Tuesday, December 3, 2024

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ቀላሉ ሥራ ጠመንጃ ይዞ ጫካ መግባት ሆኗል›› መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ የኦፌኮ ሊቀመንበር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የዕውቆቹ ፖለቲከኞች የለማ፣ የልደቱ አያሌውና የወርቅነህ ገበየሁ መምህር ናቸው፡፡ በደርግ ዘመን የመኢሶን አባል በነበሩበት ወቅት ለሰባት ዓመታት ታስረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በስፋት ተሳትፎ ከማድረጋቸውም በላይ፣ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ህልሞች››፣ ‹‹የኢትየጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች – ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢሕአዴግ›› የሚሉ መጻሕፍቶቻቸውን ጨምሮ ሌሎች ጽሑፎችን ለአንባቢያን አድርሰዋል፡፡ መስፍን ፈለቀ ከመረራ (ፕሮፌሰር) ጋር በወቅታዊና አገራዊ ጉዳች ላይ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡እርስዎ በግልጽና በድፍረት በመተቸት ይታወቁ ነበር፡፡  አሁን  ግን  ዝምታን መርጠው  ጠፍተዋል  ለምን?

መረራ (ፕሮፌሰር):- ነገሮች በፈጣን ሁኔታ ነው የሚቀያየሩት፡፡ አገሪቱ በታሪኳ ዓይታው የማታወቀው ችግር ውስጥ ነው የገባችው፡፡ በዚህ ሁኔታ ቶሎ ቶሎ ሐሳብ መስጠት ያዳግታል፡፡ እንደ ፓርቲ የራሳችን ሥራ ለመሥራት እሞከርን ነው፡፡ በቅርቡ የማዕከላዊ ኮሜቲ ስብሰባ አድርገን የአገሪቱን ሁኔታ ገምግመን የትግላችንን አቅጣጫ አስቀምጠን ተለያይተናል፡፡ የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ እያንዳንዱን አባል ማለትም የወጣት ክንፋችንን፣ የሴቶች ሊግና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ  አስመርጠን እንደገና አደራጅተናል፡፡ ሆኖም የአገሪቱ ሁኔታና የሚዲያው ጩኸት መልክ እስኪይዝ ዝምታን መርጠን ነበር፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቧል፡፡ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን፡፡ በ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ በተመሠረተው ኮኮስም የራሳችንን ኃላፊነት እየተወጣን ነው፡፡ ጩኸቱ ሲበዛ እኛ ዝም ስንል ሰዎች የት አሉ ብለው መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ የአገሪቱ ገጽታ ሲበላሽ ስምምነትና ድርድር ተካሄደ ይባላል፡፡ ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ደርድር ተካሄደ ሲሉ እንሰማለን፡፡ ሆኖም ይህ አገሪቱን ከመገዳደር ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ እያመጣት አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በየጊዜው ሐሳብ እንዳንሰጥ አድርጎናል፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት በርካታ ታጋዮች አልቀዋል፣ የደም ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ግን ለውጡ ያው ነው ፈቀቅ ያለ ነገር የለም፡፡ ትንሽ ቀንቷቸው ወደፊት የመጡ ሌላውን የማፈን እንጂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሰፍነውን ሀቀኛ መንገድም ሆነ አሠራር አይከተሉም፡፡ ቤተ መንግሥት ከገቡ እዚሁ ለመቆየት የፈለጉትን ያደርጋሉ እንጂ፣ ለአገር ለውጥ ሲተጉ አይስተዋልም፡፡ በእርግጥ ዝምታ ጥሩ አይደለም፣ ግን በእሳት ላይ ቤንዚን ላለማርከፍከፍ ነው፡፡

ሪፖርተርጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የኦሮሞ ጥያቄ ተመልሷል፣ ውክልና አግኝቷል የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ? ካልተስማሙስ ለምን?

