Saturday, September 23, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ይቅርታና ቅንነት እስከ ምን?

በቤተልሔም መኮንን

በአንድ ወቅት በአንድ መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሦስት ሴቶች ነበሩ፡፡ አንደኛዋ የሁለቱ ሴቶች አለቃ ስትሆን፣ ሁለቱ ሴቶች ደግሞ ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ባልደረቦች ናቸው፡፡ ሁልጊዜም ሥራቸው የግድ ከሁለቱ አንዱ እንዲኖሩ ያስገድዳልና አንደኛዋ ስትቀር አንደኛዋ መሸፈን ግዴታ ነው፡፡ በመሆኑም አንደኛዋ ሁልጊዜ ፈቃድ ስትፈልግ  ባልደረባዋ ሥራዋን ስለምትሸፍንላት በፈለገችው ሰዓት ትወጣለች፡፡ ነገር ግን ሌላኛዋ ፈቃድ በምትፈልግበት ሰዓት ባልደረባዋ ልትሸፍንላት ፈቃደኛ ስለማትሆን አትወጣም ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ አንደኛዋ እንደለመደችው መልካሟን ሴት ሄዳ ሸፍኝልኝ አለቻት፣ ያቺ መልካም ሴትም እንደ ሁል ጊዜው ሳታቅማማ እሺ አለቻት፡፡ ያኔ ጮሀ ማልቀስ ጀመረች፣ አለቅየዋ ደንግጣ ከቢሮ ወጣችና ምን ሆና እንደሆነ ጠየቀቻት ልጅቷም ‹‹አልቻልኳትም በመልካምነቷ አሸነፈችኝ እኔ ብዙ ጊዜ እንድሸፍንላት ስትጠይቀኝ እምቢ እያልኳት እሷ ግን ሁሌም ስጠይቃት እሺ ትለኛለች፤›› በማለት መለሰች፡፡

አለቅየዋ በዛችኛዋ መልካምነት ተማርካ ወደ ቢሮዋ ይዛት ሄደችና ጠየቀቻት፡፡ ‹‹እንዴት እንዲህ ልትሆኚ ቻልሽ ካንዴም፣ ሁለት፣ ሦስቴ እሷ ክፉ ብትሆንብሽም አንቺ ግን ሁሌም በመልካምነት ነው የምትመልሽላት ለምንድን ነው?›› በማለት ጠየቀቻት፡፡ ልጅቷም ‹‹በርግጥ እሷ እምቢ ስትለኝ በጣም እናደድ ነበር፣ እሷ ስለከለከለችኝ ፈቃድ ባልወጣሁባቸው ቀናት በጣም ብዙ ያጣኋቸውና የተጎዳኋቸው ጉዳቶች ነበሩ፡፡ እኔ ዕረፍት በማጣቴ ብዙ ነገሮች ተበላሽተውብኛል፣ ነገር ግን ነገ እኔም በተራዬ እሷ ፈቃድ እንዳትወጣ ብከለክላትና የእሷም ነገሮች እንደ እኔ ቢበላሹባት፣ እኔ ልክ አሁን እንደተናደድኩት ብትናደድ እኔ ምን አገኛለሁ? በቀጣይስ ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖረናል? እኔም እንደ እሷ የማደርግ ከሆነ እኔስ ከእሷ በምን እሻላለሁ? ብዬ አሰብኩ፡፡ በቃ እሷ እንዲህ ነች፣ ከቻልኩ እሷ ከእኔ መልካምነትን እንድትማር ማድረግ  እንጂ ከእሷ ክፋትንና ራስ ወዳድነትን መማር የለብኝም ብዬ ወሰንኩ፡፡ ከዚያ በኋላ እሷ በጠየቀችኝ ሰዓት በጣም ደስ እያለኝ ነው የምሸፍንላት፣ ያን ሳደርግ ደግሞ ለራሴ በጣም እርካታን ይሰጠኛል፣ እንደውም ሁሌ ብትወጣና ብሸፍንላት ደስታውን አልችለውም፤›› በማለት መለሰችላት፡፡ 

አሁን በዓለማችንና በአገራችን ውስጥ ያለው ትልቁ ትርምስና ችግር የዚህችን መልካም ሴት ዓይነት ቅን ልብ ማጣት ነው፣ የዓለምን ኑሮ እጅግ ያከበድነው እኮ በክፉዎች ሴራ ብቻ ሳይሆን በክፉዎች ሴራ ምክንያት ተጎዳን በምንል ሰዎች በቀልና ‹‹የአፀፋ ምላሽ›› የተነሳ ነው፡፡ ስንቶቻችን ነን የልጅቷን ያህል ቅን ልብ ያለን? ሰዎች ምንም ያህል ቢጎዱን አፀፋ ከመመለስ ይልቅ በእኛ መልካምነት ልብ እንዲገዙ ሞክረን የምናውቅ? ምንም መወሻሸት አያስፈልገንም፣ አብዛኞቻችን ፍርድ ሰጪዎች ነን ከነአባባሉም ‹‹ብድሩን የማይመልስ ወንድ አይወለድ›› እያልን እንተርታለን፣ በእልህና በትዕቢት እየነዳንና እየተነዳን ለበቀል ከመዘጋጀት ይልቅ ቆም ብለን፣ ምን ሆና ነው? ምን ሆኖ ነው? ብለን ያን ሰው ለመረዳት መሞከርና በክፋት አስቦም ከሆነ እንደ ልጅቷ በመልካምነት ለማስተማር የሚታሰብ አይደለም፡፡

አንዳንዴ ክፉዎች ናቸው የምንላቸው ሰዎች ለምን እንደዚያ እንደሆኑ አስበን አናውቅም፣ የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ሲመጣ አዕምሮው ንፁህ ወረቀት ሆኖ ነው፡፡ እዚያ ንፁህ ወረቀት ላይ የሚጽፉት ወላጆች፣ ዘመዶች፣ ጎረቤቶችና ማኅበረሰቡ ናቸው፡፡ ያ ሰው ታዲያ እነዚህ ሁሉ አካላት በጋራ ሆነው በሰጡት ማንነት ለምንድነው የሚፈረድበት? ራሳችንን በዚያ ሰው ጫማ ውስጥ እናስገባና እናስበው፣ እኛስ ብንሆንስ በዚያ ሁኔታ ነው ያደግነው? ሲጀመር ራሳችንስ እንደዚያ ሰው አለመሆናችንን ምን ያህል እርግጠኛ ነን? ምክንያቱም ከዚያ ሰው የተሻልን ሰዎች ነን ብለን የምናስብ ከሆነ የታለ መልካምነታችን? የታለ ርህራሄያችን? የታለ ፍቅራችን? የታለ ይቅርባይነታችን? የዚያን ሰው ክፋት መልሰን በእሱው ላይ ከደገምነው ታዲያ ከእሱ በምን ተለየን፡፡

በአንድ ወቅት አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ ታሪክ ትዝ ይለኛል፣ ከእሱ ጋር አብራ የምትሠራ አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ያቺ ሴት ሁሌም ደስተኛ አልነበረችም፣ በቃ ከዚያም ከዚያም ጋር ትጋጫለች፣ ቀኑን ሙሉ ስትነጫነጭ ነው የምትውለው፣ ነገር ግን ማንም ሰው ይቺ ሴት ችግሯ ምንድነው ብሎ ሊረዳት የሞከረ አልነበረም፡፡ ሁሉም መጥፎ ሰው ናት፣ ሰው ትጠላለች ብለው ፈረጇት፣ ለሥራ እንኳን ከእሷ ጋር ሲገናኙ አስቀድመው በጥላቻ መንፈስ ነበር የሚቀርቧት፣ ያ ሁኔታ ደግሞ የበለጠ ልጅቷ ያለችበትን ሁኔታ አባባሰው፣ እናም መታመም ጀመረችና ሐኪም ቤት ሄዳ ስትመረመር፣ የጭንቅላት ዕጢ እንዳለባት ተነገራት፣ ለካ ለዚያ ነበር ትነጫነጭ የነበረው፣ እናም ልጅቷ በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙም ሳትቆይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ አብረዋት ሲሠሩ የነበሩት ልጆች በጣም ተፀፀቱ፣ አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ለልጅቷ በፍጥነት መሞት ሁሉም አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ልጅቷን ተረድተዋት ቢሆን ኖሮ እሷ ስትነጫነጭ በጥላቻ ከመመለስ ይልቅ ሰው ወዶ እንደዚያ እንደማይሆንና አንድም በአስተዳደግ ወይ ደግሞ በሆነ ችግር ምክንያት እንደሚሆን አስቦ እንደ መልካሟ ሴት መልካምነትን ለማስተማር ቢሞክሩ ኖሮ ልጅቷ ልትድን ሁሉ የምትችልበት አጋጣሚ ይኖር ነበር፡፡ ለዚህ ነው እናቶቻችን ማዘን ለክፉ ነው የሚሉት፡፡

ፈጣሪያችን በቀላችሁን ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ ነው ያለን፡፡ እኛ ግን የበደለንን ሰው በቻልነው መጠን ተበቅለነው አላረካ ሲለን ነው ፈጣሪ እንዲበቀልልን የምንፈልገው፡፡ ነገር ግን ቂምና በቀልን በውስጣችን አኑረን ሰዎችን ለመጉዳት የምንጓዘው ጉዞ ‹‹መርዝ ራሳችን ጠጥተን የተቀየምነው ሰው እንዲሞት መጠበቅ ነው›› ይባላል፡፡ በቀላችን የምንበቀለውን ሰው ከመጉዳቱ በፊት አስቀድሞ እኛን ነው የሚገድለን፡፡ ስለሆነም ውስጣችን ያለው የበቀልና የፈራጅነት አባዜ ከውስጣችን እስካልወጣና ልባችን እንደ መልኳሟ ሴት በርህራሄና አጥፊን በማጥፋት ሳይሆን ወደ ትክክለኛው መስመር በመመለስ ካልተሞላ በምድሩም በሰማዩም ከበዳያችን ቀድመን የምንጎዳው ራሳችን ነን፡፡

እስቲ ውስጣችንን እንመርምር፣ ውስጣችን ውስጥ ስንት ክሶች አሉ? የሚመለከቱንም የማይመለከቱንም፣ አፈጻጸሙ ግራ ገብቶን እንጂ ፍርድ የሰጠንባቸው ስንት ብይኖች አሉ? ቤተሰቦቻችንና የትዳር አጋሮቻችን፣ አለቃችንና የሥራ ባልደረቦቻችን፣ የቤት አከራዮቻችንና ጎረቤቶቻችን፣ ዘመዶቻችንና ጓደኞቻችን፣  መንግሥትና የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ባለታክሲዎች፣ ባለመኪናዎች፣ በየመንገዱ የሚያጋጥሙን የምናቃቸውም የማናቃቸውም ሰዎች… ወዘተ በቀን ውስጥ ስንት ክስ እናስተናግዳለን? ስንት ብይንስ እናሳልፋለን? የሚገርመው ግን እነዚህ ሁሉ የምንናደድባቸውና የከሰስናቸው ሰዎች በጣም ተረጋግተውና ደስተኛ ሆነው ኑሯቸውን እየኖሩ ነው፡፡ እኛ ግን በእነሱ ምክንያት ደስታ የራቀው ቀን እያሳለፍን ነውና ማንን ነው እየጎዳን ያለነው? ስለዚህም ቅን መሆንና ይቅርታ አድራጊ መሆን ያለብን ለማንም ሳይሆን ለራሳችን ስንል ነው፡፡ ፈጣሪያችን ሁሉን ማድረግ የሚችለው እንደኛ ቢሆን የሰው ልጅ በዚህች ምድር ይኼን ያህል ሺሕ ዘመኖች ባልኖረ ነበር? እኛ በደለኞቹ በሐሳባችንም በድርጊታችንም ስህተት ሳንሠራ መንቀሳቀስ የማንችለው ሰዎች ይቅርና፣  ፍጹም ንፁህ ፍጹም ቅዱስ የሆነው አምላክ ከባድ የሆኑ የርኩሰት ሥራዎች እዚህ ምድር ላይ እያየ ለፍርድ አይቸኩልም ይልቁንም ‹‹አትፍረድ ይፈረድብሃል›› ብሎ በታላቁ መጽሐፍ አስተማረን እንጂ፡፡

ዝሙት ውስጥ የነበረችው የማርያም መግደላዊት ታሪክ መቼም ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ጌታ እግር ላይ ወድቃ እግሩን በእንባ እያጠበች በፀጉራ ስታደርቅ አይሁዶች መጥተው እቺ ሴት ዘማዊ ስለሆነች በአይሁድ ሥርዓት በድንጋይ ተወግራ ትገደል ብለው ፈረዱባት፡፡ ጌታ ግን ከመሀላችሁ ምንም ኃጢዓት የሌለበት ካለ በድንጋይ ወግሮ ይግደላት፣ ብሎ መሬቱ ላይ ጫር ጫር ሲያደርግ የእያንዳንዳቸው ኃጢዓት ግንባራቸው ላይ ተጽፎ ታየ፣ የሴቲቷ ከሳሾችም በድንጋጤ አካባቢውን ጥለው ጠፉ፣ ኢየሱስም ማርያም መግደላዊትን ሁለተኛ ይኼን ሥራ እንዳትሠራ አስተምሮ ሸኛት፡፡

ሼክስፒር ‹‹እንደ በረዶ የነጻህ ብትሆንም ከሐሜት አታመልጥም›› እንዳለው፣ በዚህች ምድር ያለ ማንኛውም ሰው በጥፋቱም ሆነ ያለ ጥፋቱ ያልተከሰሰና ጣት ያልተቀሰረበት ሰው የለም፡፡ ሁላችንንም ሰዎች እንደከሰሱንና እንደፈረዱብን፣ እኛም ሰዎችን እንደምንከሰውና እንደምንፈርደው ፍርድ ቢሆን ማንም ምድር ላይ የሚቀር አይኖርም፣ ዓለምም ዖና ሆና ትቀር ነበር፡፡

በዓለማችን ላይ ምንም በደል ሳይኖርባቸው በሐሰት ውንጀላ ብቻ ከ30 እና 40 ዓመት በላይ የተፈረደባቸውና ከእነዚያ ሁሉ ዓመታት እስር በኋላ ጥፋተኛ አይደላችሁም ተብለው የተፈቱ፣ ዕድሜያቸውን የተሰረቁ፣ ይባስ ብሎም በሞት ቅጣት የተቀጡ ሰዎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ አብዛኞቻችን ሰዎችን በመክሰስና በመፈረጅ ራሳችንን የምናፀድቅ ነው የሚመስለን፡፡ ለዚህም ነው ዓለም አሁን የያዘችውን ቅርጽ የያዘችው፣ ለሚፈጠሩት ማንኛውም ችግሮች ሁሉም ሰው ኃላፊነት አይወስድም፡፡ ከራሱ አልፎ ሁሉም ሰው ጣቱን በሌሎች ላይ ይቀሥራል፣ አንዱ አንዱ ላይ ይጠቁማል ወይም ደግሞ በድምፅ ብልጫ ከችግሩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለው ምስኪን ሰው ላይ በማሳበብ፣ ችግሩ የበለጠ እንዲሰፋና የበለጠ እያመረቀዘ መስተካከል የማይችልበት ደረጃ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው ችግሩ ሲፈጠር ለችግሩ መፈጠር የእኔም ድርሻ አለበት ብሎ ቢያስብና በእሱ በኩል ያለውን ስህተት ለማረም ቢሞክር ችግሩን ከሥሩ ማድረቅ ይቻል ነበር፡፡

‹‹ኡኡኡ… ዘመኑ እኮ ከፍቷል ጿጿጿ…›› እያልን በሰዎች እያመካኘን ከንፈራችንን ከመምጠጥ ውጭ ራሳችንን ለመመልከት ሞክረን ስንቶቻችን እናውቃለን?   ዓለም እኮ እኛ ነን፣ አገር እኛ ነን፣ የእኛ የሰው ልጆች ስብስብ ነው፡፡ አገርም ዓለምም የሚሆነው ታዲያ እኛ ያልሰጠናትን መልካምነትና ቅንነት ዓለም ከየት አምጥታ ትስጠን? ዘመን ይመጣል ይሄዳል እኛ ነን ክፉም ደግም ዘመን የምናደርገው፡፡

ስለዚህ ሌሎችን የከሰስንበትን ዶሴ እንዝጋና የራሳችንን ዶሴ እንክፈት፡፡ ሌሎችን የመዘንበትን ሚዛን እስቲ ራሳችንን እንመዝንበት፣ እንዲሻሻል የምንፈልገው ነገር ካለ ማሻሻልና መቀየር የምንችለው ራሳችንን ብቻ ነው፡፡ ሙሉ ሥልጣንና ምርጫ በተሰጠን እኛነታችን ላይ እንሥራ፡፡ ፈጣሪያችን በታላቁ መጽሐፍ ‹‹ላንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ነገር ለሰዎችም እንዲሁ አድርግ›› እንዳለው፣ ሌሎች እንዲሆኑልን የምንፈልጋቸውን ነገሮች እኛ በመሆን እንጀምር፣ ብዙ ጊዜ ሰዎች ቅንና መልካም ሲሆኑልን በጣም ደስ ይለናል፣ ታዲያ ያ በሰዎች የወደድነውን መልካምነት ለምን ገንዘባችን አናደርገውም? ለጥፋቶቻችን ሁሉ ሰበብ እየፈጠርን በእገሌ ምክንያት፣ እንዲህ ስለሆንኩኝ፣ ስለተበደልኩኝ እያልን የሰዎቹን ስህተት እኛም ከመድገማችን በፊት ራሳችንን እስቲ ቅንነትን እናላብሰው፣ ቅንነትን ስንለብስ በሰዎች ከመፍረድ ይልቅ ለሰዎች ማዘን እንጀምራለን፡፡ ለሰዎች ማዘን ስንጀምር ሰዎችን መረዳት እንጀምራለን፣ ሰዎችን መረዳት ስንጀምር፣ ለሰዎች ይቅርታ ማድረግ እንጀምራለን፣ ይቅርታ ማድረግ ስንጀምር ዘር ቀለም ሳንለይ ሰዎችን መውደድ እንጀምራለን፡፡ ከዚያም ልክ እንደ ልጅቷ በክፋት ሲመጡብን በመልካምነት ለመቀየር እንሠራለን፣ እንደዚያ ስንሆን ደግሞ እርስ በርስ ፍቅርና ሰላም ይሆናል፡፡

ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋራው የሁለት ወንድማማቾች የቅንነት ታሪክ ሁሌም ልቤ ውስጥ አለ፡፡ ወንድማማቾቹ ወላጆቻቸው በሞት ከተለዩዋቸው በኋላ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላም ታላቅ ወንድምዬው ትዳር ለመያዝ ወሰነና ከታናሽ ወንድሙ ጋር ሀብት ንብረት ተካፍሎ ለብቻው እዚያው ከወንድሙ ብዙ ሳይርቅ ቤት ሠራ፡፡ ዘመኑ ሀብት በእህል በሚገለጽበት ዘመን ነውና ወንድማማቾቹ እህሎቻቸውን ተካፍለው በየጎተራቸው አስገቡ፡፡ ነገር ግን ወንድማማቾቹ አንዳቸው ላንዳቸው ሌት ተቀን ያስባሉ፣ ታናሽዬው ሁልጊዜ፣ ‹‹ወንድሜ እኮ ትዳር ይዟል ልጅ ይወልዳል ከእኔ ጋር እኩል የተካፈለው እህል እኮ አይበቃውም፣ እኔ ብቻዬን ነኝ የሚሻማኝ የለም፤›› ይልና በሌሊት ሁሉም ሲተኛ አንድ አኩፋዳ እህል በጨለማ እየወሰደ ወንድሙ ጎተራ ያስገባል፡፡

በተመሳሳይ ታላቅየውም ስለወንድሙ ይጨነቃል፣ ‹‹ወንድሜ እኮ ብቻውን ነው፣ ማንም ካጠገቡ የለም፣ ቢቸግረው እንኳን ማንም አያግዘውም”፣ ይልና እሱም በየቀኑ አንድ አኩፋዳ እህል በጨለማ ማንም ሳያየው የወንድሙ ጎተራ ያስገባል ከዛም ሁለቱ ወንድማማቾች ሲያዩ እህላቸው አይጎልም፣ እና ሁለቱም ይገረማሉ፡፡ በየግላቸውም እንዴ እኔ በየቀኑ አንድ አኩፋዳ እየወሰድኩ ይሄ እህል እንዴት አይጎልም ይላሉ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ሁለቱም አኩፋዳቸውን ተሸክመው ሲሄዱ በመንገድ ላይ እኩል ተገናኙና ተቃቅፈው አለቀሱ፡፡ ቅንነት እንዲህ ነው፡፡ የሁለቱም ወንድማማቾች ልብ በፍቅርና፣ በቅንነት የተሞላ ስለሆነ አንዳቸው አንዳቸውን ይረዳሉ፣ አንዳቸው ላንዳቸው ያስባሉ፣ አንዳቸው ላንዳቸው ያዝናሉ፣ አንዳቸው ላንዳቸው ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ የትኛቸውም ጋ አይጎልም፣ ሁሌም ሙሉ ነው፡፡ ነገር ግን አንደኛቸው ራስ ወዳድ ቢሆኑ ታሪካቸው ይኼ ሳይሆን እንደ አቤልና ቃየል የመገዳደል ታሪክ ይሆን ነበር፡፡

ስለዚህ እኛም እርስ በርስ ጣት መቀሳሰራችንን ትተን፣ በፍቅር እንደ ወንድማማቾቹ ተሳስበን፣ ሌሎች ማለታችንን ትተን ሁላችንም የራሳችንን የቤት ሥራ ብንሠራ፣ ራሳችንን መልካምና ቅን ብናደርግ፣ ሁሉም በየግሉ አጠገቡ ላለው ወንድሙ የፍቅር፣ የርህራሄና የምሕረት ልብ ቢኖረው፣ አገራችን ብሎም ዓለም ምን ዓይነት መልክ ይኖራት ነበር?  

እርግጥ ነው ዲያቢሎስ በምድር ላይ ተከታዮቹን መምራት እንደሚችል የተሰጠው ሥልጣን አለ፡፡ ዓለም የፈጣሪንም የሰይጣንንም መንገድ ይዛለች፡፡ መልካሞች እንዳሉ ሁሉ ክፉዎችም አሉ፣ ነገር ግን አሁን በጣም ችግር የሆነው የፈጣሪን መንገድ፣ መልካሙን ጎዳና ነው የምንመርጠው የምንለው ሰዎች፣ በክፉዎች ወጥመድ እየወደቅን፣ የክፉዎችን መንገድ በመከተላችን፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ይልቅ ለዲያቢሎስ በመገዛታችን፣ መልካምነትን እንደ ኋላ ቀርነት እየቆጠርን እልኸኝነትንና፣ በቀለኝነትን በማበረታታችን፣ የዲያቢሎስን ተከታይ ቁጥር በዓለማችን ሚዛን እንዲደፋ በማድረጋችን፣ በዓለማችን የበዙት ለጆሮ እንኳን ለመስማት የሚዘገንኑ ክፉ ሥራዎች እንዲስፋፉ አስተዋጽዖ እያደረግን ነው፡፡

በመሆኑም ሼክስፒር በግጥሙ ‹‹ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፣

                           ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፤››  እንዳለው ሁላችንም የልጅቷንና የወንድማማቾቹን ማስተዋልና መልካምነት አርዓያ በማድረግ ከክፎች ከመማር ይልቅ መልካምነትን ማስተማር፣ ከስግብብብነትና ለእኔ ለእኔ ከማለት ይልቅ መተሳሰብ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው በመረዳት፣ ለመልካምነት ዘብ በመቆም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቁጥር ማብዛት ይጠበቅብናል፣ ይህን በማድረግ ለአገራችን መልካም ዜጎችን ማፍራት ብንችል ኢትዮጵያችንን የዓለማችን ታላቋ አገር ማድረግ እንችላለን፡፡ በእኔ፣ ባንተ፣ ባንቺ በእኛ በልጆቿ ቅንነት ብቻ ኢትዮጵያ ከኃያላን ኃያል አገር መሆን ትችላለች፡፡ ምክንያቱም እሷ በተፈጥሮ ሀብታም ግን በዜጎቿ ቅን አለመሆን፣ ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ደሃ የሆነች አገር ስለሆነች፣ አሁንም የልጆቻችን ታላቅ አገር እጃችን ላይ ነች፡፡ በመሆኑም ክፉዎች ሳያጠፉብን ራሳችንን ቅን በማድረግ፣ በምሕረት፣ በርህራሄና በፍቅር አገራችንን ታላቋ ኢትዮጵያ እናድርጋት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles