Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦክሎክ ሞተርስ በዓመት 15 ሺሕ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም ፈጥሮ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓመት 15,000 ሺሕ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ የመገጣጠም አቅም በመገንባት ወደ ምርት ሥራ መግባቱን ኦክሎክ ሞተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስታወቀ።

ኩባንያው የተበተኑ የተለያዩ ሞዴል ተሽከርካሪዎችን ከውጭ በማስገባት በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ባስገነባው ማምረቻ ውስጥ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም መጀመሩን ገልጿል።

የኩባንያው መሥራችና የቦርድ አባል አቶ አህመድ መሐመድ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት 200 የተገጣጠሙ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ማጠናቀቁንና፣ ከውጭ ያስገባቸው የተበትኑ የተሽከርካሪ ክፍሎች ሞጆ ደርሰዋል። ከውጭ ወደ አገር የገቡት የተሽከርካሪ ክፍሎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመገጣጠም 300 ተሽከርካሪዎችን ለገበያ እንደሚያቀርብም ገልጸዋል።

ኩባንያው በቀጣይ 15,000 ሺሕ መኪናዎችን በዓመት ለመገጣጠም ውጥን ይዞ ለዚህ የሚሆን አቅም መገንባቱን የገለጹት አቶ አህመድ፣ ለዚህም ቃሊቲ አካባቢ 6000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መገጣጠሚያ ማዕከል ተገንብቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ተሽከርካሪዎችን ከመገጣጠም በተጨማሪ ከተሽከርካሪዎች ጋር የተያያዙ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ ለመሥራት ከሁለት የውጪ አገር የመኪና አቅራቢዎች ጋር ስምምነት ማደረጉንም ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎችም ጄቱርና ዌሊንግ ሞተርስ መሆናቸውን አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ወኪል የሌላቸው በመሆኑ በኩባንያዎቹ የሚመረቱ ተሽከርካሪዎችን የገዙ ባለንብረቶች በመለዋወጫ እጥረት መቸገራቸውን የገለጹት አቶ አህመድ፣ ይህንን ችግር ለመፍታት ኦክሎክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከተጠቀሱት ድርጅቶች ጋር መስማማቱን ተናግረዋል። 

በስምምነቱ መሠረት ኦክሎክ ሞተርስ በአገር ውስጥ የሚገኙ የጄቱርና ዌሊንግ ሞተርስ ተሽከርካሪዎች እክል ሲገጥማቸው የጥገና አገልግሎትና መለዋወጫዎችን የማቅረብ አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ በቀጣይ ደግሞ በሁለቱ ኩባንያዎች የሚመረቱ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ ለመገጣጠም ስምምነት መድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በገፍ እየገባ ያለው የኤሌክትሪክ መኪናዎች መለዋወጫና የሰርቪስ (ጋራዥ) እንዲኖራቸው ብዙዎች እንደሚቸገሩ አስረድተው፣ እነዚህን ተሽከርካሪዎች ጥገና ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ማስገባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ማኗል መኪናዎችን ወደ አውቶማቲክ የሚቀይሩ ቴክኖሎጂዎች ማስመጣታቸውን፣ ይህም ሥራ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎቱን ለማቅረብ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው በአውቶሞቲቭ ዘርፍ የ18 ዓመታት ልምድ ያካበተ ሲሆን አስከ ቅርብ ዓመታት ድረስም ፒካፖችን፣ ሚኒባሶችንና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ለገበያ ሲያቀርብ የቆየ ነው። በተጨማሪም፣ በ2006 ዓ.ም. ‹‹አባንዛ›› የተሰኘ ተሽከርካሪ በማስመጣት ለታክሲ አገልግሎት እንዲውል ማድረጉም ይታወስል፡፡

ቅዳሜ ሐምሌ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ዊልንግ ሞተርስና ጄቱር ከተሰኙ የመኪና አምራቾች ጋር ስምምነት ከማድረግ በተጨማሪ ያስገነባውን ፋብሪካ አስመርቋል።

ስምምነቱ ተሽከርካሪዎች በከፊል አገር ውስጥ ከመገጣጠም በተጨማሪ፣ የመለዋወጫና የጥገና አገልግሎቶችን ማቅረብ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ኦክሎክ ሞተርስ ከዚህ ቀደም ለታክሲ ማኅበራት የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ሲያቀርብ የቆየ ድርጅት መሆኑ ይታወሳል፡፡

ኩባንያው ከአሁን በኋላም ከታክሲ ማኅበራት ጋር በመስማማት ተሽከርካሪዎችን ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለው አቶ አህመድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች