Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎችና በመከላከያ መካከል በተፈጠረ ግጭት መንገዶች መዘጋታቸው ተሰማ

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎችና በመከላከያ መካከል በተፈጠረ ግጭት መንገዶች መዘጋታቸው ተሰማ

ቀን:

  • መከላከያ በበኩሉ ሠራዊታችንን ማሸነፍ ያልቻሉ ኃይሎች በሠራዊታችን ላይ የሚጎነጉኑት ሴራ ከፍ እያለ መጥቷል ብሏል

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎችና በመከላከያ መካከል ተፈጠረ በተባለ ግጭት መንገዶች መዘጋታቸውን የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

በደንበጫ፣ ፈረስ ቤት፣ በፍኖተ ሰላም፣ በቋሪት፣ በጅጋ፣ ሞጣና ወይን ውኃ በሚባሉ አካባቢዎችና በዙሪያው ከሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መከላከያ እንደገባ፣ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በታጣቂዎችና በመከላከያ መካከል የከባድ መሣሪያ ተኩስ ልውውጥ እየተደረገ እንደሆነ የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል፡፡ በተኩሱ ሳቢያ በእነዚህ አካባቢዎች መንገዶች መዘጋታቸውንም አክለዋል፡፡

ከባህር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ 63 ተሳፋሪዎች ‹‹ቱሉሚልኪ›› በተሰኘ ቦታ ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በታጣቂዎች መታገታቸውንና መንገዱ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑም ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

በተጨማሪም ሰሜን ወሎ ዞን ከወልዲያ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ጉባ ላፍቶ ወረዳ፣ ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በወረዳው ሳንቃ በተባለው ሥፍራ ከቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠ፣ በመከላከያና በታጣቂዎች መካከል ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር፣ በለስ መገንጠያ ተብሎ በሚጠራው ልዩ ቦታ መከላከያና ታጣቂዎች እንደተገዳደሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ነዋሪው ከተኩስ ልውውጡ በኋላ ታጣቂዎቹ ወደ ጫካ ሲገቡ፣ መከላከያው ጉዳት የደረሰባቸውን ካነሳ በኋላ ቤት ለቤት እየገባ ብርበራና ፍተሻ ማካሄዱን ተናግረዋል፡፡ ነዋሪው ላይ እንግልትና ሥጋት ውስጥ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንፁኃን ሰዎች ወደ ሕክምና እንደተወሰዱ፣ ትናንት ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ተኩሱ እንደቆመም ነዋሪው አክለዋል፡፡

ተደረገ የተባለውን የተኩስ ልውወጥ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የሰሜን ወሎ ዞን ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለ ማርያም አምባዬ፣ ‹‹ሥራ ላይ ነኝ፤›› ብለው ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኮማንደር ተመስገን ቢረሳቸው በበኩላቸው ከሪፖተር ለቀረበላቸው ተመሳሳይ ጥያቄ፣ ‹‹ስብሰባ ላይ ነኝ፡፡ ስብሰባቸው ስንት ሰዓት እንደሚያልቅ አላውቅም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በክልሉ በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ከቆቦ ከተማ ወጣ ብሎ በስተ ምዕራብ ቀመሌና አካባቢው በታጣቂዎችና በመከላከያ መካከል በከባድ መሣሪያ ጭምር የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ነዋሪዎቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳስረዱት ከሆነ፣ የተኩስ ልውውጥ የተደረገው ከሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ረፋዱ 4፡00 ሰዓት ድረስ ነው ተብሏል፡፡

‹‹የተኩስ ልውውጡ ያለ ማቋረጥ ለሰዓታት ተደርጓል፤›› ያሉት ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው ሦስት የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች፣ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ተፈጥሮ በነበረው ጦርነትም እንዲህ ዓይነት ከባድ መሣሪያ አልተተኮሰም፣ ሰሞኑን ሲተኮስ የሰማነው የመሣሪያ ድምፅ ከባድ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከሦስት ሳምንት በፊት በቆቦ ከተማና ዙሪያው በተከፈተ ተኩስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካቶች መቁሰላቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከትናንት ከማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ተኩስ እንደቆመ፣ ከሰዓት በኋላ በርካታ ቁጥር ያለው መከላከያ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ፣ በከተማው የተኩስ ልውውጥ እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ፣ ‹‹የተለያዩ ግጭቶች በሚስተዋልባቸው አካባቢም ሠራዊቱ ትዕዛዝ አልተሰጠንም በማለት የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም አድርጓል የሚል ትችት ለሚሰነዝሩ አካላት፣ የሠራዊቱን መርሆዎች በደንብ ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፤›› ሲል ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

የመግለጫው ዓላማ፣ ‹‹አሁን ላይ ሠራዊታችንን ፊት ለፊት ገጥመው ማሸነፍ ያልቻሉ ኃይሎች፣ በተለያየ መንገድ በጀግናው ሠራዊታችን ላይ የሚጎነጉኑት ሴራ ከፍ እያለ በመምጣቱ፣ ውሸት ሲደጋገም እውነት የሚመስላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሠራዊቱ ሸሽቷል፣ ተማርኳል፣ በዚህ ወጥቷል፣ በዚህ ገብቷል የሚለው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን ለማሳየት ነው፤›› ብሏል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...