መረራ (ፕሮፌሰር):- በመጀመሪያ የኦሮሞ ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ ኦሮሞን መወከል ማለት እኮ የኦሮሞ ሕዝብ እንዲህ የሚባል ሰው ሊወክለኝ ይችላል ብሎ ሲመርጥ ነው፡፡ ያ የተመረጠው ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ ነፃነትና መብት አክብሮ ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ ሆኖም አሁን በኦሮሚያ ክልል ያለው ምንድነው? ኦሮሞ በታሪኩ እንዲህ ዓይነት ጦርነት ውስጥ ገብቶ አያውቅም፡፡  የደርግ ቀይ ሽብር እንኳን ኦሮሞን በዚህ ስፋትና ጥልቀት ቀውስ ውስጥ አልከተተውም ነበር፡፡ ዋናው ጉዳይ መለኪያው ምንድነው? ቋንቋ ከሆነ ንጉሥ  ኃይለ ሥላሴ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ጄኔራል ተፈሪ በንቲን ማንሳት እንችላለን፡፡ ምንድነው መለኪያው? መለኪያው አንድ ሕዝብ መብቴን፣ ጥቅሜና ነፃነቴን ያስከብርልኛል ብሎ መምረጡ ነው፣ እስካልመረጠ ድረስ አይወከልም፡፡ ስለዚህ የውክልና ጥያቄ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተመርጦ የማስተዳደርና የመምራት ጥያቄ ነው፡፡ ይህ መንግሥት ሥልጣን የያዘው በነፃና ሀቀኛ ምርጫ አይደለም፡፡ እኔ በኢትዮጵያ የተደረገውን ምርጫ ከጆሴፍ ስታሊን ጋር ነው የማመሳስለው፡፡ ጆሴፍ ስታሊን ‹‹እናንተ ምረጡ እኛ እንቆጥራለን›› ነው ያለው፡፡ አብዛኛው የአፍሪካ ምርጫ እንዲህ ነው፡፡

ሪፖርተር– በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለው ቀውስ መነሻ ምንድነው ብለው ያምናሉ? ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ወይም መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው አካል የሁሉንም  የኦሮሞ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ሐሳብ  ይዤ  ነው እየታገልኩ ያለሁት ይላል፡፡ ከእናንተ ጋር በመርህ የሚገናኝ ነገር አለው?

መረራ  (ፕሮፌሰር):- በኦሮሞ ሕዝብ የመብት ጥያቄ ላይ ልዩነት የለንም፡፡ እነሱ ምን አልባት ጫካ ስለሆኑ ጠንከር ያለ ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳድር መብትና በኦሮሞ ነፃነት ጥያቄ ላይ ልዩነት የለንም፡፡ እኛ ባዶ እጃችንን ከተማ ነው ያለነው፡፡ እነሱ ደግሞ ይኼ ያንሰናል ብለው ጫካ ገብተዋል፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ እኮ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሲነሳ ነበረ፣ ብዙ ሰው ይህንን ይረሳል፡፡ እነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሳይወለዱ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል በባሌና በሐረርጌ ነበር፡፡ ጫካም ያለው ኦሮሞ፣ ከተማምም ያለነው የመብት ትግሉን ለመቀጠል ልዩነት የለንም፡፡ ልዩነት ያለው ስትራቴጂ ላይ ነው፡፡ እነሱ ጠመንጃ አላቸው፣ እኛ ደግሞ ባዶ እጃችንን ነን፡፡ ሁሉም በአቅሙ ለትግሉ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የኦሮሞ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ አሁንም አልተመለሰም፡፡

ሪፖርተርበእርስዎ ዕይታ ኦነግ ሸኔ ወይም ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ጦር ብሎ የሚጠራው ማነው?

መረራ (ፕሮፌሰር):- የኦሮሞ ነፃ አውጭ ማለት ኦሮሞን ነፃ ለማውጣት ጫካ የገባ ኃይል ማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ይከበርልኝ ነው፡፡ ይህም ጥያቄ በመሬቱ፣ በሀብቱ፣ በቀዬው ላይ ባለቤት የመሆን ነው፡፡ ይህ ችግር አሁንም አልተፈታም፡፡ ሥልጣን የሕዝብ መሆን አለበት፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የተከፈለው መስዕዋትነት ለዚህ ነው፡፡ ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊ አገር እስካልተፈጠረች ድረስ ዘላቂ ሰላም ማምጣት አይቻልም፡፡ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ሦስት ናቸው፡፡ አንዱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት፣ ሁለተኛው ሀቀኛና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ ሦስተኛው ልማትና ብልፅግና፡፡ 

ሪፖርተርእርስዎ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሔ ብለው በተደጋጋሚ የሚያነሱት አንድ ሐሳብ አለ። ይኸውም አዲስ ማኅበራዊ ውል (ሶሻል ኮንትራት) ያስፈልጋል የሚል ነው። ይህን ሲሉ ሁሉም የተስማማበት አዲስ ሕገ መንግሥት ያስፈልጋል ማለትዎ ነው?

መረራ (ፕሮፌሰር):- ስለሕገ መንግሥቱ ጉዳይ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት ብዙ ቀውሶች የተፈጠሩት እንዴት ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ትፈጠር በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ሌሎች የሥልጣንና ተዛማጅ የቀውስ ምንጮች እንዳሉ ሆነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ እንዴት ትፈጠር ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ልትፈጠር የምትችለው ደግሞ እንዴት እንደራደር? የአገሪቱ ምርጫ በምን መሥፈርትና መንገድ ይካሄድ? ምን ዓይነት የፌዴራል ሥርዓት በአገሪቱ ይቋቋም? እንዴት ሀቀኛና ፍትሐዊ ሽግግር ይካሄድ? የሚሉትን ጥቄዎች ሁላችንም በስምምነት ስንመልሳቸው ነው፡፡

ሪፖርተር– በሁሉም ወገኖች ስምምነት ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ቢባልና እርስዎ ሁለት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳቦችን ብቻ እንዲያነሱ ዕድል ቢሰጠዎት የትኞቹን አንቀጾች እንዲሻሻሉ ያቀርባሉ?

መረራ (ፕሮፌሰር):- ሕገ መንግሥት ምንጊዜም ቢሆን ሊሻሻል ነው የተዘጋጀው፡፡ ሰው ነው የጻፈው፣ ሰው ደግሞ ፍላጎቱ ሲቀየር ይቀየራል፡፡ ግን በስምምነት መሆን አለበት፡፡ በተለይ ወሳኝ በሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ከሌለ ስለተጻፈ ብቻ ሥራ ላይ አይውልም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ችግር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ወረቀት ላይ የተጻፈው ሌላ ነው፣ ሥራ ላይ የሚውለው ሌላ ነው፡፡ ለምሳሌ ዴሞክራሲያዊ አስተዳዳር፣ ፍትሐዊ ምርጫ፣ እውነተኛ ፌዴራሊዝም ጽሑፍ ላይ ቢኖሩም ተግባራዊ አይሆኑም፡፡ በንጉሡ ዘመን ‹‹በሕግ አምላክ›› ካልክ ሰው ይቆማል፡፡ አሁን ያ የለም፣ የሕግ የበላይነት የለም፡፡ ፍርድ ቤት ብትሄድ፣ ፖሊስ ጣቢያ ብትሄድ፣ ሌላም ተቋምም ብትሄድ ከገዥው ፓርቲ ብቻ ትዕዛዝ የሚቀበሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ሕገ መንግሥቱ ብሔርና ቋንቋ ላይ ስለተመሠረተ ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የብሔርና የቋንቋ መብቴ ይከበር ይላሉ፣ ነገር ግን ሁለቱም መሬት ላይ የሉም፡፡ ለምሳሌ ኦሮሞን ተመልከት፣ ዋናው ጥያቄው አልተመለሰልኝም የሚለው ይህ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተጻፈ እንጂ ተግባራዊ አልሆነም ብሎ ነው ጫካ ገብቶ እየታገለ ያለው፡፡ በስምምነት እናሻሽል ካልን ሰጥቶ የመቀበል መርህን መከተል አለብን፡፡ ምንም ይሁን ምን ተስማምተን መሆን አለበት፡፡ ካልሆነ አደጋ ነው፡፡ ይህ አደጋ ደግሞ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ሊበትን ይችላል፡፡

ሪፖርተርአሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ  ዓውድ ውስጥ በኦሮሞና በአማራ የፖለቲካ ፍላጎቶች መካከል የሚታየውን ውጥረትና መገዳደርንዴት ይመለከቱታል?

መረራ (ፕሮፌሰር):- እሱን በደንብ የሚገልጸው የቡዳ ፖለቲካ የሚለው ነው፡፡ መፍትሔው መነጋገር ነው፡፡ ለመነጋገር ደግሞ ከዚያም ከዚህም የሚወረወሩ ነገሮችን ትመለከታለህ፡፡ ይህ ደግሞ የሰላምን በር ከመዝጋት ውጪ ሌላ ጥቅም የለውም፡፡ የቃላት ውርውሩ ፖለቲካውን ከማበላሸት ውጪ ሌላ አቅም የለውም፡፡ ምርጫ ቦርድ ተወሳስቦ የተያዘው ፖለቲካው ስለተበላሸ ነው፡፡ ምናልባትም ልጅቱ የለቀቀችው በጤና እክል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ሳያት ጤነኛ ናት፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር በጣም ጠቧል፡፡ አገሪቱን ችግር ውስጥ የከተቱ ሁሉም በመጨረሻ ሰዓት ይከፍላሉ፡፡ የሁላችንም ዋስ ዴሞክራሲ መሆን አለበት፡፡ ማን ምን ያህል ሥልጣን ላይ ይቆያል ነው ጥያቄው፡፡ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መብት እስካልተከበረ ድረስ ሰላም አይሰፍንም፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ተሸክሞ የትም መድረስ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ከብልፅግና አቅምና ብቃት በላይ ናት፡፡

ሪፖርተር፡– ስለመንግሥትና ስለኦነግ ድርድር የሚያውቁት ነገር ካለ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ምን ይፈይዳል ይላሉ?

መረራ (ፕሮፌሰር):- እኔም በስሚ ስሚ ነው የሰማሁት፡፡ ሆኖም ከመንግሥት ጋር በታንዛንያ ያልተስማሙት በሥልጣን ጥያቄ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ሥልጣን የማጋራት ፍላጎት የለውም፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ በምርጫ መካፈል ትችላላችሁ፣ የሠራችሁት ወንጀል ካለ አንነካችሁም የሚል ሐሳብ ከመንግሥት ተነስቷል፡፡ እነሱ ደግሞ ሥልጣን ካልያዙ በኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ ለአራተኛ ጊዜ ታሪካዊ ስህትት ሊሠሩ ነው፡፡ የመጀመርያው በመኢሶን ዘመን የኦሮሞ ምሁራን ከደርግ ጋር ተስማምተው በኋላ ያለቁበት ነው፡፡ እኔም ወንድሜን ገለውብኛል፡፡ ከዚያ በኋላ በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ መጣ የሆነው ሆነ፡፡ ኦነጎች መጥተው ሥልጣን ተካፈሉ፣ በኋላ ተጣልተው ወጡ፡፡ ሦስተኛ እነ ዳውድ ኢብሳ ከኤርትራ እናስተናግዳችኋለን ተብለው መጡ፣ የሆነውን ዓይታችሁታል፡፡ አሁን በታንዛንያ ነገ ምርጫ ትሳተፋላችሁ ተብሎ  ለማሳመን ተሞከረ፡፡ በምርጫው እንኳን እነሱ እኛ ከተማ ተቀምጠን ሰላማዊ ትግል የምናደርገው እንድንሳተፍ  ዕድሉ አልተሰጠንም፡፡ እዚህ ከተማ ላለነው ዕድሉ ሳይሰጥ እንዴት መሣሪያ ይዞ ጫካ የሚታገለው ይህን አምኖ ማሣሪያ ጥሎ ይመጣል? እንደ እኔ ትክክለኛ ጥያቄ ነው ያነሱት፡፡ የፖለቲካ ሜዳው ዴሞክራሲያዊ ከሆነ ወደ ጫካ የሚሄደው አውሬ መሆን አለበት፡፡ ብልፅግናም እንደ ኢሕአዴግ እየተጫወተ ነው፣ ወደ ጫካ እየገፋ ነው፡፡ መንግሥት ከተማ ያለውን ወጣት የሚደበድብ ከሆነ ወጣቱ ከተማ ምን ይሠራል? ስለዚህ ወጣቱ ከተማ ትቶ ወደ ጫካ ገባ፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (/) ወደ ሥልጣን ሲመጡ የገቡትን ቃል ፈጽመዋል ብለው ያምናሉ?

መረራ (ፕሮፌሰር):- ይህንን ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል፡፡ እኔም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የምትገባውን ቃል ካልፈጸምክ ያስቸግርሃል ብዬዋለሁ ቃልህን ሥራ ላይ ለማዋል ተዘጋጅ፣ መለስንም እንዲህ አድርግ ብዬው ነበር፡፡  ይህ ጉዳይ የመራራን ዕውቀት አይሻም፡፡ ይህንን የኦሮሚያ፣ የአማራና የትግራይ ጫካ ይመስክር፡፡ መፍትሔው አንድ ነው፡፡ የጋራ ብሔራዊ መግባባትና ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ  ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መፍጠር፡፡ ሌላ ‹‹ማጂክ ፎርሙላ›› ያለ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱን የኢኮኖሚ ስብራት እንዴት ያዩታል?

