Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባለህበት እርገጥ!

ሰላም! ሰላም! ሰላማችሁ ይብዛ! የክረምቱ ወራት ገስግሰው እዚህ ደርሰን መቼም ለእናንተ የምደብቃችሁ ነገር የለም። ሰሞኑን እጆቼን አጣምሬ ስለትናንቱና ዛሬው እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሳስብ ነበር። ቀስ በቀስ ብዙ ዕንቁላሎች በእግራቸው ከመሄድ አልፈው በአናታቸው ቆመው እያየሁ፣ ስለዝግመት ለውጥ ለማወቅ ብቻ በትምህርቴ ገፍቼ ቢሆን ኖሮ እያልኩ አንድ ጊዜ ራሴን ረገምኩ። ሁለተኛ ልደግም ስል ግን ማንጠግቦሽ ሰምታኝ ኖሮ፣ ‹‹አንተ ሰውዬ እንኳን ተምረህ ደልለህም የዋጋ ንረቱን አልቻልከው?›› ብላ ተቆጣችኝ። ‹እውነቷን ነው› ብዬ ይኼው ሳምንቱን ሙሉ ለንሰሐ ማልጄ እየተነሳሁ መደዳውን ሳስቀድስ ሰነበትኩ። ዳሩ አስቀድሰን ስንመለስ ዓለም ጥምጣሟን ቀይራ ትጠብቀናለች። እንዲያውም አንድ ቀን አዛውንቱ ባሻዬ ከታወቀ ደብር ጠበል እንዳስመጡ ሰማሁ። ድንገት በኑሮ ጫና ምክንያት በተስተጓጎለው ቀልቤ ሰበብ ደጀ ሰላም መሳሙን ብዘነጋ እንኳ ብዬ በጄሪካን ቀንሼ አመጣሁና ቤት አስቀመጥኩት። ጠርጥር አትሉም ታዲያ!

እንደ ፈራሁት ከትናንት በስትያ ያሻሻጥኩት ቪላ ቤት አወዛግቦኝ ማልጄ ስነሳ፣ ባይሆን አንድ ኒኬል ፀበል ጠጥቼ ለመውጣት ጄሪካኑን ስፈልገው አጣሁት። ‹‹የት ሄደ?›› ብዬ ከእነ ምልክቱ ማንጠግቦሽን ብጠይቅ፣ ‹‹ይኼን ሁለት ቀን ምግብ ተሠርቶበት በላኸው እኮ። ባይሆን ለሌላም ግዜ ውኃ ስትሄድ እንዳልቸገር ጄሪካን በርከት አድርገን ገዝተን ማስቀመጥ አለብን…›› አለችኝ። ጉድ እኮ ነው ፀበል መሆኑን ልነግራት አልፈለግኩም። ነግሬያት ደግሞ ሁለታችንም ለንሰሐ ስንሯሯጥ ጉልቻችን ይፍረስ? አይታወቅማ። አብዝቶ ምሕረት የሚለምን ሰው ሕይወት እንደምን እየጣፈጠችው ትሄዳለች? ከልቤ እኮ ነው። ደላላነቴ ቀርቶብኝ ስለዳርዊን የዝግመቱ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ በጨረፍታ የሰማሁትን በደንብ በተማርኩ ኖሮ ብዬ በማሰቤ የጀመርኩት የፀፀት ጉዞ ደግሞ ሌላ ፀፀት ላይ ሲጥለኝ፣ ‹‹ሰው ማለት በፀፀት ላይ የሚያጠነጥን አዝጋሚ ፍጡር ነው…›› ብዬ የራሴን ‹ቲዮሪ› ደመደምኩላችሁ። ምናለበት ሐሳብ እንደ መደምደም ፍጥነታችን የተቦረቦሩ መንገዶችን ሞልተን የሀብት ጉዞ ላይ ‹ፋስት› ብንሆን ነው የምላችሁ፡፡ አነቃቂ ልሁን መሰል!

እስካሁን ያልጠየቃችሁኝ ጥያቄ እኔ ራሴ ላንሳውና ጨዋታችንን እንቀጥል። ‹ብሎ ብሎ ደግሞ ለምን የዳርዊን ‹ቲዮሪ› ላይ ወሰደህ?› በሉኝ። የወሰደኝማ የዝግመት መጨረሻው ጭራቅነት ነው እንዴ? የሚል ሌላ ጥያቄ ነው። ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ይኼን የልቤን ጥያቄ ሳነሳበት አፌን በእጁ አፈነው። ዘመናዊ አነቃቂዎች ቢሰሙኝ መቼም አያምኑኝም። እንዴት? ‹የለም እሱ አያፍንህም። መንግሥት ነው ያፈነህ› ነዋ የሚሉኝ። አንዱ ባለፈው በረደኝ ብሎ በደንብ ያልተቀጣጠለ ከሰል ለመሞቅ መኝታ ቤቱ አስገብቶ ታፍኖ ሞተ። አስከሬኑ ተመረመረ። በጭስ ታፍኖ መሞቱ ለወዳጅ ዘመድና ለሠፈርተኛው ሳይቀር ተነገረ። ሐኪሞቹን ግን የሚያምናቸው ጠፋ። ታዲያ ከአነቃቂዎቹ መካከል አንዱ፣ ‹‹ችግሩ ከከሰሉ ሳይሆን ከሰውዬው አጠቃቀም ስለሆነ፣ ከዚህ በኋላ ከሰል ስታያይዙ ‹በሎው ኦፍ አትራክሽን› መሠረት መሆን አለበት…›› እያለ ምስኪን አዳማጮቹን አወዛገበ ተባለ። ይህንን ጉድ የሰማች አንዲት ብልጥ፣ ‹‹ከእንዳንተ ዓይነቱ አንቂ አንድ ሲኒ ቡና የበለጠ ያነቃል…›› ብላ አሾፈችበት መባሉን ሰማሁ፡፡ ግሩም ሐሳብ ነው!

በቀደም ዕለት አንዱ በስልኩ ሬዲዮ እያዳመጠ ሳለ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ እኛም ደላላ ወዳጆቹ ከቀልዱ ጠበል እንዲደርሰን ድምፁን ከፍ አድርገው አልነው፡፡ ‹‹ወንድሞቼ ሰውዬው ወይ አብዷል ወይም በሰው እየቀለደ መሆን አለበት፡፡ ገንዘብ የምትፈልጉ ከሆነ ዘወትር ስለገንዘብ ብቻ አስቡ፣ ከዚያ በራሱ ጊዜ ሰተት ብሎ ይመጣል እያለ እያጃጃለን እኮ ነው ሳቄ የመጣው….›› ሲለን ለጊዜው ግራ ብንጋባም ሙሉ ሐሳቡን ስናዳምጥ የዝንፈቱ መነሻ ገባን። አንድ ጊዜ በፌስቡክ አንድ ሰባኪ መሳይ አዳራሹ የሰበሰባቸውን ምስኪኖች፣ ‹‹ጌታ ስልካችሁን ያለ ቻርጀር እየሞላው ነው…›› ብሎ ከፊት የደረደራቸውን ወረበሎቹን ስልክ እያስወጣ ‹እውነት ነው… እውነት ነው…› እያሰኘ ሲያጃጅል የነበረው አይረሳኝም፡፡ ከዚያም የባንክ ደብተራቸውን ከምሮ በተዓምር የዋሆችን ሚሊዮኖችን ለማስቆጠር ናላ ሲያዞር የነበረውም እንዲሁ፡፡ ሬዲዮ ውስጥ የሰማነውም የእነዚያ ቢጤ መሆኑ ሲታወሰኝ እንደ ዕብድ መሳቅ ጀመርኩ፡፡ ነካ አደረገኝ መሰል!

ድሮ ልጆች ሆነን አባቴ የነገረኝ ተረት አሁንም ትዝ ይለኛል። ነገን በልጆቻችሁ መኖር የምትፈልጉ ወላጆች በዚህ አጋጣሚ ልብ በሉ። ልጆች በምትገዙላቸው ‹ብራንድ› ጫማዎች፣ ያለ ዕድሜያቸው ኪሳቸው ውስጥ በምታጭቁላቸው ገንዘብ፣ በምታስተምሯቸው ውድ ውድ ትምህርት ቤቶችና በልደት ገጸ በረከቶች አያስታውሷችሁም። ፕሮፌሰርም ይሁኑ አውሮፕላን አብራሪ በማስተዋልና በጥበብ አዕምሯቸው ውስጥ በምትሰንቁት ምሳሌያዊ ትምህርት ብቻ ነው የሚያመሠግኗችሁ። ለምሳሌ እኔ የአባቴን ሳስታውስ፣ ‹‹አንድ ሰውን ቀቅሎ የሚበላ ጭራቅ ነበር…›› ብሎ የነገረኝ ተረት ትዝ ይለኛል። እናም አንድ ቀን እናቷ ገበያ ጥላት የሄደች ታዳጊ ብቻዋን ቤት ውስጥ ተቀምጣ ጭራቁ ከተፍ አለባት። ወዲያው እሳት አቀጣጥሎ ገንቦ ውስጥ ከተታት። ውኃ ለመሙላት ውኃ ሊያመጣ ሲሄድ ልጅቷ ቶሎ ወጥታ ገንቦውን ድንጋይና እንቧይ ሞልታ ተደበቀች። ጭራቁ ያመጣውን ውኃ በገንቦው ሞልቶ እሳቱን እየቆሰቆሰ ተቀመጠ። ተቀምጦ ገንቦው ውስጥ ያለው እንቧይ ‹ጧ!› ሲል ‹ዓይኗ ፈነዳ› ይላል። ‹ጧ!› ሲል ‹ጉንጯ ፈነዳ› ሲል መጨረሻ ላይ ገንቦው ራሱ ፈነዳና ጭራቁን ገደለው። በቆፈሩት ጉድጓድ መቀበር ይመጣል ነው ነገሩ። የዘንድሮ ወፍ ዘራሽ አነቃቂዎችና አጉል ሰባኪዎች ከዚህ ተረት ምን ይማሩ ይሆን፡፡ እንጃ ነው መልሱ!

 በነገራችን ላይ አንድ ጥሩ ይዞታ ላይ የነበረ ሲኖትራክ ካጋዛሁት ደንበኛዬ ጋር እንዲሁ በወሬ በወሬ ለልጆች ተረት ስለማውራት ልምድ አንስተን ስንጫወት፣ ‹‹የአሁን ዘመን ልጆች እኮ ተበድለዋል። ከእራት በኋላ ቴሌቪዥን ማየት ይፈቀድልን ብለው መነትረክ ነው የሚያውቁት። አፍ የሚያስከፍት ተረት እንዳልሰማን፡፡ ኑሮውም ነው መሰል አፍ የሚያስከፍት ተረት ሆኖብን የልጅነት ጣዕማቸውን ወላጆች እያበላሸነው ነው…›› አልኩት። ‹‹አይ አንተ የዘንድሮ ልጅ እንኳን ለተረት መቼ ለወተት ይመቻል? አጥንት ብቻ እኮ ነው…›› አለኝ። ‹ምንድነው የሚለኝ? በቋንቋና በምናብ ሳንበደል አድገናል ብለን ተኩራርተን ሳንጨርስ በአማርኛ ላንግባባ ነው?› ብዬ ስደነግጥ ቀጠለ። ‹‹ይኼውልህ እኔ የአምስት ዓመት ልጅ አለኝ። አንድ ቀን አጠገቤ ተቀምጦ የሆነ ነገር እየጎረጎረ አስነጠሰው። ‹ዕደግ› እንደማለት ‹ይማርህ› ማለት። መውለዴን ብቻ እንጂ ስለልጅ አስተዳደግ ያልተማሩትን ወላጆቼን ያህል እንዳላሰብኩበት ያወቅኩት ያኔ ነው፣ ያዘኛ። ‹ማን ነው የሚምረኝ?› ብሎ ጀመረ። አንዴ ስቻለሁና ‹ፈጣሪ!› ብዬ መለስኩለት። ‹ምን አጥፍቼ ነው የሚምረኝ?› አለኝ። ብዙ ላስረዳው ሞከርኩ። ስላልተዋጠለት አንድ ጥያቄ ብቻ ጠየቀኝ። ‹አልምርህም ቢለኝ ዝም ትለዋለህ?› አለኝ። ‹ፈጣሪ መሐሪ ስለሆነ እንቢ አይልም› ስለው፣ ‹እንቢ ካላለ ታዲያ መጀመሪያም ጥፋት የሚባል የለም ማለት ነዋ› ብሎ ተነስቶ ሄደ። ይኼውልህ የዛሬ ልጅ…›› ብሎ ያጫወተኝ ትዝ ይለኛል። እንዴት ይረሳል!

እኛም እንዲህ ነበርን ወይስ እንጀራ እንጀራ ስንል ‹ሎጂክ› ተነነብን? ምን ያልተነነብን ነገር አለ ዘንድሮ ብዬ እኮ ነው? የማዳበሪያው ትውልድ ነገር ከተነሳ ራሱን በራሱ ማንበብና መጻፍ ያስተማረ ጩጬ ያለውን ልመርቅላችሁ። አንድም በልማትና በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተባባሪ በመሆን፣ አንድም በፈጣን አላቂ ዕቃዎቻቸው የወረሩንን ሰዎች ዕቃዎች እያነሳ ጽሑፋቸውን ያነባል። ሲያነብ ‹ሜድ ኢን ቻይና› ነው። ቢል ያው ‹ቻይና› ነው። እና ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹እኔንም የሠራኝ ቻይና ነው እንዴ?›› ጉድ እኮ ነው ይቀራል ብለህ ነው ትንሽ ከቆየን? ማሙሽ ይቀራል? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የዘመኑ ትምህርት ጥራት የደረሰበትን አሳዛኝ ደረጃ ከነገረኝ በኋላ ይህንን ቀልድ አከለበት፡፡ ‹‹አንዱ ከአንድ ስም አይጠሬ ዩኒቨርሲቲ ተብዬ በአካውንቲንግ ተመርቆ ባንክ ሊቀጠር ይሄዳል፡፡ የቃል ፈተና ላይ ደርሶ ሦስቱን የወለድ ዓይነቶች ግለጽ ሲባል ውኃ ወለድ፣ አየር ወለድ፣ አቡ ወለድ አለ…›› ሲለኝ ትን ብሎኝ ልሞት ነበር፡፡ ፈጣሪ ነው ያተረፈኝ!

በሉ እንሰነባበት። ያሻሻጥኩት ሲኖትራክ ኮሚሽን አካውንቴ ውስጥ አስገብቼ አመሻሽ ላይ ባሻዬ ደወሉልኝ። የማርያም አራስ ሊጠይቁ ያለ እኔ አልሆንላቸው ብሎ ነበር የደወሉልኝ። ተያይዘን አራስ ጥየቃ። ሳያት የት እንደማውቃት ጠፋኝ እንጂ መልኳ አዲስ አልሆነብኝም። ባሻዬን ጠጋ ብዬ ‹‹መቼ አገባች? አልሰማሁም ማግባቷን?›› አልኳቸው። ባሻዬ ደንግጠው፣ ‹‹ኧረ እባክህ ስለፈጠረህ ዝም በል። እኔ የወለደ እንጠይቅ አልኩህ እንጂ ስለጋብቻ እናጣራ ብዬ አመጣሁህ?›› ብለው ሲቆጡኝ ነገሩ ገባኝ። የገባኝ መስዬ ባሻዬን ለመካስ፣ ‹‹እንዴት ነበር ታዲያ ምጡ? ጠናብሽ?›› ብዬ መጠየቅ። አፌ አያርፍም እኮ አንዳንዴ። ‹‹ማማጥ ድሮ ቀረ። ዕድሜ ለቀዶ ማዋለድ…›› አለች። ባሻዬን ቀና ብዬ አላየሁም። ግድ ካልሆነ ባሻዬ በምንም ተዓምር በቀዶ ማዋለድ መገላገልን አይደግፉም። ስንቀለቀል መስማት የማይፈልጉትን ስላሰማኋቸው እንደሚቆጡኝ ገብቶኛል። ምኔ ሞኝ ነው ታዲያ? አውቄ የስልኬን የደውል ድምፅ ነካክቼ ተደወለልኝ ብዬ፣ ‹ማርያም ጭንሽን ታሙቀው› ብዬ ላጥ። ይሞታል ወይ አለ ዘፋኙ!

እንደወጣሁ ወዲያው ለምሁሩ ልጃቸው ደወልኩለት። የተለመደችዋ ግሮሰሪ እንድንገናኝ ተነጋገርን። ስንገናኝ የሆነውን ነገርኩት። እንደ ወትሮው በአባቱ ወግ አጥባቂነት ዘና እያለ ያጫውተኛል ስል ኮስተር ብሎ፣ ‹‹በቃ አምጦ መውለድ ተረት ሊሆን ተቃረበ ማለት ነው?›› አለኝ። ‹‹አቤት?›› አልኩት ባሻዬ የመጡ መስሎኝ ክው ብዬ፡፡ ‹‹አሳሳቢ የሆነ እክል ሊገጥም እስካልቻለ ድረስ ሰው ለምን አምጦ መውለድ እንደሚፈራ አልገባኝም። በምጥ የሚወለድ ልጅ እኮ ጤናማነቱና ጥንካሬው ሌላ ነው። እህ በአቋራጭ የመክበር፣ በአቋራጭ የመድለብ፣ በአቋራጭ የመንገሥ የዘመኑ አካሄድ ስንቱን ጤናማ ተፈጥሯዊ በረከት አበላሸው መሰለህ? ሕመም ፈርተን፣ ላብ ተፀይፈን፣ ሥራ ንቀን፣ ጎንበስ ማለት ጠልተን፣ በአጠቃላይ ከምጥ ገሸሽ ብለን ያዋጣናል? ማቆራረጥና ዝላይ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ፍራ…›› እያለ ሲናገር እኔ ደግሞ ልቤ ውስጥ የተመሰገው ሁሉንም ነገር በአቋራጭ የመፈለግ ክፉ አባዜ ነበር፡፡ ደዌ በሉት!

‹‹አንተ ከአንድም ሦስትና አራት ዲግሪዎች ያሉህ ምሁር ነህ፡፡ እንዲያው ምድረ አነቃቂና ሰባኪ ምነው የአቋራጭ ሀብት ፍለጋ ላይ ሲረባረቡ ዝም ይባላል…›› ስለው ከት ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ‹‹ወዳጄ አንበርብር ራስ ወዳድ ፖለቲከኛ ከተመቸው በአቋራጭ ሥልጣን ላይ ወጥቶ ዕድሜ ልኩን ተዘፍዝፎ ቢቀመጥበት አይጠላም፡፡ ስግብግብ ነጋዴ ዝንተ ዓለም ምስኪኑን ሕዝብ አጥንቱን እየጋጠ ሀብት ቢያጋብስ ምኞቱ ነው፡፡ የጠቀስካቸው ሰዎችም የሚታለል ካገኙ እንደ ላም ሲያልቡት ቢኖሩ ደስታቸው ነው፡፡ ትልቁ ችግር የአድራጊዎቹ ሳይሆን ድርጊቱ እንዲለመድና እንዲባባስ የምናደርገው የእኛ ስንፍና ነው፡፡ አዕምሯችንን በዕውቀት ከማበልፀግ ይልቅ ከንቱ ነገሮች ላይ ጊዜያችንን እያጠፋን የብልጦቹ መጫወቻ እንሆናለን፡፡ እነሱ እኮ ከዚህች ዓለም ጋር ዘለዓለማዊ ኮንትራት የተፈራረሙ ይመስል ለኅሊናቸውም ሆነ ለነፍሳቸው አይጨነቁም…›› ሲለኝ ነገሩ ተፍታታልኝ፡፡ ‹‹ችግሮቻችን ያሉት እዚያ ሳይሆን እዚህ እኛ ዘንድ ነው ማለት ነው…›› ስለው፣ ‹‹ወንድሜ እኛ እኮ ነገራችን ሁሉ ባለህበት እርገጥ ነው፡፡ ከዚያ ሁሉ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ወጥተን ሌላ ጦርነት ለመጀመር ስናኮበኩብ ዓለም ይታዘበናል አንLልም እኮ፡፡ ባለህበት እርገጥ…›› እያለ ተመረረ፡፡ መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት