Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምኢኮዋስ የሚፈተንበት መፈንቅለ መንግሥት

ኢኮዋስ የሚፈተንበት መፈንቅለ መንግሥት

ቀን:

የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) አባል አገሮች መፈንቅለ መንግሥት የሚፈታተናቸው ሆነዋል፡፡ አገሮቹ በኢኮዋስ መፈንቅለ መንግሥት እንዳይካሄድ እየጣሩ፣ ከተካሄደም በተካሄደበት አገር ማዕቀብ እየጣሉ ድርጊቱን ለመከላከል ቢጥሩም አልተሳካም፡፡

አባል አገሮቹ፣ እ.ኤ.አ. ከ2020 ወዲህ ብቻ ባሳለፍነው ሳምንት በኒጀር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ጨምሮ አምስት መፈንቅለ መንግሥቶችን አስተናግደዋል፡፡

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ የኢኮዋስ ሊቀመንበር ሆነው በተሾሙ በ15ኛው ቀን በኒጀር የተፈጸመው መፈንቅለ መንግሥት፣ እሳቸው በቀጣናው እናስቀረዋለን ብለው ቃል የገቡበትን ንግግር ያከሸፈም ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ የኢኮዋስ ሊቀመንበር ሆነው ከ20 ቀናት በፊት ሲሾሙ ‹‹የኢኮዋስ ቀጣና ከዚህ በኋላ መፈንቅለ መንግሥትን አይታገስም፡፡ ለዴሞክራሲ መቆም አለብን፡፡ ካለዴሞክራሲ አስተዳደር፣ ነፃነትም ሆነ የሕግ መከበር አይኖርም፤›› ብለው ነበር፡፡

ሆኖም እሳቸው የኢኮዋስ ሊቀመንበርነቱን ይዘው ወር እንኳን ሳይሞላቸው ነበር የኒጀር ፕሬዚዳንታዊ ዘብ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዞምን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ያስታወቀው፡፡

መፈንቅለ መንግሥቱን ያወገዙት ፕሬዚዳንት ቲኒቡ፣ በቤንን ፕሬዚዳንት ፓትሪክ ታሎን የተመራ አሸማጋይ ቡድንም ወደ ኒጀር ልከው ነበር፡፡ ለአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስና ለሌሎችም የውጭ አገር መሪዎች የስልክ ጥሪ ያደረጉት ቲኑቡ፣ በሳምንቱ ማብቂያ ላይም የኢኮዋስ አባል አገሮች መሪዎችን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው በአቡጃ መክረዋል፡፡

አልጀዚራ እንዳሰፈረው፣ 15 አባል አገሮች ያሉት ኢኮዋስ ከአስቸኳይ ስብሰባው በኋላ በኒጀር ላይ የአየር በረራን ጨምሮ የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥሏል፡፡

በኒጀር መፈንቅለ መንግሥቱን ላከናወነውና በአብዱራማን ቴቻኒ የሚመራው ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ሕገ መንግሥታዊውን አሠራር ወደነበረበት እንዲመለስ የሳምንት ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ይህ ካልሆነ ኃይል እንደሚጠቀም ጠቁሟል፡፡

በቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒና ማሊ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ለተከናወኑት መፈንቅለ መንግሥቶች ኢኮዋስ ጠንኮራ ዕርምጃ አልወሰደም በሚል ሲተች የከረመ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ጠንከር ብሎ መውጣቱን ዘገባው ያሳያል፡፡

ሆኖም የኒጀር ወታደራዊ ሽግግር መንግሥት፣ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት አስጠንቅቋል፡፡

ከዚህ ቀደም በቡርኪና ፋሶና ማሊ መፈንቅለ መንግሥት ያደረጉ ወታደራዊ መሪዎችም የኒጀሩን ፕሬዚዳንት ባዞም ወደ ሥልጣን መመለስ ‹‹የጦር አዋጅ እንደማስነግር ነው›› ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የኢኮዋስ ማኅበረሰብን ሊከፋፍለው ይችላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

በአገር ውስጥ ችግር ሳይሆን በውጭ ላለው ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጥ ነበር በሚል ሲተች የከረመውን የኒጀር የቀድሞ መንግሥት ለማምጣት ወታደራዊ ዕርምጃ መውሰድም የኒጀር ዜጎች ለተቃውሞ እንዲወጡ ያደርጋል ሲሉም፣ በዓለም አቀፍ ክሪያሲስ ግሩፕ ኤክስፐርት ናማዲ ኦባሲ ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል በኒጀር ጉዳይ ጣልቃ ተገብቶ ችግሩን መፍታት ካልተቻለ ችግሩን የከፋ ሊያደርገውም ይችላል፡፡ ምክንያቱም በኢኮዋስ አባል አገሮች ውስጥ የሽብር ጥቃት እየተስፋፋ ነው፡፡

በአገሮቹ በ2023 የመጀመርያው መንፈቅ ብቻ 1,800 የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ በዚህም 4,600 ሰዎች ሲሞቱ 4.5 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የኢኮዋስ ኮሚሽን ሊቀመንበር ኦማር ቶሬይ ባለፈው ወር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እንዳስታወቁት፣ በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አባል አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ ካልተስተካከለ የቀጣናው ደኅንነት የከፋ አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡

ከዚህ ቀደም መፈንቅለ መንግሥት በተካሄደባቸው ማሊ፣ ቡርኪናፋሶና ጊኒ በታጠቁ ኃይሎች የሚሰነዘር ጥቃትም እንደቀጠለ ነው፡፡

ፀረ ፈረንሳይ አመለካከት እያደገ መምጣቱም ወታደሮች አገሮችን እንዲቆጣጠሩ ዕድል እየፈጠረ ነው፡፡

በአባል አገሮቹ ውስጥ ያሉ አለመረጋጋቶች ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር ተደምረው ኢኮዋስን እየፈተኑት ይገኛሉ፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም፣ አባል አገሮቹ በኒጀር የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት የሚይዙበት አኳኋን ተቀባይነት ያለው መሆን አለበት፡፡ አገሮቹ ኃይላቸውን ማጠናከር ላይ ካልሠሩም በቀጣናው የሚታየው የመፈንቅለ መንግሥት ልማድ ለቀጣናው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ሥጋት ይሆናል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1990 ወዲህ በአፍሪካ 43 መፈንቅለ መንግሥቶች ተደርገዋል፡፡ 41 የመፈንቅለ መንግሥት ጥረቶች ደግሞ ከሽፈዋል፡፡ ከከሸፉት ውስጥ አሥራ ሦስቱ ከ2000 እስከ 2009 ድረስ ባሉት ጊዜያት የተሞከሩ ሲሆን፣ 36 ሙከራዎች የተከናወኑት ደግሞ ከ2010 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ከ2020 እስካሁን ደግሞ አፍሪካ ዘጠኝ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን አስተናግዳለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...