Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የከበሩ ማዕድናትን እሴት ሳይጨመርባቸው ለገበያ ማቅረብ ሊከለከል ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የከበሩ ማዕድናትን እሴት ሳይጨመርባቸው ለውጭ ገበያዎች እንዳይቀርቡ ሊከለከል መሆኑን፣ የኢትዮጵያ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ይህን ያስታወቀው ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣ ጌጦች አቅራቢዎች፣ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ምሥረታ ሲካሄድ ነው፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጉታ ለገሠ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በከበሩ ማዕድናት የበለፀገች ብትሆንም ማዕድናቱ እሴት ሳይጨመርባቸው ለገበያ ስለሚቀርቡ በየዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታጣለች፡፡

በዓለም አቀፍ ገበያ እሴት የተጨመረበት ኦፓል በኪሎ 12,000 ዶላር እንደሚሸጥ ገልጸው፣ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በጥሬው ስለምትልክ በኪሎ 6000 ዶላርና ከዚያ በታች እንደሆነና ይህም ሲሰላ ከአንድ ኪሎ ግራም ብቻ በግማሽ ያነሰ ገቢ እንደምታገኝ አስረድተዋል፡፡ 

በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ በቀላሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በግማሽ እንደምታጣ ጠቁመው፣ ይህ መስተካከል አለበት በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ ከማዕድን ሚኒስቴርና ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመነጋገር፣ እሴት ሳይጨመር የሚቀርቡ ማዕድናት ቀስ በቀስ ለማስቀረት ከስምምነት መደረሱን አስረድተዋል፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የማዕድን ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ቅርፅ የሚያስይዙ ተቋማት እንደነበሩ ገልጸው፣ እነዚህን ተቋማት ወደ ሥራ በማስገባት ለመወጣቶች ሥራ እንዲፈጥሩና የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በፖሊሲ ተደግፎ ሲሠራበት የቆየው የከበሩ ማዕድናት እሴት መጨመር ቀርቶ እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህም ምክንያት አገር ማግኘት ያለባትን ጥቅም ከማስቀረት በተጨማሪ ዘርፉ የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተውና እሴት ጨምረው ያመርቱ እንደነበር፣ ይሁን እንጂ ጥሬ ማዕድን ወይም እሴት ያልተጨመረበት መሸጥ ሲፈቀድ ሥራቸው የተስተጓጎለባቸው ወጣቶች ቁጥራቸው በርካታ መሆኑን አክለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ይህንን ችግር ለመፍታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከማድረግ በተጨማሪ፣ ዘርፉ አዋጭ አካሄድ እንዲኖረው ጥናቶችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በማዕድን ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ምርቶች እሴት ተጨምሮላቸው ለገበያ የሚቀርቡበትን ሒደት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በ2014 ዓ.ም. በማዕድን ሚኒስቴር ሥር ከተቋቋሙ ሁለት ኢንስቲትዩቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ነው፡፡

በዋናነት በማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር፣ የሰው ሀብት ልማት በማደራጀትና በፖሊሲዎች ላይ ጥናት በማድረግ ለአገር የበለጠ ገቢ ለማስገኘት የተቋቋመ ኢንስቲትዩት መሆኑን ጉታ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች