Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ ‹‹የወደፊት የግብይት ሥርዓትን›› በጀመረ በሁለት ወራት ውስጥ የ285 ሚሊዮን ብር ምርት አገበያየ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የምርት ገበያ በቅርቡ በጀመረው ‹‹የወደፊት የግብይት ሥርዓት›› አማካይነት ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ከ4,400 ሜትሪክ ቶን በላይ የተለያዩ ምርቶቹን ማገበያየቱን አስታወቀ፡፡ በ2015 በጀት ዓመት ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያየቱንም ገልጿል፡፡

ከኢትዮጵያ የምርት ገበያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ተገበያዮቹ በራሳቸው መንገድ ተዋውለው ግብይት መፈጸም የሚያስችላቸው የወደፊት ግብይት ከተጀመረ ገና  ሁለት ወራትን ቢያስቆጥርም በርካታ ተገበያዮች እየተስተናገዱበት ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ነፃነት አበበ ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ በወደፊት ግብይት ተገበያዮች በየራሳቸው እየተዋዋሉ ግብይት እየፈጸሙ ሲሆን፣ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ከ4,400 ሜትሪክ ቶን በላይ ተገበያዮች በዚህ የግብይት ሥርዓት መጠቀማቸው ፍላጎቱ ከፍ እያለ መሆኑን ያሳያል፡፡ 

ባለፉት ሁለት ወራት በወደፊት ግብይት የተገበያዩት ምርቶች ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ነፃነት፣ በዚህ ግብይት ሥርዓት ከተገበያዩ ምርቶች መካከል አረንጓዴ ማሾና የተለያዩ የቦሎቄ ዓይነቶች ሲሆኑ እነዚህ ምርቶች 54 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በገንዘብ መጠን ደግሞ ከፍተኛ ድርሻ የያዘው ቡና መሆኑ ታውቋል፡፡ እንደ አቶ ነፃነት ገለጻ ከአረንጓዴ ማሾና ከቦሎቄ ሌላ ቡናና ሰሊጥም በወደፊት ግብይት ሥርዓቱ ግብይት የተፈጸመባቸው ቢሆንም፣ ቡና በምርት መጠን አነስተኛ ሆኖ በገንዘብ መጠኑ ከፍ ያለ ግብይት ሊፈጸምበት የቻለው ከሌሎቹ ምርቶች ከፍ ያለ ዋጋ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የግብይት ሥርዓት በተለይ የወጪ ንግድ ውሎች በቶሎ እንዲፈጸሙ ከማስቻሉም በላይ፣ ተገበያዮች በሚፈልጉት መንገድ ግብይትን እንዲፈጽሙ እያስቻላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

የምርት ገበያውን የ2015 የበጀት ዓመት ክንውንን በማስመልከት አቶ ነፃነት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 257 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ምርቶችን አገበያይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተገበያዩት ምርቶች ውስጥ ቡና፣ ሰሊጥና አኩሪ አተር ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዙ ተገልጿል፡፡ 

የኢትዮጵያ የምርት ገበያ በበጀት ዓመቱ አዳዲስ ምርቶች ወደ ግብይት ሥርዓቱ ያስገባ ሲሆን፣ ይህም በምርት ገበያው የሚገበይ ምርት ቁጥር ወደ 22 ከፍ እንዲል አስችሏል፡፡ ምርት ገበያው ዘንድሮ ወደ ግብይት ሥርዓት ውስጥ ካስገባቸው ምርቶች መካከል ዕጣን፣ ግብጦ፣ ባቄላና ኮረሪማ በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን የስንዴ ግብይትንም ዳግም አስጀምሯል፡፡ 

በተለይ ዕጣን በአገር ውስጥ የጥራት መሥፈርት እንዳልነበረውና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለመጀመርያ ጊዜ ይህንን የጥራት መሥፈርት አዘጋጅቶ ዕጣን በምርት ገበያው በኩል ማገበያየት የጀመረበት ዓመት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ከዚህ ሌላ ምርቱ እየጨመረ የመጣው ስንዴ ከዚህ በፊት የምርት ኮንትራት ቢኖረውም፣ አሁን ካለው የምርት ባህሪ፣ ከምርቱ መጠን መጨመርና ከተጠቃሚዎች ፍላጎት አንፃር የምርት ኮንትራት ማሻሻያ ተደርጎበት እየተሠራበት ነው፡፡ ይህ የምርት ኮንትራት ማሻሻያ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፀድቆ በሥራ ላይ እንዲውል የተደረገ ነው፡፡   

ምርት ገበያው ሲጀመር በቆሎና ስንዴ በማገበያየት ሲሆን፣ በዚያን ወቅት ለውጭ አገር ይቀርብ የነበረ ስንዴ ብቻ በማገበያየት የተወሰነ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ነፃነት፣ አሁን ግን በአገር ውስጥ እሴት ጨምረው ለሚያቀርቡ እንደ ዱቄት ፋብሪካዎች፣ ፓስታና መኮሮኒ አምራቾች ጭምር እንዲጠቀሙ በማለት፣ ይህንን ያጠቃለለ የምርት ኮንትራት ማሻሻያ ተደርጎ ግብይቱ እየተከናወነ ነው፡፡ 

አዳዲስ ባንኮችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ከማስገባት አንፃርም በተሠራው ሥራ ወደ አምስት አዳዲስ ባንኮችን በዚህ ዓመት በማስገባት አጠቃላይ ከምርት ገበያው ጋር የሚሠሩ ባንኮችን ቁጥር 22 ማድረስ ተችሏል ተብሏል፡፡

የባንኮች ቁጥር እያደገ መሄድ ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ያስረዱት አቶ ነፃነት፣ በተለይ አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ላኪዎች የተለያዩ የባንክ ሥርዓቶችን በመጠቀም ክፍያና ርክክብ ሥርዓት እንዲጎለብትና ተደራሽነት እንዲሰፋ ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አባል ያልሆኑ ገበሬዎች፣ ላኪዎች በቀጥታ መጥተው እንዲገበያዩ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቶ ሥራ ላይ የዋለ በመሆኑ በመረጡት ባንኮች እንዲገበያዩም ዕድል ይሰጣል፡፡ ይህም ተጨማሪ ተገበያዮች ወደ ግብይት ሥርዓቱ እንዲመጡ ያደርጋል፡፡ 

በበጀት ዓመቱ የምርት ገበያው ሌላው ዋነኛ ተግባሩ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችለው የአገልግሎት አድማሱን ከማስፋት አንፃር ያከናወነው ሥራ ነው ያሉት አቶ ነፃነት፣ ምርት ገበያው ራሱ ተቀብሎ ከሚያገበያያቸው ምርቶች በተጨማሪ ለሌሎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በቀጥታ ትስስርና በኮንትራት (በውል ግብይት) በኮንትራት እርሻ የሚገበያዩ ሰዎች የመጋዘንና የጥራት ምርመራ አገልግሎት መስጠቱ በተረጋገጠ የምርት ደረጃ ግብይት እንዲካሄድ አስችሏል፡፡ በዚህ አሠራር ወደ ምርት ገበያው ቅርንጫፎች በመምጣት አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት በመዘርጋቱ በርካቶች እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት በዚህ ዓመት የተጀመረ ሲሆን፣ በዋናነት ከምርት ገበያው ውጪ ያሉ ተገበያዮች በሚኖራቸው ስምምነት መሠረት ወደ ምርት ገበያው መጥተው ይህንን አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ሥርዓቱን ወደ ተሻለ አገልግሎት ከፍ ለማድረግ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ የኦንላይን ግብይት እንደሚጀምር ገልጿል፡፡ ይህ የኦንላይን ግብይት ሒደቱን በእጅጉ ያዘምናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ እንደ አቶ ነፃነት ገለጻ፣ የግብይት አሠራር አንዴ ሥርዓት ተዘርግቶለት በዚያው የሚቀጥል ባለመሆኑ፣ አዳዲስ ሥርዓቶች እየተፈጠሩ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግን የሚጠይቅ ነው፡፡  ስለዚህ ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመናዊ አሠራር መተግበር ስለሚገባ ምርት ገበያው ወደ ኦንላይን ግብይት በመግባት አሠራሩን የሚያዘምን ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ቴክኖሎጂ የተገበያዮች መብዛት ዓለም አቀፍ ጋር ካለው የምርት ገበያዎች ዕድገት አንፃር የኦንላይን ግብይት መጀመር በማስፈልጉ ይህ አሠራር ይተገበራል፡፡ 

ይህንን ዕቅዱን በተያዘለት ጊዜ ለመጀመር ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ ለዚሁ ሥራ ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም ጋር ውል መፈራረሙን አስታውሰዋል፡፡ የኦንላይን ግብይትን ፕሮጀክት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚተገበር ሲሆን ለዚህ የሚሆነው ሶፍትዌሩ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኦንላይን ግብይት መጀመር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አሁን የሚጠቀምበትን የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ወደ ተሻለና ዘመናዊ አገልግሎት የሚያሳድግም ነው ተብሏል፡፡ ይህም እስካሁን ባለው አሠራር ተገበያዮች ወደ ምርት ገበያው የግብይት ማዕከላት  ቀርበው መገበያየታቸው ቀርቶ ካሉበት ሆነው በሞባይል በኮምፒውተራቸውና በማንኛውም የዲጂታል መሣሪያ ግብይታቸውን ማከናወን የሚችሉበት ሥርዓት እንደሚሆን አቶ ነፃነት አብራርተዋል፡፡ 

ምርት ገበያው የበለጠ ተደራሽ እንዲሆን የሚያግዝ ሲሆን፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት የበለጠ የሚያሳድግ፣ በግብይት የሚሳተፉ ሰዎችም እንዲበራከቱ የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡    

ተገበያዮች የሚፈልጓቸውን የግብይት የጥራት፣ የመጋዘንና የሌሎችም ምርት ገበያው የሚሰጣቸውን አገልግሎት በኦንላይን ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓትን የሚፈጥር መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፣ ለወጪ ንግድ ግብይትን ከማሳደግም አኳያም ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ 

በዚሁ ጉዳይ አቶ ነፃነት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ምርት ገበያው ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን በመዘርጋት እንደ ፈር ቀዳጅ የሚቆጠር ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ድምፅ የማስተጋባት የግብይት መድረክ ከተፈጠረ በኋላ ወደ ኤሌክትሮነክ የግብይት ማዕከል መሸጋገሩ ይታወሳል፡፡ በተለይ እንደ ቡና ያሉ ምርቶች የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓት ተዘጋጅቶላቸው እየተሠራበት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ኦንላይን ግብይት ሥርዓት መግባቱ ምርት ገበያው በየጊዜው አሠራሩን እያሳደገ መምጣቱን ያሳያል ተብሏል፡፡ ከዚህ ዕቅዱ ባሻገር ምርት ገበያው አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ እንዲገቡ የሚያስችሉ ሥራዎችን የሚቀጥልበት መሆኑንም አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ ዓመትም ዝግጅት ሲደረግባቸው የቆዩ አዳዲስ ምርቶች እንዲገቡ ይደረጋል፡፡

በአዲሱ ዓመት በምርት ገበያው በኩል ይገበያያሉ ተብለው ከሚጠበቁ ምርቶች መካከል የማዕድን ምርቶች በቀዳሚነት ተጠቅሷል፡፡ የማዕድን ምርቶችን በምርት ገበያው በኩል ለማገበያየት ዕቅድ ተይዞ የነበረው ቀደም ብሎ ቢሆንም፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተነሳ በመሃል መቋረጡ ተገልጿል፡፡ 

አብዛኛው የማዕድን ምርቶች ግጭቶች በነበረባቸው አካባቢዎች ያሉ በመሆኑ፣ አሁን ግን በቶሎ የሚጀመርበት ዝግጅቶች አጠናቅቀው በተለይ ለጌጣ ጌጥ የሚሆኑ የማዕድን ምርቶች ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአቶ ነፃነት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህም ሌላ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ ቢታቀፉ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈቱ የተወሰነባቸው ምርቶች ወደ ምርት ገበያው ለማስገባት በዕቅድ ተይዞ እየተሠራባቸው ነው ተብሏል፡፡ በተለይ የሲሚንቶ ምርትን በምርት ገበያው በኩል ለማገበያየት ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ሲሚንቶን በምርት ገበያው በኩል ለማገበያየት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዝግጅት እየተደረገበት ነው፡፡ ሲሚንቶን በምርት ገበያው የግብይት ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፍ መደረጉ በሲሚንቶ የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አሁናዊ ችግሮችን ሊፈታ የሚችልና የቁጥጥር ሥርዓቱንም በቀላሉ ለማሳለጥ እንደሚረዳ ታምኖበት የሚተገበር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ሌላ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ የጨው ምርቶችንና ለምግብነት የሚውል የገበታ ጨው በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያይ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችንም ለማስገባት ዕቅድ መያዙንም ለማወቅ ተችሏል፡፡  

የምርት ገበያ ሥርዓት አንድ ምርት አስገብቶ የሚቆም ባለመሆኑ፣ በርካታ ባለድርሻ አካላት እነዚህን በሚመለከት፣ ከሚመለከታቸው የክልል የፌዴራል ተቋማት ጋር እየሠሩ የሚገኙ መሆኑን የገለጹት አቶ ነፃነት፣ ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ግብይቶች በዘመናዊና በሕጋዊ ሥርዓት እንዲጓዙ የሚያስችል ይሆናል ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች