Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ከታክስ በፊት ስድስት ቢሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የገቢና ወጪ ዕቃዎች የማጓጓዝ ሥራዎችን የሚሠራው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በ2015 የበጀት ዓመት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶችና ከሌሎች የገቢ ምንጮች ከታክስ በፊት 6.06 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኘ፡፡

ድርጅቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመርከብ አገልግሎት ዘርፍ በራሱ መርከቦች፣ የኪራይ (Slot Carrier and Charter) መርከቦችን በመጠቀም 3,890,680 (ሦስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ዘጠና ሺሕ ስድስት መቶ ሰማኒያ) ቶን ዕቃ ለማጓጓዝ አቅዶ 4,095,550 (አራት ሚሊዮን ዘጠና አምስት ሺሕ አምስት መቶ ሃምሳ ቶን) ማጓጓዙ ታውቋል፡፡ በ2014 የበጀት ዓመት ይህ አኃዝ 3,616,343 (ሦስት ሚሊዮን ስድስት መቶ አሥራ ሦስት ሺሕ ሦስት መቶ አርባ ሦስት) ቶን እንደነበር ይታወሳል፡፡

ድርጅቱ እንዳለው ከሆነ ከአራት ሚሊዮን በላይ የገቢ ጭነቶችን በባሕር ባጓጓዘበት ዓመት፣ ከባሕር ትራንስፖርት ከጭነት ማስተላለፍና በወደብና ተርሚናል ከሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲሁም ከሌሎች የገቢ ምንጮች 42.73 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል፡፡

ሪፖርተር ከድርጅቱ ባገኘው መረጃ መሠረት ከፋይናንስ አፈጻጸም አንፃር ኢባትሎአድ በ2015 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት 5.4 ቢሊየን ብር ለማግኘት አቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የተገኘው ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍ 6.06 ቢሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡

ድርጅቱ ካጓጓዘው አጠቃላይ ጭነት ውስጥ በመልቲሞዳል የትራንስፖርት ሥርዓት ከ92 ሺሕ በላይ ባለ ሃያ ጫማ ኮንቴይነሮች የሚገኙ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ከሦስት ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በዩኒ ሞዳል ከ1.6 ሚሊዮን ቶን በላይ ገቢ እንዲሁም ከ281 ሺሕ ቶን በላይ ወጪ ጭነት ማስተላለፉ የታወቀ ሲሆን፣ በሚሰጠው የወደብና ተርሚናል አገልግሎት 347,876 (ሦስት መቶ አርባ ሰባት ሺሕ ስምንት መቶ ሰባ ስድስት) የቲኢዩ ኮንቴይነሮች ማስተናገዱ ተጠቅሷል፡፡

ምንም እንኳን ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ያገኘው ገቢ እንደተጠበቀ ሆኖ በአገሪቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት በሦስት ደረቅ ወደቦች (መቀሌ፣ ኮምቦልቻና ወረታ) ሙሉ በሙሉና በከፊል ጉዳት በመድረሱ ምክንያት ለረዥም ጊዜያት አገልግሎት መቋረጡ፣ መንግሥታዊ የሆኑ አስመጪ ድርጅቶች ለሚያስመጧቸው ጭነቶች የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን አለማሟላትና ክፍያ አለመፈጸም ተግዳሮቶች ሆነው እንደቆዩ ሲገልጽ ነበር፡፡

በዓለም ላይ የተከሰተው የማጓጓዣ ዋጋ (Freight Rate) መናርና የኮንቴይነር እጥረት መከሰቱ፣ እንዲሁም ማዳበሪያ ግዥ በወቅቱ ተፈጽሞ ከማጓጓዝ በተገናኘ የተለያዩ ክፍተቶች እክል እንደሆኑበት ከዚህ ቀደም ያስታወቀው ኢባትሎአድ በአጠቃላይ የበጀት አፈጻጸሙ ዙሪያ በቀጣይ መግለጫዎችን እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች