Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሴቶች የንጽሕና መጠበቂያዎች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡት መቼ ነው?

የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያዎች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡት መቼ ነው?

ቀን:

ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች (ሪፎርሞች) በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

ከማሻሻያዎቹ መካከል ተማሪዎች የሚማሩት ትምህርት ከዘመኑ ጋር ተስማሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የትምህርት ተቋማትን ምቹና ማራኪ እንዲሆኑ ማስቻልና በተለይ ለልጃገረድ ተማሪዎች የወር አበባ ጤናና ሥነ ንጽሕና መጠበቂያ አገልግሎቶችን ማቋቋምና በሚገባ ማደራጀት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራምና የጥራት ማሻሻያ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ዋጌሶ እንደገለጹት፣ ለተማሪዎች በክፍል ውስጥ የመገኘት፣ የመቆየትና የመዝለቅ ምጣኔ በወንድና በሴት ሲነጻጸር ሴቶች ሌሎች ተደራራቢ ችግሮቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው ከወር አበባ ጋር በሚገናኙ ችግሮች ሳቢያ 20 በመቶ የሚሆኑት የትምህርት ቀናት ይባክኑባቸዋል፡፡

ለሴት ተማሪዎች ይህን ያህል መጠን ያላቸው የትምህርት ቀናት ባከኑ ማለት ተፈላጊውን ዕውቀት እንዳይጨብጡ ምክንያት እንደሚሆንባቸው፣ በዚህም የተነሳ ወደኋላ እንደሚቀሩ፣ በዚህም ተስፋ ይቆርጡና ትምህርታቸውን እንደሚያቋርጡ ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡

‹‹ተስፋ ሳይቆርጡ እየሄዱ ቢማሩም አንድ ክፍል ይደግማሉ፣ እንደምንም ብለው የማይደግሙ ቢሆንም እንኳን ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር እኩል ለመሆን ዕድላቸው አነስተኛ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጥረቶቹ በቂ ናቸው ብሎ መወሰድ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የወር አበባ ጤናና ሥነ ንጽሕና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ቁርጠኛ ነን›› በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው ዓውደ ጥናት ኃላፊው አቶ ዮሐንስ እንዳብራሩት፣ እንደ አገር ከ51,000 በላይ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ለሴት ተማሪዎች ምቹ ሁኔታ ወይም የተሟላ መሠረተ ልማት ያላቸው ትምህርት ቤቶች በአኃዝ እጅግ በጣም አነስተኛ ናቸው፡፡

በመቶኛ እንኳን ቢወሰድ ከ12 በመቶ እንደማይበልጡ፣ ከዚህ አንጻር 88 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ተፈላጊውን መሠረተ ልማት ያሟሉ እንዳልሆኑ፣ ስለዚህ ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት የማሻሻል ዘመቻ በመካሄድ ላይ እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የዘመቻው አካል ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት በሚመጡበት ጊዜ የትምህርት ቤት ቆይታቸው ምቹ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችለውን የወር አበባ ጤናና ሥነ ንጽሕና አጠባበቅን የሚመለከት ተግባራትን ማከናወን እንደሚገኝበት ገልጸዋል፡፡

ይህንንም አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር አካታችና ተደራሽ የሆነ የውኃ፣ የመፀዳጃ ቤትና የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ክፍሎችን ለመገንባት የሚያስችሉና ደረጃቸውን የጠበቁ ልዩ ልዩ ዲዛይኖችን በማዘጋጀት የወር አበባ ጤናና ሥነ ንጽሕና አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ቁርጠኛነቱን ማሳየቱን ነው ያመለከቱት፡፡

የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይነህ ጉጆ አካል ጉዳተኞች ከጤና ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በተለይ 24 ሰዓት ዊልቸር ላይ ቁጭ የሚሉት ሴቶችና ልጃገረዶች ከወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚመጣባቸው ችግር ከሁሉም በላይ አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ከሴት አካል ጉዳተኞች መካከል የትምህርት ዕድል ያላገኙ እንዳሉ ገልጸው ዕድሉ ተሳክቶላቸው በትምህርት ገበታው የሚገኙ ቢኖሩም የወር አበባቸው ሲመጣባቸው በአግባቡ መቆጣጠር የማያስችላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ዞር ብለው ምን እንደተፈጠረ እንኳን ማየት የማይችሉ ዓይነ ስውራንና የአዕምሮ እክል ያለባቸው ሴቶችና ልጃገረዶች ችግር በእጅጉ የከፋና የባሰ መሆኑን ነው ኃላፊው የጠቆሙት፡፡

የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጃ ድጉማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ምርቶችን ማግኘት የቅንጦት ዕቃ የሆነባቸው በርካታ ልጃገረዶችና ሴቶች እንዳሉ፣ ይህ ዓይነቱ ችግር በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አስከፊ ደረጃ ላይ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ ሴቶች ለወር አበባ መጠበቂያ የሚገለገሉት አብዛኛውን ጊዜ የተቀደዱ አሮጌ አልባሳትን በመስፋት፣ እንዲሁም በሌሎች ጤንነታቸው ባልተጠበቁ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ሁኔታ በመነሳት በወር አበባ ንጽሕና አጠባበቅ ዙሪያ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲደረግና የወር አበባ ጤናና ሥነ ንጽሕና ምርቶችን ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

የጤና ሚኒስቴር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ ከወር አበባ ጋር ተያይዞ ያለውን የጤና ችግር የመከላከልና ብሎም የማስቀረት፣ እንዲሁም በትምህርት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚታየውን የተዛባ አመለካከት የመቀየርና የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር በአገር አቀፍ ደረጃ እያከናወነ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ አሁንም ድረስ ሴቶች በወር አበባ ጊዜያቸው ከማኅበረሰቡ ጋር እንዳይቀላቀሉ፣ አብረው እንዳይበሉና እንዳይታዩ፣ ምግብና ውኃ እንዳያቀርቡ ገደብ ሲጣልባቸው ይስተዋላል፡፡ በትምህርት ተቋማት፣ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች፣ በማረሚያ ቤቶችና በመጠለያ ጣቢያዎች የውኃና የሳሙና አቅርቦትና የሳኒቴሽን (የአካባቢ ንጽሕና) አገልግሎት አለመኖር ወጣት ልጃገረዶችና ሴቶችን ለመገለል፣ ለጭንቀትና ለሥነ ልቦና ተፅዕኖ እንደዳረጓቸውም አመልክተዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር የተዛባ አመለካከትን ለማስቀረት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ግንዛቤ ማስጨበጫን እየሠራ ይገኛል ያሉት ደረጀ (ዶ/ር)፣ ሴት ተማሪዎች እንዴት ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ባለማወቅ ምክንያት ለሥነ ልቦና ጉዳት ብሎም ለጤና ችግር እየተዳረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የወር አበባ ጤናና ሥነ ንጽሕና መመርያን በ2009 ዓ.ም. አውጥቶ ወደ ሥራ ያስገባ ቢሆንም፣ በአተገባበር ግን አሁንም ድረስ ብዙ የሚቀር ሥራ መኖሩን ሚኒስትር ደኤታው ጠቁመው፣ የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጤና ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ (ሞዴስ) ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ችግሩን እንዳጎላው በየጊዜው የሚገለጽ ነው፡፡

በዋጋ መናር ምክንያት በገጠር የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ 72 በመቶ ወጣት ሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ምርቶችን እንደማያገኙ የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ጥምረት የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያጠናው ጥናት ያሳያል፡፡

ተማሪዎች በመደበኛ የትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ ከሚያደርጉዋቸው መሠረታዊ ምክንያቶች መካከል ደግሞ የሴቶች የወር አበባ የንጽሕና መጠበቂያ (ሞዴስ) እጥረት አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

ዩኒሴፍ ከዚህ በፊት ባወጣው ሪፖርት፣ በአፍሪካ ከአሥር ልጃገረዶች አንዳቸው በወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ዕጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንደሚቀሩ ጠቁሟል፡፡

ለችግሩ መከሰት እንደ ምክንያት ካነሳቸው ውስጥም የመንግሥት ትኩረት ማነስ፣ ቋሚ በጀት ያለመኖርና የለጋሽ አካላት ቁጥር መቀነስ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በኢትዮጵያም ችግሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ችግሩ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በሚማሩ ሴት ተማሪዎች ላይ ጎልቶ ይታይ እንጂ በከተማም ይስተዋላል፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ በ2014 ዓ.ም.  በመዲናዋ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ አስጠናሁት ባለው የዳሰሳ ጥናት፣ ችግሩ በገጠርና በከተማ ባሉ ትምህርት ቤቶች በስፋት እንደሚስተዋል አመላክቷል፡፡

በጥናቱ መሠረትም፣ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች 54 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ወቅት በሚከሰት የንፅህና መጠበቂያ እጥረት ምክንያት በመደበኛ የትምህርት ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ ማረጋገጡን ከወራት በፊት አንስቶ ነበር፡፡

በዚህም ቢሮው ለገንዘብ ሚኒስቴር ለዘጠኝ ወራት ያህል ባደረገው ውትወታ ጉዳዩ በአዋጅ ተደንግጎ በምገባ ኤጀንሲው በኩል ተካቶ ለተማሪዎች እንዲቀርብ፣ ከውጭ ለሚያስገቡ ነጋዴዎች ከ30 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ወደ አሥር በመቶ በመቀነስ ማስገባት እንደሚችሉና ከተጨማሪ ታክስ ደግሞ ነፃ እንዲሆን መደረጉንም  ቢሮው ከዚህ ቀደም  ተናግሮ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የታክሱ ጉዳይ አሁንም ስላለመተግበሩ የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያዎች ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡ ለማድረግ የጤና ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...