Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር መጠን በ25 በመቶ እንዲገደብ ወሰነ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሰኔ ወር መጨረሻ የዋጋ ንረትን ከ20 በመቶ በታች ለማድረግ ታቅዷል

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዱ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ እንደሚያደርግ ሲያስታውቅ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር መጠን በ25 በመቶ እንዲገደብ ወሰነ፡፡

የብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ወዲያውኑ ሥራ ላይ እንዲውሉ ካሳለፋቸው በርካታ የፖሊሲ ዕርምጃዎች መካከል፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር መጠን በእጅጉ ለመቀነስ የተወሰነው ይገኝበታል፡፡ የቦርዱ ውሳኔ ይፋ የተደረገው ዓርብ ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር መጠን በእጅጉ በመቀነስ ከዓምናው ከሲሶ ወይም ከ1/3ኛ አንዳይበልጥ የወሰነ ሲሆን፣ በሌላ አነጋገር ይህ የብድር መጠን በ25 በመቶ ይገደባል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ቀጥታ ብድርን እንደ የመጨረሻ አማራጭ የሚጠቀመው የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ፣ በበቂ መጠን ለገበያ መቅረብ ሳይችል ሲቀር ብቻ እንደሚሆን መግባባት ላይ መደረሱን ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠሙ ተከታታይ ጫናዎች (ኮቪድ፣ ግጭት፣ ድርቅ) የመንግሥት የወጪ ፍላጎት እንዲጨምርና የገቢ ዕድገት እንዲቀንስ በማድረጋቸው፣ የኢትዮጵያ የፊስካል ተግዳሮት ከፍ ብሏል ሲል የገለጸው ማዕከላዊ ባንኩ፣ ይህ በመሆኑም የመንግሥት የበጀት ጉድለት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ብሏል፡፡

የውጭ ብድርና ዕርዳታ ውስን በመሆኑ አብዛኛውን የበጀት ጉድለት ከአገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮች፣ በተለይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚገኝ ብድር እንዲሸፈን መገደዱን ባንኩ አስታውሷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድና ሥራ አመራር በ2016 የበጀት ዓመት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ቅድሚያ በመስጠት በበጀት ዓመቱ ለመንግሥትም ሆነ ለግሉ ዘርፍ በሚሰጠው ብድር ዕድገት ላይ ገደብ ለማስቀመጥ መወሰኑን ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የባንክ (የክሬዲት) ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንደሚገደብ፣ በዚህም ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲያስተካክሉ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ባንኮች የጥሬ ገንዘብ አጥረት ሲገጥማቸው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ የብድር ፋሲሊቲ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል የተባለ ሲሆን፣ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ወጪ ንግድ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ (forex surrender requirement) እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው አዲሱ መመርያ መሠረት፣ የሸቀጦችና የአገልግሎት ላኪዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ፣ አሥር በመቶ ለባንካቸው የሚያስተላልፉ ሲሆን፣ ቀሪውን 40 በመቶ ወደ ራሳቸው የባንክ ሒሳብ እንዲያስገቡ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ይፋ የተደረጉት የገንዘብ ፖሊሲ ዕርምጃዎች የባንክ ብድር (ክሬዲት) ዕድገትን ከመቀነስ ውጪ ብድሩን እንደማያስቀሩ ልብ ሊባል ይገባል ያለው ብሔራዊ ባንክ፣ የክሬዲት ዕድገትን መግታት በራሱ ግብ ሳይሆን በኢትዮጵያ የዋጋ ንረትን በቀጣይነት ለመቀነስ የሚደረግ የጋራ ዓላማ ወሳኝ ክፍል እንደሆነ ይታወቅ ብሏል፡፡

የብድር ጣሪያን በተመለከተ የተላለፈው ውሳኔ እስከ 2016 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ ብቻ የሚቆይ ጊዜያዊ ዕርምጃ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከዚያ በኋላ ባንኩ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ አገሮች ወደ የሚጠቀሙበት በወለድ ተመን ላይ ወደ ተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ የሚሸጋገር እንደሚሆን ይፋ ተደርጓል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በዋነኛነት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ከሚገኝባቸው ሦስት ጉዳዮች ውስጥ ቀዳሚው የዋጋ ንረትን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን በቅርቡ ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የአቅርቦት ውስንነት፣ የማምረቻ ወጪ መጨመርና ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች በተለያየ ደረጃና በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ለዋጋ ንረት መንስዔ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ሌሎች አካላት ያደረጓቸው የተለየዩ ጥናቶች አሳይተዋል፡፡

ባንኩ በሰኔ 2015 ዓ.ም. ባደረገው ዝርዝር ግምገማ የአቅርቦት ውስንነት፣ የማምረቻ ወጪ መናር (ውጫዊ ምክንያቶችን ጨምሮ) እና ልል የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲዎች በድምሩ በኢትዮጵያ ለተከስተው የዋጋ ንረት አስተዋጽኦ እንዳላቸው ማረጋገጡን አመላክቶ ነበር።

በኢትዮጵያ በተከታታይ በታዩ ውስጣዊና ውጫዊ ክስተቶች (ኮቪድ፣ ግጭት፣ ድርቅ፣ ዓለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታዎች) የተነሳ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲዎች ላላ እንዲሉ መደረጉ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለዋጋ ንረት ብቸኛ ምክንያቶች ባይሆኑም፣ የዋጋ ንረትን የመዋጋት ሥራን እንዳልደገፉ ያስታወሰው ብሔራዊ ባንክ፣ ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋ የተደረገው ውሳኔ በመካከለኛው ጊዜ የዋጋ ንረት ሥጋት እንደሚኖር ታሳቢ በማድረግ የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ደረጃና በቀጣይነት ለመቀነስ ተገቢና ቁጥብ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን መውሰድ ስለሚያስፈልግ የተወሰነ እንደሆነ ገልጿል፡፡

የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ከሚወሰዱ አጠቃላይ ዕርምጃዎች በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የዋጋ ንረትን ከ20 በመቶ በታች፣ በ2017 ዓ.ም. ደግሞ ከአሥር በመቶ በታች ለማውረድ የታሰበው ዕቅድ ይገኝበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች