- እኔ ብቻ ይሆን ግን እንዲህ የምሆነው?
- ምን ሆንሽ?
- ግርም፣ ብግን የሚያረገኝ?
- ምንድነው ያስገረመሽ?
- የምትሠሩት ነገር ሁሉ ግርም ይለኛል።
- እንዴት… ምን ሰምተሽ ነው?
- ውይይቱ ላይ የሚባሉት ነገሮች ናቸው?
- ምን ሲባል ሰምተሽ ነው?
- ክልሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የመደመር ትውልድ መጽሐፍ በመሸጥ 360 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቢያቅድም እስካሁን የሰበሰበው ግን 25 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ይላሉ።
- እና…?
- እናማ በቀሪዎቹ ሐምሌና ነሐሴ ወራት መጽሐፉን ለማኅበረሰቡ በስፋት በመሸጥ ያቀዱትን ገቢ እንዲሰበስቡ ከክልሉ አመራሮች ጋር ተግባብተናል ይላሉ።
- ታዲያ ይኼን ማለታቸው ምን ያስገርማል?
- የክልሉ ማኅበረሰብ አርሶ አደር መሆኑን አስቤ ነዋ?
- አርሶ አደር ቢሆንስ?
- የእርሻ ወቅት ሳያልፍ ማዳበሪያ ይቅረብልኝ ብሎ ሰላማዊ ሠልፍ ለወጣ አርሶ አደር ምን ሊቀርብለት እንደሆነ አስቤ ነዋ?
- ምን ሊቀርብለት ነው?
- የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ነዋ!
- እያሾፍሽ ነው?
- ኧረ በጭራሽ! ኧረ ሌላም ጉድ አለ። ሚኒስትሩ የሚሉትን ስማ …
- ሰማሃቸው?
- በቅጡ አልሰማሁም፣ ምን አሉ?
- ሆሆ… መቼም ዘንድሮ ጉድ ነው የምሰማው።
- ምንድነው ያሉት?
- የሐረሪ ክልል የጠቅላይ ሚኒስትሩን የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሸጦ በሚያገኘው ገቢ የሚተገብረውን ፕሮጀክት እየገለጹ ነበር።
- እኮ ምን አሉ? ፕሮጀክቱ ምንድነው?
- የመደመር ትውልድ መጽሐፍን ሸጦ በሚያገኘው ገቢ የጅብ ምገባ ትርዒትን ያለማል ነው የሚሉት።
- ታዲያ ምኑ ነው ያስገረመሽ?
- የምታቅዱት ፕሮጀክቶች ናቸዋ!
- እንዴት? ይኼ ምን ያስገርማል?
- ማኅበረሰቡ የሚቀምሰው ተቸግሮ እያማረረና የኑሮ ውድነት ትርዒት እየሠራበት መሆኑ ጠፍቶህ ነው?
- የኑሮ ውድነት ችግር መኖሩንማ መንግሥትም አልካደም።
- እሱ እኮ ነው የሚገርመኝ?
- ምኑ?
- መንግሥት የማኅበረሰቡን መሠረታዊ ችግር እያወቀ የጅብ ምገባ ትርዒት ለማበልፀግ ፕሮጀክት መንደፉ።
- ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ጠፍቶሽ ነው?
- እንዴት ሆኖ?
- ለምን አይሆንም?
- በጅብ ምገባ የሥራ ዕድል ለመፍጠር?
- አዎ!
- ቢፈጠር እንኳ የሥራ ዕድል ነው ለማለት ይቸግረኛል።
- ለምን?
- ጅብ የመመገብ የሥራ ዕድል መጨረሻው አያምርም።
- ለምን?
- መንግሥት በጀት አጠረኝ ብሎ ምግብ ማቅረቡን ያቋረጠ ቀን ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስበው።
- ምን ይፈጠራል?
- ጅብ ሁለቱንም ይቀረጥፋል።
- ሁለቱንም ማለት?
- መጋቢውንም፣ የሥራ ዕድሉንም።
- የጀመሩት ፕሮጀክቶች ፋይዳ አልገባሽም ብቻ ሳይሆን የሚገባሽ አይመስለኝም።
- እንዴት አይገባኝም?
- ቢገባሽማ እንዲህ ያሉ ማንም ሞክሯቸው የማያውቃቸውን ልዩ ሥራዎች አታጣጥይም ነበር።
- ማንም ሞክሯቸው የማያውቃቸው ነው ያልከው?
- አዎ!
- እርግጥ ነው ጅብ የመመገብ ፕሮጀክት የቀረፀ መንግሥት በአገራችንም ሆነ በዓለም መንግሥታት ታሪክ ተሰምቶ አይታወቅም።
- ፌዙን ተይውና እውነቱን ብትቀበይ ይሻላል።
- የምርህን ነው?
- አዎ።
- እስኪ ንገረኝ፣ በማንም ተሞክሮ አያውቅም የምትለው የትኛውን ሥራ ነው?
- ማዕድ ማጋራት!
- እኔ ይህ የመንግሥት ሥራ አይመስለኝም። የመንግሥት ሥራ ሀብት መፍጠርና ሀብት ማከፋፈል መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው።
- ማንም አይደፍረውም የምልሽ በዚህ ምክንያት እኮ ነው። አለ የምትይ ከሆነ ደግሞ ጥቀሺልኝ?
- በእርግጥ ማዕድ ማጋራት በሌሎች ተቋማት እንጂ በመንግሥት የተለመደ ሥራ አይደለም።
- በሌሎች ተቋማት ማለት?
- በሃይማኖት ተቋማት!