Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገር አቋራጭ የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች በግብር አከፋፈል ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በተደረገ የግብር አከፋፈል አሠራር ለውጥ ሥራችንን ለመሥራት ተቸገርን ያሉ 13 አገር አቋራጭ የጭነት ትራንስፖርት ባለንብረቶች አክሲዮን ማኅበራት፣ ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡

የጭነት ትራንስፖርት ተሽከርካሪ ባለንብረቶቹ ዓመታዊ ግብራቸውን ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት በቁርጥ ግብር ሲከፍሉ የነበረ ሲሆን፣ በለውጡ መሠረት የቁርጥ ግብሩ ቀርቶ ተሽከርካሪዎቹ ባስገቡት ገቢ እንዲሆን ተደርጓል።

አሠራሩ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው በሥራ ባህሪው የተነሳ የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ ሕጋዊ ደረሰኝ መመዝገብና የሒሳብ መዝገብ ለማያያዝ አስቸጋሪ በመሆኑ እንደነበር፣ ማኅበራቱ ለትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን በጻፉት ደብዳቤ ቅሬታቸውን ለመንግሥት አቀርቧል፡፡

ሆኖም የተሽከርካሪዎቹ ባለንብረቶች የዓመት ገቢያቸው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በመሆኑ፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶቹ ደረሰኝ አሳትመው ገቢና ወጪን የሚያመላክት የሒሳብ መዝገብ እንዲያዙ የሚያስገድድ መመርያ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገባቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በአሥራ ሦስት ማኅበራት የተደራጁ 1,465 የጭነት ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤያቸው ባብራሩት መሠረት፣ አሽከርካሪዎቹ በየዕለቱ ሥምሪታቸው ሕጋዊ ደረሰኝ እንደማይቀርብላቸውና ሰነድ አልባ ወጪዎች ያጋጥሟቸዋል፡፡

ፌዴሬሽኑም ከማኅበራቱ ቅሬታዎቹ በዝርዝር እንደደረሱትና ለአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ፣ እንዲሁም የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በግልባጭ እንዲያውቁት በማድረግ ደብዳቤ እንደጻፈላቸው የፌዴሬሽኑ የሥራ አመራሮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይም ከገቢዎች ቢሮና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር፣ ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ለችግሩ ዕልባት ለመስጠት እንደሚወያዩ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡

ባለንብረቶቹ ለጥገና መለዋወጫዎችና ለባለሙያዎች አገልግሎት የሚፈጽሙት ክፍያ በከፍተኛ መጠን የጨመረ መሆኑንና ለዚህም ወጪ ሕጋዊ ደረሰኝ የማይገኝ እንደሆነ፣ ለተሽከርካሪዎች ጥበቃ በቀን ቢያንስ እስከ 300 ብር ያለደረሰኝ እንደሚያወጡ፣ እንዲሁም ለጭነት ሥራ የሚከፈለው የደላላ ክፍያም በተጨማሪ ደረሰኝ ከሌላቸው ወጪዎች መሀል እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

ተሽከርካሪዎች ጂቡቲ ውስጥ አደጋ ቢያጋጥማቸው ለመኪና ማንሻ ክሬን እስከ 800 ሺሕ ብር እንደሚያወጡ፣ ለጥበቃም በቀን እስከ አሥር ሺሕ ብር፣ ለፖሊስ ሪፖርት ደግሞ እስከ 50 ሺሕ ብር እንደሚያወጡ፣ እነዚህ ወጪዎችም በደረሰኝ ስለማይወራረዱ በገቢና በወጪ ሥሌት መሠረት የሚከፈል ግብር እንደማያዋጣቸው አስረድተዋል፡፡

የማኅበራቱ አባላት የ2015 በጀት ዓመት ግብር ለመክፈል በክፍላተ ከተሞች ገቢዎች ጽሕፈት ቤት በሄዱበት ወቅት፣ አንዳንድ ክፍላተ ከተሞች ለሚቀጥለው ዓመት ደረሰኝ አሳትመው የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ በግዴታ እንዳስፈረሟቸው፣ የተወሰኑት ደግሞ የሒሳብ መዝገብ ካላመጡ ግብር መክፈል እንዳይችሉ እንደነገሯቸው ለፌዴሬሽኑ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

ከማኅበራቱ አንደኛው የሆነው የደጀን አገር አቋራጭ ትራንስፖርት ማኅበር (በኋላም ወደ አክሲዮን ማኅበርነት የተቀየረ) አመራር የሆኑት አቶ ክብረት ዓለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማኅበራት ወደ ንግድ ድርጅትነት ከመቀየራቸውና የመንግሥትን ግብር ይክፈሉ ከመባሉ በፊት በራሳቸው በተበታተነ ሁኔታ ግብር ይከፍሉ የነበሩ ባለንብረቶች፣ አሁን ከማኅበሩ ጋር የኪራይ ውል ግብተው እንዲከፍሉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር ነው ብለዋል፡፡

‹‹ዘርፉ በደንብ ተደራጅቶ እንዲቀጥል የቁርጥ ግብር እንዳለ ሆኖ፣ ትራንስፖርተሩም ከማኅበሩ ጋር በኪራይ ውል ሳይሆን ኮንትራት እየወሰደ መሥራት ነው ያለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች