Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ተስፋ አዲስ ለካንሰር ሕሙማን ሕፃናት

የሕፃናት ካንሰርን ለመከላከልና ለማከም የሚረዳ ድጋፍ ለማድረግ በኅዳር 2005 ዓ.ም. ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ‹ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት› ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ከአራት የመንግሥት ሆስፒታሎች ጋር ማለትም ከጥቁር አንበሳ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ኮሌጅ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ጋር እየሠራ ነው፡፡ ድርጅቱ ከምሥረታው ጀምሮ ታካሚዎች ሕክምናቸውን እንዳይቋረጥ ከማደሪያ እስከ ምግብና መድኃኒት፣ እንዲሁም የሥነ ልቦና ትምህርት አልፎም የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

የካንሰር ታካሚዎች ሕፃናት በሆስፒታል ቆይታቸው ወቅት በቂ እንክብካቤ የሚያገኙበትንና በቀጣይነት ሕክምናውን እንዲከታተሉ ጥረት ያደርጋል፡፡ ወ/ሮ ሳራ ኢብራሂም የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በድርጅቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የድርጅቱን ዓላማና ዓላውንም ተግባራዊ የሚያደርግበትን አካሄድ ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ ሳራ፡- ድርጅቱ የተመሠረተው ልጆቻቸው በካንሰር ታመውባቸው በሕክምና የዳኑላቸው ወላጆች ትብብር ሲሆን፣ ወላጆቹም ሊተባበሩ የቻሉት ልጆቻቸው ከዳኑ እኛ ደግሞ ለቀሩት የካንሰር ታካሚ ሕፃናት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ከሚል ቅን መንፈስ ተነሳስተው ነው፡፡ በዚህም መሠረት ድርጅቱ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት አካባቢ ከፍ ብሎ በ2005 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡ ዓላማውም ለካንሰር ታካሚ ሕፃናት የሕክምና ጥራት በማሻሻል የሕፃናትን ሕይወት ማዳንና ወላጆቹም ለልጆቻቸው የተሻለ እንክብካቤ እንዲያደርጉ ማብቃት ነው፡፡ ዓላማውንም ተግባራዊ የሚያደርገው የሆስፒታሎችን የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ክፍልን አቅም በመገንባት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ በማስቻል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን የአቅም ግንባታ የሚከናወነው በአራት የመንግሥት ጤና ተቋማት ለሚገኙ የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ክፍሎች ነው፡፡ እነርሱም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ፣ የጥቁር አንበሳ፣ የጎንደርና የጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ሆስፒታሎች ውስጥ ያሉ የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ክፍሎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ያከናወናችሁት የአቅም ግንባታ ሥራ ምንድን ነው?

ወ/ሮ ሳራ፡- በቅርቡ ያከናወንነው የአቅም ግንባታ ሥራ አለ፡፡ የሠራነውም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ፣ በእናቶችና የሕፃናት ሕክምና ማዕከል ለሚገኘው የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ዋርድ ነው፡፡ በዋርዱ ለሚገኝ የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ክፍል ለሕክምና አስፈላጊ በሆኑ ግብዓቶች እንዲሟላና እንዲደራጅ አድርገናል፡፡ የእያንዳንዱ ክፍልና የዋርዱ ግድግዳዎች ሕፃናትን ሊማርኩ በሚችሉ ልዩ ልዩ ዓይነት ሥዕሎች እንዲዋቡ ተደርጓል፡፡ ዋርዱ ከ15 በላይ አልጋዎች የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ በእያንዳንዱም ክፍል ሁለት አልጋዎች ተዘርግተዋል፡፡ በዚህም ዋርድ ከተመደቡት የሆስፒታል ሕክምና ባለሙያዎች ባሻገር ድርጅቱ አንድ ሳይኮሎጂስትና ሌላ አንድ መረጃ የሚያጠናክር ሠራተኛ መድቧል፡፡  

ሪፖርተር፡- በአራቱም ሆስፒታሎች የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ክፍሎች ከአቅም ግንባታ ሥራ ባሻገር፣ ለታካሚ ሕፃናቱ ምን እያደረጋችሁላቸው ነው?