መረራ (ፕሮፌሰር):- ሳናውቅ ቀላል ያልሆነ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ጠፍቷል፡፡ በደርግ ጦርነት 17 ዓመታት ያለ ዕረፍት ስንት ሰው አለቀ? ስንት ንብረት ወደመ? ያ ትምህርት ቤት ቢሠራ ሆስፒታል ቢሠራ ምን ውጤት ይመጣ ነበር? ስለዚያ ጉዳት በደንድ ሳናስብ ኢሕአዴግ መጣ፡፡ በኤርትራ ጦርነት ስንት ሰው አለቀ? ስንት ንብረት ወደመ? በኋላ ሦስተኛው መጣ፣ ከሁሉም በላይ ውድመት አደረሰ፣ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደመ፡፡ ጦርነት አገሪቱን ወደኋላ ነው የወሰዳት፣ ተጠያቂነት ያስፈልጋል፡፡ በምትሠራው ነገር የማትጠየቅበት ከሆነ ያስቸግራል፡፡ እኔ ከፖለቲካው በላይ የሚያሰጋኝ የኢኮኖሚው ስብራት ነው፡፡ ወጣቱ ከተማ ዳቦ ከምለምን ብሎ መሣሪያ ይዞ ጫካ መግባትን አማራጭ አድርጓል፡፡ የዋጋ ንረቱ በቀላሉ ይቆማል ብዬ አላምንም፡፡

የእኔ ትልቅ ሥጋት በርካታ ተማሪዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡ በጎን የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራት እያለ ግርግር ይፈጥራል፡፡ ዋናው ጉዳይ አስተማሪ ሰርቪስ ውስጥ እየዋለ፣ በቂ ምግብ ሳይበላ፣ ሌላ ትርፍ ሥራ እየሠራ ነው የሚያስተምረው፡፡ ከዚያ የሚወጣው ወጣት ጥያቄው ነገ ምን አገኛለሁ ነው፡፡ ምን ተስፋ አለው? ይኼ ተስፋ ያጣ ወጣት ወደ ቀላሉ ሥራ ይገባል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ቀላሉ ሥራ ጠመንጃ ይዞ ጫካ መግባት ሆኗል፡፡ እዚህ የቀን ሠራተኛ ከሚሆንና እሱንም አጥቶ ባዶ እጁን ከማደር ጠመንጃ ይዞ ጫካ መግባት ይቀላል፣ ይኼ አደጋ ቀላል አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሥራ አጥነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ ይህ ወጣት ድሮ የቀን ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ አሁን ግን ወጣ ብሎ ምግቡን የሚያገኘው ጫካ በመግባት ነው፡፡ እኔ ለአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ሁኖ እያየሁ ያለሁት እሱን ነው፡፡ እዚህ ዳቦ ካላበላኸው ለምን እዚህ ተኝቶ ይሞታል? ጓደኛው፣ የሠፈሩ ልጅ እኮ ጫካ አለለት፡፡ ጠመንጃ ደግሞ አሁን ትርፍ ነው ለምን እንደሆነ ባላውቅም፡፡ እኔ ይህንን አደጋ በጣም እፈራዋለሁ፡፡ ይህ ተስፋ ያጣ ወጣት፣ የሊቢያ በረሃና የሜዲትራኒያን ባህር የሚበላው ወጣት፣ በታንዛንያ ጫካ በጅብ የሚበላ ወጣት እዚህ በሚያገኘው ጠመንጃ ለምን ጫካ ገብቶ አይበላም? የዋጋ ንረቱ በቀላሉ የሚቆም ነገር አይደለም፣ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ሙስና በሀቅ መቆም አለበት፡፡ መሠረታዊ የሆነ የፖሊሲ፣ የአስተዳደርና የአመራር ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የእርስዎ ምክትል አቶ ጀዋር መሐመድ ለምን ጠፉ፣ ለቀጣይ ምርጫ ምን አስባችኋል?

መረራ (ፕሮፌሰር):- እኔ እንደምገምተው የፖለቲካ ምኅዳሩ አልተመቸውም፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር ጠቦበታል፣ መንግሥትም እሳት ሆነበት፡፡ መንግሥት አሁን በገፋበት መንገድ ወደፊትም ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ይደረጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ከኦነግም ጋር ስምምነት አለን፡፡ ከእኛ ሃምሳ በመቶ ከእነሱ ሃምሳ በመቶ ተወካዮችን አዘጋጅተን በምርጫ ለመምጣት ዕቅድ አለን፡፡ በትብብርም ለመሥራት ተስማምተናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -