Sunday, October 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየመከፋፈል ሥጋት ያጠላበት ኢኮዋስ

የመከፋፈል ሥጋት ያጠላበት ኢኮዋስ

ቀን:

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር ከሳምንት በፊት የተከናወነው መፈንቅለ መንግሥት ለቀጣናው ሥጋት ደቅኗል፡፡ በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) አባል አገሮችም ውስጥ መከፋፈልን እየፈጠረ ነው፡፡

ከ15ቱ የኢኮዋስ አባል አገሮች ውስጥ በቅርቡ በቡርኪና ፋሶና ማሊ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄዱ ሲሆን፣ በኒጀር የተደረገው ደግሞ ሦስቱ አገሮች እርስ በርስ እንዲተጋገዙ ዕድል ፈጥሯል፡፡

የፈረንሣይ ቅኝ ግዛት የነበሩት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች፣ ለፈረንሣይ የነበራቸው አመለካከት ማሽቆልቆልም ደግሞ ለኢኮዋስ ሌላው ፈተና ነው፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. በ1994 በሩዋንዳ የተፈጸመውን የእርስ በርስ ጦርነት፣ ፈረንሣይ ማስቀልበስ ስትችል ይህንን ባለማድረጓ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አልቀዋል የሚለው ግንዛቤም በማኅበረሰቡ ውስጥ መስረፁ ኢኮዋስ አንድነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል እያደረገ ነው፡፡

የመከፋፈል ሥጋት ያጠላበት ኢኮዋስ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የፈረንሣይ ቅኝ በነበረችው ኒጀር ተቃዋሚዎች የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ታይተዋል (ኤኤፍፒ)

‹‹ፈረንሣይ አትድረስብን›› የሚሉ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸው ቡርኪናፋሶ፣ ማሊና ኒጀር ይገኙበታል፡፡

ኢኮዋስ መፈንቅለ መንግሥት በተከናወነ ቁጥር በአባል አገሩ ላይ ሰላም እንዲሰፍን በመደራደርና ማዕቀብ በመጣል ሚና ሲጫወት የከረመ ቢሆንም፣ አሁን  መፈንቅለ መንግሥት የሚከናወንባቸው አገሮች እየፈረጠሙ መጥተዋል፡፡

በቅርቡ በኒጀር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ፣ ኢኮዋስ የአገሪቱ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ተፈናቃዩን ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዞምን ወደ ሥልጣን እንዲመልስ ካልሆነም ወታደራዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታውቆ ነበር፡፡

ይህን ለማድረግ እስከ እሑድ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ የጊዜ ገደብ የሰጠው ኢኮዋስ፣ ወታደራዊ ዕርምጃ ሳይወሰድ ቀርቷል፡፡

ለዚህም ወታደራዊ ዕርምጃው እንደሚኖር ሆኖም ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ቅድሚያ መስጠቱን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡

ኢኮዋስ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ያቀስቀመጠው ቀነ ገደብ ሲያልፍ ደግሞ፣ ኒጀር የአየር ክልሏን ዘግታለች፡፡

ወታደራዊ መንግሥቱም የአየር ክልሉን የዘጋው ከጎረቤት አገሮች ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን ለመመከት እነደሆነ አስታውቋል፡፡

በናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ የሚመራው ኢኮዋስ፣ በኒጀር ወታደራዊ ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑን ተከትሎ ኮትዲቯርና ሴኔጋል ሐሳቡን ደግፈዋል፡፡

ሆኖም ከአባል አገሮቹ የነበረው የፖለቲካ ድጋፍ ተመሳሳይ አልነበረም፡፡ ቤኒን ወታደር እንደማትልክ ስታስታውቅ፣ መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገዱት ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊና ኒጀር የኢኮዋስን ዕቅድ አጣጥለውታል፡፡

በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙትና ከኢኮዋስ አባልነት የታገዱት ወታደራዊ መንግሥታትም፣ ኢኮዋስ በኒጀር ላይ ዕርምጃ ከወሰደ ‹‹ጦርነት አውጇል›› ሲሉ በመግለጽ ድጋፋቸው ለኒጂር እንደሚሆን አሳውቀዋል፡፡

 በኒጀር የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ኢኮዋስን ብቻ ሳይሆን ፈረንሣይንም ፈትኗል፡፡ የቀድሞ የፈረንሣይ ቅኝ በነበረችው ኒጀር መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ፣ ፈረንሣይ በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ ያላትን ቦታ የሚያሽመደምድ ሆኗል፡፡

ሁነቱ ለፈረንሣይ ብቻ ሳይሆን አሜሪካ በአካባቢው ላላት ወታደራዊ እንቅስቃሴም ሥጋትን ያጫረ ነው፡፡

ለፈረንሣይ ታማኝ አገልጋይ የነበሩት የቀድሞው የኒጀር ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዞም፣ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደባቸው በኋላ ተቃዋሚዎች በፈረንሣይ ኤምባሲ በመገኘት ኤምባሲውን መዝጋታቸውን ኒውዮርክ ታይምስ አስፍሯል፡፡

መፈንቅለ መንግሥቱን ያከናወነው መከላከያ ኒጀር ከፈረንሣይ ጋር ያላት ትብብር ማብቃቱን አሳውቋል፡፡

ይህ በኒጀር የተከሰተው ፈረንሣይን የማግለል አካሄድ ከዚህ ቀደም በቡርኪና ፋሶና ማሊም የታየ ነበር፡፡ ሦስቱም አገሮች የፈረንሣይ ቅኝ ግዛት የነበሩ ሲሆን፣ ፈረንሣይ በየአገሮቹ ያላትን ተቀባይነት አሳጥተዋታል፡፡

ፈረንሣይ በቀጣናው ድህነትን ለመዋጋት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና አይኤስን ለመዋጋት በሚል የነበራት ሚናም ተዳክሟል፡፡

በኢዥያ ግሩፕ የአውሮፓ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሙጃታባ ራህማን እንደሚሉት፣ ፈረንሣይ የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ይመጣል ብላ አላየችም፡፡ በማሊና በቡርኪና ፋሶ ከገጠማት ተቃውሞም አልተማረችም፡፡

ፈረንሣይ ለአሥርት ዓመታት ከበርካታ የቀድሞ ቅኝ ግዛት አገሮቿ ጋር የተወሳሰበ ግንኙነት ነበራት፡፡ በአገሮቹ ወታደሮች በማሰማራት፣ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በማሳደር፣ በቀጥታ ከየአገሮቹ ፕሬዚዳንቶች ጋር በመገናኘት ፍላጎቷን ስታስጠብቅ ቆይታለች፡፡

በቁጥጥር ሥር የሚገኙት የኒጀር የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዞምም የፈረንሣይን በአጠቃላይም የምዕራባውያን ቀኝ እጅ ነበሩ፡፡ ከሌሎች በተለየም የውጭ ዕርዳታ ይጎርፍላቸው ነበር፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...