ወ/ሮ ሳራ፡- የማኅበራዊና የሥነ ልቦናዊ ድጋፍ ለሕፃናቱና ለወላጆች እናደርጋለን፡፡ ይህም የሚያጠቃልለው የምግብ ድጋፍ ለታካሚዎችና ለወላጆች፣ እንዲሁም ከክልል ለመጡና አቅማቸው ለማይፈቅድላቸው ታካሚዎች የትራንስፖርትና የማደሪያ አገልግሎት እናመቻችላቸዋለን፡፡ ታካሚዎች በቀላሉ የኪሞቴራፒ መድኃኒት ለማግኘት እንዲችሉ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንሠራለን፡፡ ለታካሚ ልጆች የትምህርት ቁሳቁሶችን እናሟላለን፡፡ ለወላጆች በተለያዩ ዘርፍ ሥልጠና፣ ለታካሚና ለወላጆች ደግሞ የምክር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በእያንዳንዱ ሆስፒታል የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ክፍል ያለበትን ክፍተት በመረዳት ድጋፎችን ማድረግና ማሳሰብን ያካትታል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ ለማኅበረሰባችን ትምህርትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ሥራዎቹም ትኩረት የሚያደርጉት ‹‹የሕፃናት ካንሰር ሊከሰት ይችላል፣ ግን በጊዜው ከተደረሰበትና ከታከሙ ብዙ ልጆች ሕይወታቸውን ልንታደግ እንችላለን›› በሚል መርህ መረጃን የማዳረስ ዓላማ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የድርጅቱን ዕገዛና ድጋፍ የሚሹ ሕፃናትን እንዴት ነው የምታገኟቸው?

ወ/ሮ ሳራ፡- አገልግሎት በምንሰጥባቸው ሆስፒታሎች ውስጥ ሁሉ የመደብናቸው ሳይኮሎጂስቶች አሉ፡፡ ሳይኮሎጂስቶቹ ከሐኪሞች ጋር አንድ ላይ ሆነው ያጣሩና ይልኩልናል፡፡ በተረፈ በተለያዩ ሦስት ቦታዎች ማለትም ጎንደር፣ ጅማና አዲስ አበባ ማደሪዎች አዘጋጅተናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፈንድ ከየት ነው የምታገኙት?

ወ/ሮ ሳራ፡- ዋና መሥሪያ ቤቱን በአሜሪካ ካደረገውና ‹‹ኢዚላን ፕሮጀክት› እየተባለ ከሚጠራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ፈንድ እናገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ውዳሴ የሕክምና ምርመራ ድርጅትና ሌሎችም ግለሰቦች ተገቢውን ዕገዛና ድጋፍ ያደርጉልናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ስንት የካንሰር ታካሚዎች ሕፃናትን ታድጓል?

ወ/ሮ ሳራ፡- ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ከሁለት ሺሕ በላይ የሆኑ የካንሰር ታካሚ ሕፃናትን ታድጓል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በሽታው ፀንቶባቸው ሕይወታቸው ያለፉ ይገኙባቸዋል፡፡ ካንሰር በጊዜ ከተደረሰበት የመዳን ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ማኅበረሰቡ ይህንኑ ተገንዝበውና ተስፋ ሳይቆርጡ ልጆቻቸውን ከማሳከም ወደ ኋላ ማለት እንደሌለባቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የካንሰር ታካሚ ሕፃናትን በመታደግ ዙሪያ ያጋጠማችሁ ችግር ምንድነው?

ወ/ሮ ሳራ፡- የመድኃኒት እጥረትና የዋጋ ውድነት ችግር በዋነኛነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ ሌላው ችግር ደግሞ ድርጅቱ የራሱ የሆነ ተሽከርካሪ የለውም፡፡ የድርጅቱን ድጋፍ የሚሹ የካንሰር ታካሚ ሕፃናትን የምናመላልሰው በትራንስፖርት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በአጠቃላይ የሪሶርስና የአመለካከት ችግሮችም ሳይጠቅሱ መታለፍ የሌለባቸው ናቸው፡፡ መድኃኒትን በተመለከተ መንግሥት በጤና መድን በኩል የሚያቀርበው እንዳለ ሆኖ፣ አንዳንዴ ደግሞ ከውጭ በሚገዛበት ጊዜ 45 ብር የነበረው አሁን ወደ 1,500 ብር ከፍ ብሏል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች