‹‹ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር በተለይ በብሪክስ ጉዳይ ተወያይተናል››
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ኢትዮጵያ አባል ለመሆን ፍላጎት ያሳየችበት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ (BRICS) ቡድን አባል አገሮች መሪዎች የኢትዮጵያንና የሌሎች አገሮችን የመቀላቀል ጥያቄ ለማስተናገድ፣ በነሐሴ ወር በሚካሄደው ጉባዔ እንደሚያፀድቁ፣ የደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ ናሌዲ ፓንዶር (ዶ/ር) ሰሞኑን በአዲስ አበባ በነበራቸው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት ስለኢትዮጵያ ብሪክስን የመቀላቀል ዕድል ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ከኢትዮጵያና ከሌሎችም አገሮች እየቀረቡ ያሉትን ጥያቄዎች ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአምስቱ የብሪክስ አባል አገሮች መሪዎችና ተወካዮች (ደቡብ አፍሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድና ብራዚል) እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 22 እስከ 24 ቀን 2023 በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በሚያካሂዱት ጉባዔ አዳዲስ አባላት በማካተት፣ ‹‹መመርያዎችና ዘዴዎች ላይ፣ እንዲሁም ቡድኑን የማስፋት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ያሳልፋሉ፤›› ሲሉ ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
የብሪክስ አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአባልነት ጥያቄዎችን ተቀብለው በሚያስተናገዱበት አሠራር፣ መመርያዎችና ዘዴዎች ላይ እየተወያዩበት እንደሆነ፣ ውጤቱ ደግሞ ለመሪዎቹ ጉባዔ ቀርቦ ‹‹የመጨረሻ ውሳኔ›› እንደሚተላለፍበት አስረድተዋል፡፡
ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ 150ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በአዲስ አበባ በስካይላይት ሆቴል ተገኝተው ያከበሩት ሚኒስትሯ ፓንዶር (ዶ/ር)፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በተለይ በብሪክስ ጉዳይ መልካም ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ (የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)ን በብሪክስ ጉባዔ እንዲካፈሉ ጋብዘዋቸዋል፤›› ሲሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስለነበራቸው ውይይትም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ በተጨማሪም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስላደረጉት ውይይት ሲገልጹ፣ በአኅጉሪቱ ወሳኝ በሆኑት በሁለቱ አገሮች (ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ) መካከል ትብብርን ለማሳደግ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ‹‹በአፍሪካ የመሪነት ሚና የሚጫወቱ›› መሆናቸውን፣ ይህንንም ሚናቸውን ማጠናከርና ማስቀጠል በሚችሉበት ላይ ውይይቱ እንዳተኮረም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ በብሪክስ የመካተት ዕድል ላይ ሪፖርተር ላነሳላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወሳኝ አገር ናት፣ ሆኖም ሌሎችም 22 አገሮች መቀላቀል ይፈልጋሉ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ጨምሮ የመቀላቀል ዕድል ያላቸው በርካታ አገሮች ናቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ሚኒስትሯ እሑድ ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከገቡ በኋላ፣ በቀጣዩ ቀን በተካሄደው በአራተኛው የደቡብ አፍሪካና የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በስብሰባው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በሁለቱ አገሮች የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በኮልፌ የቀድሞ ፈጥኖ ደራሽ የፖሊስ ማሠልጠኛ የመጀመሪያው ጥቁር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ፣ በትግላቸው ወቅት በኢትዮጵያ ሲሠለጥኑበት የነበረውና በኋላም በስማቸው ወደ ሙዚየምነት የተቀየረውን ሕንፃ ጎብኝተዋል፡፡
በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚካሄደውን የብሪክስ ጉባዔ በወቅቱ ቡድኑን በሊቀመንበርነት የምትመራው ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ሁሉም የአኅጉሪቱ መሪዎች በጉባዔው እንዲሳተፉ መጋበዛቸው የሚታወስ ነው፡፡
ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ ብቻ አባል የሆነችበት ብሪክስ ሩሲያን ሳይጨምር የቡድኑ አባል አገሮች ሁሉም በመሪዎች ደረጃ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት በሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ትዕዛዝ በማውጣቱና ደቡብ አፍሪካም የፍርድ ቤቱ አባል በመሆኗ ፕሬዚዳንቱን ለማሰር ስለምትገደድ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ እንደሚወከሉና በቪዲዮ ስብሰባውን እንደሚከታተሉት መገለጹ አይዘነጋም፡፡