Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ በቂ የፋይናንስ ዝግጅት ቢኖረውም ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጥያቄ አለመቅረቡን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰላማዊት መንገሻና በኤልያስ ተገኝ

  • ለሁለት የሲሚንቶ ፕሮጀክቶች ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለቋል

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኢንዱስትሪዎችን በፋይናንስ ለመደገፍ የሚያስችል በቂ የፋይናንሰ ዝግጅት ቢያደርግም፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተፈለገው ልክ የብድር ጥያቄ አለማቅረባቸውን ገለጸ፡፡

ግዙፍ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የሚቀርቡ ጥያቄዎች ቁጥር ባንኩ ከገነባው የፋይናንስ አቅም አንጻር በቂ አለመሆናቸውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. የፖሊሲ ባንኩን የ2015 በጀት ዓመት ሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ተናግሩ፡፡

ዮሐንስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ባንኩ የቀረበለትን ያህል የሜጋ ፕሮጀክቶች ጥያቄ ቢያስተናግድም፣ በሚጠብቀው ልክ ግን ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኢንቨስትምንቶች የብድር ጥያቄዎች እንዳልቀረቡለት ተናግረዋል፡፡

ባንኩ አሁን ላይ ለአንድ ፕሮጀክት እስከ ስምንት ቢሊዮን ብር ፋይናንስ የማድረግ አቅም እንደፈጠረ የተነገረ ሲሆን፣ ለአብነትም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ሁለት የሲሚንቶ ፕሮጀክቶችን በድምሩ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ፋይናንስ እንዳደረገ ተመላክቷል፡፡

‹‹ብዙ ፕሮጀክቶች መምጣት ቢኖርባቸውም አልመጡም፣ ባንኩ አልሰጠም፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ እስከ 200 ቢሊዮን ማስተናገድ (ማበደር) ቢችልም፣ በበጀት ዓመቱ ያበደረው ግን በጣም ዝቅተኛ ነው፤›› ያሉት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ከዚህ ቀደም (ሪፎርም ከመደረጉ በፊት) ልማት ባንክ ፕሮጀክቶች ቀርበውለት የፍትሐዊነትና የማፅደቅ ችግር እንደነበረበት፣ አሁን ግን የመጡለትን ፕሮጀክቶች በፍትሐዊነት እንደሚያስተናግድ አስታውቀዋል፡፡ ከየትኛውም ክልል የሚቀርቡ ፕሮጀክቶች በፍትሐዊነት እየተስተናገዱ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር በተገናኘ የአገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጎት ትልቅ መሆኑን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ከ70 በመቶ በላይ የፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት እንዳለ፣ በቀጣይም በዘርፉ ኢንቨስትመንት ካልተደረገ ይህ ክፍተት ወደ 88 በመቶ እንደሚያድግ ዮሐንስ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በተለይም የአገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጎትና አቅርቦት በአጭር ዓመታት የሚሞላ ባይሆንም፣ በቀጣዮቹ ዓመታት ይህንን ከፍተት ለማቀራረብ ልማት ባንክ ዕቅዱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ልማት ባንክ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚገነቡ የሲሚንቶ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ፣ የትኞቹንም ዓይነት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልተው ወደ ልማት ባንክ መምጣት እንዳለባቸው ዮሐንስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ልማት ባንክ በራሱ በነበሩበት የአሠራር ችግሮች ምክንያት የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ የሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ጥያቄ በወቅቱ ባለመፈቀዳቸው መጓተታቸውን የገለጹት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ አሁን ላይ መንግሥት ባንኩን ከሪፎርም ጋር አያይዞ በወሰደው የማሻሻያ ዕርምጃ ሥራዎች ምላሾች ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ የተለያዩ አዳዲስ ስልቶን በመተግበር ባደረገው የአፈጻጸም መሻሻል፣ በ2013 ዓ.ም. 4.3 ቢሊዮን ብር፣ በ2014 የበጀት ዓመት 3.9 ቢሊዮን ብር እንዲሁም አምና 6.4 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ማትረፉ ተገልጿል፡፡

ባንኩ የካፒታል መጠኑን ከሦስት ዓመት በፊት ከነበረበት 2.6 ቢሊዮን ብር ወደ 38 ቢሊዮን ብር ማሳደጉንና በዚህም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 46.4 ቢሊዮን ብር ብድር ማጽደቅ መቻሉን ይፋ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም ካጸደቀው ጠቅላላ ብድር ከ19.3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ማሠራጨቱ የተብራራ ሲሆን፣ 13.5 ቢሊዮን ብር ብድር በውሉ መሠረት ለመሰብሰብ መቻሉም ተጠቅሷል፡፡

ዮሐንስ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩን ጠቅላላ ሀብት 160.8 ቢሊዮን ብር ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ አጠቃላይ ካፒታሉ 38 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኮርፖሬት አገልግሎት ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በላይ በበኩላቸው ባንኩ ባካሄደው ሪፎርም የዲስትሪክቶችን ቁጥር ከ12 ወደ 24፣ የቅርንጫፎችን ቁጥር ከ78 ወደ 100 ማሳደጉንና በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን እንዳስቻለው አስገንዝበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች