Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት በሪል ስቴት አካባቢ ያለውን እንቅስቃሴና የተጋነነ ዋጋ ሳይረፍድ ይመልከት!

በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ ትልልቅ የክልል ከተሞች ውስጥ መሠረታዊ የኅብረተሰቡ ችግሮች ተብለው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የመኖሪያ ቤት እጥረት በዋናነት ሊቀመጥ የሚችል ነው፡፡ 

የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ ነው፡፡ እያደገ ካለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት አንፃር ግን በበቂ ሁኔታ የቤት አቅርቦት ባለመኖሩ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲባባስ እያደረገ ነው፡፡ 

ፍላጎቱን የሚመጥን የቤት አቅርቦት አለመኖሩ ደግሞ የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ያቃልላሉ ተብለው የሚታሰቡ የሪል ስቴት ልማቶችም ቢሆኑ እየተጠየቀባቸው ያለው እጅግ የተጋነነ ዋጋ ብዙኃኑን የቤት ፈላጊ የሚጋብዙ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የሪል ስቴት ልማት በቅርብ ቁጥጥር የማይደረግበትና በዘፈቀደ በሚደረግ የተጋነነ ዋጋ ዛሬ ላይ በአገር ነዋሪ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል አቅምን የሚመጥን አልሆነም፡፡ እነዚህ የሪል ስቴት አልሚዎች ዋና ትኩረታቸው ዳያስፖራዎችን አድርገዋል፡፡ ሽያጫቸውንም የሚያካሂዱት በውጭ ምንዛሪ ወይም የውጭ ምንዛሪ ተመንን መሠረት አድርገው በመሆኑ አገሬውን ዘንግተውታል ማለት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የቤት ፍላጎትን በተወሰነ ደረጃ ሊቀርፉ ይችላሉ የተባሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ይፋ መደረጋቸው ቢሰማም እነዚህ ፕሮጀክቶች በተጨባጭ መሬት ላይ ባለመውረዳቸው ቤት የማግኘት ፍላጎት በእጅጉ እንዲጨምር አድርጓል፡፡

በመሆኑም በወራት ልዩነት እየተደረገ ያለው የቤት ኪራይ ጭማሪ ማቆሚያ እያጣ ነው፡፡ በተለይ የመኖሪያ ቤቶች የኪራይ ዋጋ አለመቀመጥ በተከራይና አከራይ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ሕጋዊ የሚያደርግ አሠራር አለመኖር ተከራዮች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው፡፡ ጫና ማሳደር ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን አማራጭ በማሳጣት ለማኅበራዊ ቀውስ እያደረገ ነው፡፡ 

በተለይ ተቀጣሪ ሠራኞች ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ደመወዛቸውን ለቤት ኪራይ እያዋሉ እንደሚገኙም በላይ በላዩ እየተጨመረላቸው እስከ መቼ ይቀጥላሉ? የሚለው ጉዳይ ያሳስባል፡፡ 

በአከራዮች መልካም ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተው የአከራይና ተከራይ ግንኙነት አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነም ችግሩን የበለጠ ያባብሳል፡፡

በአከራይ ውሳኔ ብቻ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ የተከራዩን ገቢ የሚያገናዝብ ያለመቻሉና ይህ አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን ተረድቶ የሕግ ማዕቀፍ የማይበጅለት ከሆነም አገር የጥቂቶች ብቻ እየሆነች ብዙኃኑን እየገፋች ትሄዳለች ብሎ መሥጋት ማጋነን አይሆንም፡፡

አብዛኛው ተጠቃሚ የደመወዝ ጭማሪ የሚናፍቅ ሆኖ ሳለ ተከራይ ግን በወራት ልዩነት የሚያደርጉት ጭማሪ የብዙ ተከራዮች ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ዜጎች በአንድ ቦታ ተረጋግተው እንዳይኖሩም እያደረገ ነው፡፡

በተከራዩበት አቅራቢያ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ላለመፈናቀል ክፈሉ የተባሉትን እየከፈሉ መሆኑ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ ያልቻለ ቅናሽ ወዳለበት አካባቢ እየተሰደደ እስከ መቼ ይቀጥላል?

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ አከራዮች የቤት ኪራይ እንዳይጨምሩ በሚል በተለያዩ ወቅቶች የሰጠው ማሳሰቢያ በትክክል አለመተግበሩም እኮ ያለንበትን ሁኔታ ያመለክታል፡፡

አስተዳደሩ ማሳሰቢያውን ያውጣ እንጂ የሚቆጣጠርበት መንገድ ስለሌለው አከራዮች እንዳሻቸው ዋጋ እንዲጨምሩ አግዟቸዋል፡፡ 

ብዙ ተከራዮችም ቤት ከመልቀቅ ‹‹በስምምነት›› ዋጋ ጨምረው ዝምታን የሚመርጡበት ምክንያት ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ነው፡፡

እንዲህ ያለው ሁኔታ ከአስተዳደሩ የሚሰወር ባይሆንም ወቅት እየጠበቀ ለዚህን ያህል ጊዜ የቤት ኪራይ መጨመር አይቻልም የሚለው ማሳሰቢያው ቀጥሏል፡፡ ሰሞኑን ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ 

በእነዚህ ማሳሰቢያዎች ግን እየሠሩ አይደለም፡፡ ማሳሰቢያዎቹ በተነገሩ ማግሥት ስንቶች ዋጋ እንደተጨመረባቸው የደረሰብን እናውቃለን፡፡ 

