አገር ሰላም አጥታ ከግጭት ወደ ግጭት ስትሸጋገር ሁሌም የሚጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ በተለይ በቀላሉ ተጋላጭ የሚሆኑት ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በሲዳማና በሶማሌ ክልሎች በተፈጸሙ ጥቃቶችም ሆነ በተከናወኑ ግጭቶች የተጎዱት ንፁኃን ናቸው፡፡ በግጭትም ሆነ በጥቃት ጊዜ ከማንም በላይ ተጋላጭ የሚሆኑት ነፍሰ ጡሮች፣ አጥቢ እናቶች፣ ሕፃናት፣ አዛውንቶችና አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች በተደጋጋሚ ተጋላጭ ሆነው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በቅርቡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ጦርነት ከገጠሙ ተዋጊዎች ባልተናነሰ በርካታ ንፁኃን ሰለባ ሆነዋል፡፡ በሕይወት የተረፉትም ከደሃ ጎጆዋቸው ተፈናቅለው ለምፅዋት ጠባቂነት ከመዳረጋቸውም በላይ፣ ለመግለጽ የሚያዳግቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙባቸው በተደጋጋሚ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ አሁንም አገር ተመልሳ ወደ አውዳሚ ጦርነት ስትገባ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት፣ ንብረትና መሠረታዊ መብቶች ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ መንግሥትም ሆነ ተገዳዳሪዎች የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ያሳስባቸው፡፡
በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት የሕዝብን ደኅንነት መጠበቅ ነው፡፡ ይህ በሕግ የተሰጠው ኃላፊነት ሲሆን ተጠያቂነትም አለበት፡፡ መንግሥት ሕግ ለማስከበር የተሰጠውን ሥልጣን ሲጠቀም ከማንም በፊት ሕግ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ መሠረት ኃላፊነቱን ሲወጣ ለጭቅጭቅም ሆነ ለግጭት የሚዳርጉ ችግሮች አይፈጠሩም፡፡ የሕዝብ ሰላምም ሆነ ደኅንነት የተጠበቀ ይሆናል፡፡ ከመንግሥት በተጨማሪ ገዥው ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩልነት የሚሳተፉበት ምኅዳር ስለሚኖር፣ አላስፈላጊ ንትርኮችና ለግጭት የሚጋብዙ ድርጊቶች ቦታ አይኖራቸውም፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ጀምሮ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ ስላልሆነ፣ ልዩነትን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ ይዋጣልን ማለት ቀላሉ አማራጭ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚሸከመው በላይ መከራ እየተከመረበት ሰላማዊ ኑሮ መምራት ተስኖታል፡፡ ብስለትና ብልኃት የጎደለው የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ግንኙነት ወደ ግጭት መንደርደርን እንጂ፣ በሠለጠነ መንገድ ተነጋግሮ ልዩነትን ለማጥበብ የሚያስችል ደረጃ ላይ ሊገኝ ባለመቻሉ ሕዝብ ፍዳውን ያያል፡፡
አገርን ከገባችበት ውጥንቅጥ ውስጥ ለማውጣት የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦችን በየፈርጁ የሚያቀርቡ ትጉኃን ያሉትን ያህል፣ ለችግር ፈቺ ጉዳዮች ጀርባቸውን የሰጡና ትርምስ ላይ የሚያተኩሩ ብዙ ናቸው፡፡ አገር ለገጠማት ፈተና ነባራዊ ሁኔታዎችን በቅጡ ያገናዘበ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሰዎች ተሞክረው መፍትሔ ያላገኙ ንትርኮች ላይ ጊዜ መግደል ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ህልውናዋ አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው በሁሉም አቅጣጫዎች ሰላምና መረጋጋት ሲፈጠር ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ሰላም ለማስፈን ተቀራራቢ አቋም መኖር አለበት፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የጠመንጃ ላንቃ መዘጋት ይኖርበታል፡፡ በየቦታው ግጭት ተበራክቶ መረጋጋት ሊኖር አይችልም፡፡ ከሰላም ቀጥሎ ሕዝቡ የሚበላው ምግብ፣ ልብስ፣ የሚጠለልበት ታዛ፣ የጤና ክብካቤ፣ ትምህርት፣ ትራንስፖርትና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ማግኘት አለበት፡፡ እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ እየማቀቀ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ችግር ፈቺ መላዎችን ወዲህ በሉ እያለ ነው፡፡ በማያቋርጡ ግጭቶች ምክንያት ሰላሙ ተናግቶ በፍርኃትና በጭንቀት ውስጥ ሆኖ፣ ከተደራራቢ ቀውሶች ውስጥ የሚያወጡት መፍትሔዎች ላይ ይተኮር እያለ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ከገባችበት ችግር ውስጥ የማውጣት አቅም ያላቸው ዜጎች በአገር ውስጥም በውጭም እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አቅም ጥበብን ከብልኃት ጋር አዛምደው ሲጠቀሙበት ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ በመጀመርያ አገር ለምትባለው የጋራ ቤት ማሰብ፣ አርዓያነት ያለው ሥነ ምግባር መላበስ፣ ለዴሞክራሲ መሠረታዊ እሴቶች ዋጋ መስጠት፣ ከአድልኦ አሠራሮች በመላቀቅ ዜጎችን በእኩልነት ማስተናገድ፣ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል እውነተኛውና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ማግኛ ብቸኛ መንገድ መሆኑን ማመን፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ከልብ መሥራት፣ ከአመፃና ከውድመት ድርጊቶች መታቀብ፣ ሕዝብን ማክበርና ለፈቃዱ መታዘዝ ከተቻለ የሕዝብ መከራ ይቀንሳል፡፡ ይህ ምኞት የሚሳካው ግን በዋዛ አይደለም፡፡ በበርካታ አደናቃፊ ችግሮች የተከበበ ነው፡፡ ሆኖም ለአገር ማሰብ ከተቻለ ከፀሐይ በታች የማይቻል ነገር የለም፡፡ መሰሪነትና ሴረኝነት በተፀናወተው ፖለቲካችን ለቅንነት አንድ ስንዝር ቢገኝለት ሕዝብ ሰላም አያጣም ነበር፡፡ ቅንነት በስፋትና በጥልቀት ሲናኝ ደግሞ ሕዝባችን አንገቱን ካስደፋው ቀውስ ውስጥ በፍጥነት ይወጣል፡፡ ኢትዮጵያም ሰላሟ አስተማማኝ ይሆናል፡፡
ሰሞነኛውን የአገር ትኩሳት ማብረድ ከምንም ነገር በላይ የሚቀድም ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በብሔርም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ከአጋጠሙ ቀውሶች የባሰ አደገኛ ሥጋት ተደቅኗል፡፡ በየደረጃው ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት ተሿሚዎችም ሆኑ ሌሎች አካላት፣ በአገር ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመቀልበስ በቀና መንፈስ መነሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ያጋጠመው ችግር በአግባቡ ተፈቶ አንፃራዊ ሰላም እንዲፈጠር ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ የሚታሰብ ከሆነ፣ አገር በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል፡፡ ስለዚህ በቅንነትና በስክነት ችግሩን በመፍታት አደጋውን ማስቆም ይገባል፡፡ ለስክነት፣ ለትዕግሥት፣ ለመነጋገር፣ ለመግባባትና በጋራ አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ማሳየት ጠቃሚ ነው፡፡ ከጉዳዩ ባለቤቶች በላይ በመሆን ችግሩን አላስፈላጊ ገጽታ በማላበስ ጥላቻ የሚያስፋፉ አካላትን ወደ ጎን በማለት፣ ከዋነኞቹ የጉዳዩ ባለቤቶች ጋር መደራደርና ልዩነትን ማጥበብ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ ላይ እያንዣበበ ያለው አደጋ መላ ይፈለግለት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ሚሊዮኖችን እየፈተኑም ነው፡፡ ነገር ግን ችግሮቹ በዙ ተብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይቻልም፣ አያዋጣም፡፡ የሚያዋጣው ችግሮቹ የሚቃለሉበትንና እስከወዲያኛው የሚወገዱበትን መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ችግሮች መሀል ሆኖ ከመተከዝና ምን ይሻላል ብሎ ከመቆዘም ችግሮቹ በራሳቸው ጊዜ ይዘው የመጡትንም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል፡፡ የብዙ አገሮች ልምድ የሚያሳየው በርካታ ፈጠራዎች የተገኙት በችግሮች ምክንያት ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ችግር የፈጠራ እናት ናት›› የሚባለው፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ በፍጥነት እንድትወጣና ከሚያሰናክሏት ፈተናዎች እንድትገላገል፣ በሁሉም መስክ የተሰማሩ ልጆቿ ችግር ፈቺ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መተማመንና መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ቅራኔ የሚያስፋፉ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን ልዩነቶችን በማቀራረብ ለአገር ጥቅም ለመሥራትና ለመነጋገር ይተኮር፡፡ ከጠላትነት ይልቅ ወዳጅነትን የሚያበረታቱ ጉዳዮች ይብዙ፡፡ በጥላቻ፣ በቂም በቀል፣ በመገፋፋትና በመጠፋፋት ላይ የተመሠረቱ ትርክቶች ይወገዱ፡፡ ሕዝባችንም ሰላም አግኝቶ ዕፎይ ይበል፡፡ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ሊያሳስብ ይገባል!