- ክቡር ሚኒስትር የተደረገው የዳሰሳ ጥናት የፓርቲው የሕዝብ ድጋፍ በፍጥነት እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳይ ነው።
- እኔ በዚህ ድምዳሜ አልስማማም!
- ክቡር ሚኒስትር እርሶ ባይስማሙም የተደረገው የዳሰሳ ጥናት የሚያሳየው እንደዚያ ነው።
- እኔ አሁንም አልስማም። ለጥናቱ መመዘኛ የሆነው መረጃ ትክክለኛነት ያሳስበኛል።
- እንዴት?
- የሕዝብን ድጋፍ ለመመዘን ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች የተወሰዱ አይመስለኝም። ጠቃሚ የሚባሉት መመዘኛዎች ተወስደው ቢሆን ኖሮ እዚህ ድምዳሜ ላይ ሊደረስ አይቻልም።
- ተገቢና ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች ተወስደው የተከናወነ ጥናት ስለመሆኑ በሪፖርቱ ተቀምጧል እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ አይመስለኝም። እንዳንሳሳት እሠጋለሁ።
- ክቡር ሚኒስትር ወጣቱም፣ አርሶ አደሩም፣ አርብቶ አደሩም አኩርፎናል እኮ። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ማኩረፍ ብቻ ሳይሆን ነፍጥ መዞ እየተጋጨን መሆኑ እየታወቀ እንዴት ስህተት ሊሆን ይችላል?
- ስህተት አለበት አልኩህ እኮ። ምክንያቱም የሕዝብ ድጋፍ ያለበትን ደረጃ ለመለካት ሁነኛ ናቸው የሚባሉት መመዘኛዎች ጥቅም ላይ አላዋላችሁም።
- ክቡር ሚኒስትር፣ እርሶ ሁነኛ የሚሏቸው መመዘኛዎች ምንድናቸው?
- ለምሳሌ አንዱ ማዕድ ማጋራት ነው።
- እ…?
- አዎ። የማዕድ ማጋራት ጋብዘን አልመጣም ያለ ነዋሪ አለ?
- የሚበላው የተቸገረ ሰው ግብዣ ቀርቦለት አንዴት ይቀራል ክቡር ሚኒስትር?
- ያሳተምነውን መጽሐፍ ያልገዛ የማኅበረሰብ ክፍል አለ?
- እሱን በመመዘኛነት አልተጠቀምንበትም።
- የሌማት ትሩፋትንስ በመመዘኛነት ተጠቅማችኋል?
- አልተጠቀምንም?
- ጃውሳ ናችሁ!
- ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ትርጉሙን አላውቀውም ቢሆንም ግን …
- ግን ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ጃውሳ ናችሁ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከዴሞክራሲ ሥርፀት ዳይሬክተሩ ጋር በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ነው]
- እሺ ውይይቱን ከየት እንጀምር?
- ዴሞክራሲን ለመትከል ተግዳሮት ከሆኑብን ጉዳዮች ብንጀምር መልካም ይመስለኛል ክቡር ሚኒስትር።
- ጥሩ።
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲን ለማስረፅ ከጀመርናቸው እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት መሆኑ ይታወቃል።
- ከታወቀ ለምን ትደግመዋለህ?
- ለመንደርደሪያ ያህል ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ከመንደርደር በቀጥታ ጉዳዩን ማንሳት አይሻልም?
- ጥሩ ክቡር ሚኒስትር። ተቀራርቦ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ባስቀመጥነው አቅጣጫ መሠረት አቅርበናቸዋል ብቻ ሳይሆን መቀራረባችንን የሚመጥን ስያሜ እንዲያገኙ አድርገናል።
- የምን ስያሜ?
- ተቃዋሚ የሚለውን ስያሜ በመቀየር ተፎካካሪ ብለናቸዋል።
- አሁንም መንደርደሪያ ላይ ነህ?
- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን ወደ ጉዳዩ አትገባም?
- ወደ እሱ እየመጣሁ ነው ክቡር ሚኒስትር
- እሺ ተፎካካሪ ብለን ሰየምናቸው። ምን አገኘን?
- ተፎካካሪ ብለን በመሰየም ብቻ አላቆምንም። የካቢኔ አባል ጭምር እንዲሆኑም አድርገናል።
- ጤና የለውም እንዴ ሰውዬው! ምን ልትነግረኝ ነው የፈለከው?
- ክቡር ሚኒስትር የካቢኔ አባል አድርገን፣ መኖሪያ ቤትና ቪ8 ከተቀበሉ በኋላ የሚያደርጉት ነገር ሲመዘን ግን ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።
- እንዴት?
- ወሳኝ የሚባሉ የካቢኔ አጀንዳዎች ላይ ሆነ ብለው አይገኙም። አንዳንዴ ደግሞ…
- አንዳንዴ ምን?
- አንዳንዴ ደግሞ ይገኙና አብረው የድጋፍ ድምፅ በመስጠት ይወስናሉ። ነገር ግን…
- ግን ምን?
- የካቢኔ አባል ሆነው የወሰኑበትን ጉዳይ በነጋታው በፓርቲ መግለጫ ይቃወሙታል።
- ይህማ የሚጠበቅ ነው። አንዳንዴ ዕድል ልንሰጣቸው ይገባል።
- የምን ዕድል
- እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ የመቆጠር ዕድል።