አስተዳደሩ እንዲህ ያለውን ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ከማስተላለፉ ይልቅ ሁሉንም ወገን የሚያስማማ ተከራይና አከራይ ሕጋዊ የሆነ ስምምነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ሕግ ቢተገበር በተሻለ ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ የሚያስችል ፕሮጀክቶችን ከመቅረፅ ባለፈ የተከራይ አከራይ ሕግን ማውጣት የቤቶች ዋጋን እንደየአካባቢው ሁኔታ በመታመን የኪራይ ዋጋ ጣሪያ ማስቀመጥ የግድ የሚል ነው፡፡

የሚያሳዝነው ግን ከዓመታት በፊት የተከራይና አከራይ ውለታን ሕጋዊ ማዕቀፍ ለማስያዝና በዘፈቀደ የሚደረግን የቤት ኪራይ ዋጋን ለመቆጣጠር የተሰናዳ ረቂቅ ሕግ ፓርላማ ገብቶ ቀርቷል መባሉ ነው፡፡ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ስለዚህ ረቂቅ ሕግ የሚናገር የለም፡፡ አስፈላጊነቱ ታምኖ የተረቀቀው ሕግ ፀድቆ ቢሆን አሁን የምናየው ጫና ሊቀንስ ይችል እንደነበር ነው፡፡ 

እንደዚህ ረቂቅ ሕግ ሁሉ በሪል ስቴት አካባቢ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍና በዘፈቀደ እየወጣ ያለውን ዋጋ ለመቆጣጠር ታስቦ ተዘጋጅቶ የነበረው ረቂቅም በተመሳሳይ የውኃ ሽታ ሆኗል፡፡

ይህም በመሆኑ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሪል ስቴት የሚለሙ አፓርታማዎች በካሬ ሜትር እስከ 300 እና 400 ሺሕ ብር ዋጋ እየተጠየቀባቸው ነው፡፡ ከዚያም በላይ የሚጠይቁ አሉ መባሉ ያስገርማል፡፡ የትርፍ ምጣኔያቸው ከየትኛውም ቢዝነስ በላይ እየሆነ መምጣቱ በግልጽ እየታወቀ እንዲህ ያሉ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች የመገበያያ ዋጋቸው ልቅ መሆን የመኖሪያ ቤት እጥረትን እንዳባባሰና ዜጎች በአቅማቸው ቤት ገዝተው እንዳይኖሩ እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡ አሁን አሁንማ በሪል ስቴት ልማት የሚገኘው ዳጎስ ያለ ገቢ ያስጎመዣቸው ለሌላ ቢዝነስ የገነቡትን ሕንፃ ወደ ሪል ስቴት ልማት እየቀየሩ ነው፡፡ በትናንሽ ቦታዎች ሕንፃ በመገንባት አፓርትመንት የሚሸጡ የመበራከታቸው ምክንያት ዘርፉ ያልተገባ ጥቅም የሚያገኝበት በመሆኑ ነው፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት ለመገንባት የሚቻልበትንም መንገድ እያዘጋጀ ነው፡፡ 

በሪል ስቴት አካበቢ ያለው ችግር ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ጊዜ እናስረክባለን ብለው ከደንበኞች ቅድሚያ ክፍያ ተቀብለው ለማስረከብ ወገቤን የሚሉ አልሚዎች መበራከትም በዘርፉ የሚታይ ትልቅ ችግር ነው፡፡ በራሳቸው ግድፈት በወቅቱ ማስረከብ ስላልቻሉ ቤት ተጨማሪ ክፍያ እየጠየቁ የቤት ዋጋን እያናሩ ነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ትክክለኛ የቤት ፈላጊ በተወደደም ዋጋ ቢሆን ቤት ለማግኘት የሚቸገሩበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ይህም አንዳንዶች አራትና አምስት ቤት ከሪል ስቴት ገዝተው ቤቱ ሳይጠናቀቅም ሆነ ከተጠናቀቀ በኋላ በደላሎች አካማይነት በትርፍ እየሸጡ መሆኑም ለቤት ዋጋ መናር እንደ ምክንያት እየተጠቀሰ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ይፈታል የተባለው የሪል ስቴት ረቂቅ ሕጉም ሆነ የአከራይ ተከራይን የሚመለከተው ረቂቅ በቶሎ ሊወጣ ይገባል የምንለው ችግሩ ከተባባሰ በኋላ መፍትሔ ለማፈላለግ መሞከር ውጤት አያመጣም ብለን ስለምንሠጋ ነው፡፡ 

እንዲህ ያሉ ሕጎች ቀድሞም ቢሆን የታሰቡት አሠራሮችን ሕጋዊ ለማድረግና ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን ለመከላከል በመሆኑ ጊዜ ሊሰጣቸው አይገቡም፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት በእጅጉ ከማስፈለጋቸው አንፃር የሚመለከታቸው አካላት ረቂቆቹ ከሸሸጉበት አውጥተው ያፅድቁልን፡፡

የመኖሪያ ቤት ችግርን ከመቅረፍ አንፃር ዘላቂ መፍትሔዎች ያሻሉ፡፡ ለምሳሌ የቤት ግንባታዎችን የሚያበራክቱ አሠራሮችን መዘርጋት ለትክክለኛ ገንቢዎች መሬት ማቅረብ በአግባቡ ግንባታዎቹ መካሄዳቸውን መከታተል ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት