Saturday, September 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ግልጽነት ይላበስ!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ16 ተቃውሞ፣ በ12 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም ለመከታተልና ለመቆጣጠርም መርማሪ ቦርድ በምክር ቤቱ ተሰይሟል፡፡ አዋጁ በአገሪቱ ሕግ አውጭ አካል ፀድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ሊታሰብባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ የማይገደቡ መብቶችን መጠበቅ ይጠቀሳል፡፡ በአማራ ክልል በተከሰተው መጠነ ሰፊ ግጭት ሳቢያ ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳትና የንብረት ጥፋት በመድረሱ፣ በሕግ ማስከበር ሒደት ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ግጭቱ በፍጥነት ቆሞ ለተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ተለይተው፣ ሰላማዊ ዓውድ የሚፈጥር የንግግር መድረክ ማመቻቸት ይገባል፡፡ ከዚያ በመለስ ከሕግ አግባብ ውጪ ግለሰቦችን ማሰር፣ መደብደብ፣ ያሉበትን ቦታ ለቤተሰብ አለማሳወቅና በግልጽነት ኃላፊነትን አለመወጣት እንዳይኖር ጠንካራ ቁጥጥር መደረግ ይኖርበታል፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም ሕገወጥ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማፅደቅ በተጨማሪ በአፈጻጸም ወቅት ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ በማፈላለግ፣ የሕዝብ ቅሬታዎችን በመከታተል፣ ከአዋጁና ከአፈጻጸም መመርያው በተቃራኒ የሚከናወኑ ድርጊቶችን በማስቆም፣ ሕዝቡ ቶሎ ቶሎ መረጃ እንዲያገኝ ግፊት በማድረግ፣ ግልጽነት የሚጎድላቸውን ተግባራት በማስቆምና በመሳሰሉት ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ የአማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን አገርን ለማረጋጋትና ሕዝቡን ከጭንቀት ውስጥ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት፣ ሕገወጦች የበላይነት ከያዙ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ይቀራል፡፡ ሕዝቡ ሰላምን፣ ዴሞክራሲንና ልማትን በነፃነት የሚያጣጥምበት ሥርዓት እንዲፈጠርና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ነው የሚፈልገው፡፡ ይህ አስቸጋሪ ወቅት አልፎ በመላ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የሆኑ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ የሚፈልግ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ አገሩ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ ወጥታ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት፡፡ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ሊከሰቱ የሚችሉ የግልጽነት ችግሮች በሚገባ ይጤኑ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ አስተያየት ሲሰጥ የቀረቡ የተለያዩ ድምፆች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ግጭትን ለማስቆም የሚያግዙ ድምፆች ትኩረት ካልተሰጣቸው፣ ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶች ዋጋ አልባ ይሆናሉ፡፡ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ሊደረግ የታሰቡ ውይይቶች ተስፋ የሚጣልባቸው፣ ከኃይል ይልቅ ወደ መነጋገሪያው ጠረጴዛ ለመምጣት የሚያስችሉ መደላድሎች ሲፈጠሩ ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መሣሪያ አንግበው የሚንቀሳቀሱም ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገራዊ ምክክሩ መድረክ ሲጠሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሰላም መስፈን እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ በጋራ አለመቆም ለኢትዮጵያ ህልውና ጠንቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጠመንጃ ላንቃ ተዘግቶ ሰላማዊ ንግግር እንዲጀመር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ችግር ባጋጠመ ቁጥር ወደ ኃይል ዕርምጃ መንደርደር አገር ለማፍረስ እንጂ፣ ለልማትም ሆነ ለዕድገት የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡  

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሚሆንባቸው ጊዜያት ውስጥ ሌላው ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ሕዝብን የሚያበሳጩ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ነው፡፡ ሕዝቡ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርና ደኅንነቱ የተረጋገጠ መሆኑን ማመን ይኖርበታል፡፡ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎችም ሆኑ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን፣ በአሁኑ ጊዜ የአገራቸው ሰላም ዕጦት በጣም ያሳስባቸዋል፡፡ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ባለመቻሉ ተብሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወጣ፣ ሒደቱ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ድርጊቶች እንዳይታዩበት ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ወዳዱ ሕዝብ የአገሩ ሰላምና ፀጥታ ሲረጋጋ ደስ የሚለውን ያህል፣ ግለሰቦች አላስፈላጊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ደግሞ ይከፋል፡፡ ከዚህ ቀደም ያስመረሩት ድርጊቶች ተወግደው በአገሩ በነፃነት መኖር ይፈልጋል፡፡ በአገሪቱ ሰላም ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመቀልበስ ሰላም ማስፈን ቅድሚያ ቢሰጠውም፣ አፈጻጸሙ ላይ ጥንቃቄ ካልተደረገ ሕዝብን የሚያበሳጩ ድርጊቶች መፈጸማቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የተለያዩ መረጃዎች ስለሚሠራጩ ሕዝቡን የሚያረጋጉና ካላስፈላጊ ጭንቀት የሚያወጡ ወቅታቸውን የጠበቁ መግለጫዎች በተከታታይ መውጣት አለባቸው፡፡

በሌላ በኩል ከአፈጻጸሙ ጋር ፈጽሞ መዘንጋት የሌለበት የተከሰተውን ግጭት ከማስቆም በተጨማሪ፣ ለሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ ጉዳይ ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙና የተቆላለፈው የፖለቲካ ምኅዳር እንዲከፈት፣ ብሔራዊ ውይይትና ድርድር የግድ መሆን አለበት፡፡ ሰላማዊ ውይይትና ድርድር በሠለጠነ መንገድ ሲካሄድ መፍትሔዎችን ለማመንጨትና የተሻለች አገር ለመገንባት ያግዛል፡፡ ከግጭት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ የሚቀርቡ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ይጠናከራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራትና የመሳሰሉት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ የተለያዩ ፍላጎቶችን የሚያማክል ሥርዓት መፍጠር ሲገባ፣ በአንድ አስተሳሰብ ብቻ የሚመራ ሥርዓተ መንግሥት ከሰላም ይልቅ ለጠብ የቀረበ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ሕዝብ ጥያቄ ሲያቀርብ ምላሽ የሚሰጥበት ሥርዓት ደካማ በመሆኑ፣ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ ሰላም ደፍርሷል፡፡ በርካቶች ሞተዋል፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል፣ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አደገኛ አረንቋ ውስጥ የሚያወጣ የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም እየራቃት በማያቋርጡ ግጭቶች ውስጥ ስትቆይና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ስትኖር፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በገጽታዋ ላይ የሚፈጠረው አሉታዊ ምሥል በእጅጉ ማሳሰብ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል እንዳልሆነች አሁን ሰላም ርቋት በተከታታይ ግጭቶች ምክንያት ስሟ እየጠለሸ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አደገኛ መንገድ ውስጥ ለመውጣት ዋነኛው መፍትሔ፣ በጨዋነትና በመከባበር ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ መፍጠር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዓውድ ሲኖር ጠመንጃ መነቅነቅም ሆነ በጉልበት እንፈታተን ማለት ነውር ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገቷን ቀና አድርጋ መራመድ ካስቻሏት ጉዳዮች መካከል አንደኛው፣ ከኮሪያ ልሳነ ምድር ጦርነት ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪነት በበርካታ አገሮች አንቱታን ያተረፈ አኩሪ ሥራ ማከናወኗ ነው፡፡ ለዓለም ሰላም ዘብ ለመቆም በግንባር ቀደምትነት ተሠልፋ ዕውቅና ያገኘች ኩሩ አገር፣ የውስጥ ሰላሟ ደፍርሶ በተደጋጋሚ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስትተዳደር ለምን መባል አለበት፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም የበለጠ ችግር ፈጣሪ እንዳይሆን ግልጽነት ይላበስ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...