማት ሕሩይ አማኑኤል (አምባሳደር) ከጥቂት ዓመታት በፊት ተዘጋጅቶ በነበረ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ጥናታዊ መድረክ ላይ የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳንን ግንኙነት በጥልቀት ፈትሸውት ነበር፡፡ ደቡብ ሱዳኖች ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን የነፃነት ትግልን በመደገፍ ትልቅ ሚና መጫወቷን እንደሚረዱ አንስተዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ (SPLM) በኢትዮጵያ መደገፉን የሚገልጹት ሕሩይ (አምባሳደር) ነገር ግን በአንዳንድ የደቡብ ሱዳን ኃይሎች ዘንድ የጋምቤላ አካባቢ የደቡብ ሱዳን አካል መሆን አለበት የሚል አመለካከት ሰፍኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹የደቡብ ሱዳን ጎሳዎች የሚኖሩበት አካባቢ ወደ ደቡብ ሱዳን መካለል አለበት የሚል አመለካከት አለ፡፡ የኙዌሮች ምድር (ኙዌር ላንድ) የሚል አስተሳሰብ በኅብረተሰቡ ውስጥ አለ፡፡ በአንድ በኩል ይህ ጋምቤላንም ያጠቃልላል፡፡ ዛሬ ይህን አንስቶ ግጭት መፍጠሩ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ጋምቤላ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ተቀባይ እንጂ ወደ ደቡብ ሱዳን ስደተኞችን የማትልክ አካባቢ ናት፡፡ የሌለ ችግር እያወራህ ነው እንዳትሉኝ እኔ ደቡብ ሱዳን በአካል አይቼዋለሁ፡፡ ይሀን ጉዳይ በተመለከተ ለወደፊቱ በደንብ ማሰብ አለብን፤›› በማለት ነበር ኢትዮጵያ በጋምቤላ በኩል ከየት አቅጣጫ ለሚነሳ ቀውስ ሰለባ እንደምትሆን ሕሩይ (አምባሳደር) የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -