Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአዲስ አበባ የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ የሚንከራተቱ ነዋሪዎች እንግልትና ቅሬታ

በአዲስ አበባ የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ የሚንከራተቱ ነዋሪዎች እንግልትና ቅሬታ

ቀን:

‹‹ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ሰዎችን የያዙና ያሰሩ የሕግ አስከባሪዎች ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል››

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምርያ ዕዝ

በአበበ ፍቅርና በኢዮብ ትኩዬ

በየካ ክፍለ ከተማ ደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ፊት ለፊት በርካታ እናቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች በስፋት ይታያሉ።

ትምህርት ቤቶቹ ሰሞኑን በአማራ ክልል ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የታሰሩባቸው እንደሆነ ቢገለጽም፣ ትክክለኛ ምክንያቱን የሚናገር ወይም የሚያውቅ ለማግኘት አዳጋች መሆኑ እየተገለጸ ነው። 

በየካ ክፍለ ከተማ ደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠገብ ተቀምጠው ሪፖርተር ያገኟቸው ወ/ሮ ሰዓዳ ሙሉጌታ ባለቤታቸውን ፍለጋ እንደመጡ ይናገራሉ። ‹‹ባለቤቴን ከሥራ ሲመጣ ነው አርሴማ ካራ አካባቢ የያዙት፡፡ ረቡዕ ማታ ጣቢያ ሄጄ አገኘሁትና ልብስ ሰጥቸው ተመለስኩ፡፡ ሐሙስ ጠዋት ስሄድ እዚያ የለም፣ ሾላ አካባቢ ነው ብለውኝ አራት ቀን በተደጋጋሚ ሄድኩኝ፡፡ የበላይ አካልም ተባለ ሂጄ ምንም ያገኘሁት መፍትሔ የለም፤›› ሲሉ ይናገራሉ።

ወ/ሮ ሰዓዳ የሁለት ልጆች እናት እንደሆኑና የሚተዳደሩትም ባለቤታቸው በሚያመጡት ገቢ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ‹‹የቀን ሥራ እየሠራ እርሱ ነበር የሚያስተዳድረን፣ አሁን ምንም ነገር የለንም፡፡ መጠጊያ፣ የምንበላው፣ የምንጠጣው የለንም፤››

ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ወንድይራድ ትምህርት ቤት በር ላይ ቁጭ ብለው ያገኘናቸው እኝህ እናት፣ ምን እየጠበቁ እንደሆነ ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ከትምህርት ቤቱ ግቢ ከሚወጡት ሰዎች ጋር ሲወጣ ካገኘሁት ብዬ ነው የምጠብቀው፤›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። ነገር ግን የታሰሩትን ሰዎች ለመጠበቅ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በር ላይ ከተመደቡት ፖሊሶች የተሰጣቸው ቀጠሮም ሆነ ምንም ዓይነት ምላሽ እንደሌለ ገልጸዋል።

‹‹አላስገቡንም፣ ከውጪ ነው የሚመልሱን። ስናናግራቸውም ‹እኛ ምንም የምናውቀው ነገር የለም› ነው የሚሉን ፖሊሶቹ። ባለቤቴ የት እንዳለ ሳልሰማና ሳላገኘው ይኸው ዛሬ ስድስት ቀኑ ነው፤›› ብለዋል።

ወ/ሮ አብዮት ዜጋ ይባላሉ፣ አቢቲ ተስፋዬ የተባለ ልጃቸው ታስሮባቸው ዓይኑን ለማየት ብለው ሰዎች በብዛት ታስረውበታል በተባለው ደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት ነው ያገኘናቸው።

ልጃቸው ከታሰረ 11ኛ ቀኑ መሆኑን የገለጹልን እኝህ እናት፣ ከታሰረ በኋላ ለተወሰኑ ቀናት አግኝተውት ምግብም እንዳቀረቡለት፣ አሁን ግን መግባት በመከልከሉ ካዩት አራት ቀናት እንዳለፋቸው ገልጸዋል።

‹‹ልጄ ጎበዝ ነው ይሠራል፣ አንድ ቀን የሰው እጅ ዓይቶ አያውቅም፣ ሠርቶ ሲመጣ እቤቱ እገባለሁ ሲል ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ወሰዱብኝ፡፡ ጣቢያ ድረስ ስፈልግ የለም፣ ዛሬ ነገ ይፈታል እያሉ ነበር፡፡››

ፖሊስ ልጃቸውን ያሰረው በምን ምክንያት እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት፣ ‹‹ምንም አላውቅም፡፡ ይፈታል ነው የሚሉን፣ ግን እግዚአብሔር ያውቃል እኛ አናውቅም፡፡ ግራ ገብቶን ነው ያለነው፣ ይኸው 11ኛ ቀን ነው ልጄን ካየሁት፤›› ብለዋል፡፡

ወ/ሮ አብዮት የታሰረው ልጃቸው ይፈታ ከሆነ ብለው ዘወትር ጠዋት ወደ ደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚመጡ ይናገራሉ። ‹‹ጠዋት አሥራ ሁለት ሰዓት ነው የመጣሁት፣ ከለቀቁት ብዬ እጠብቃለሁ፣ ግራ እንደገባኝ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ወደ ቤቴ እገባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ እናት ወ/ሮ አበበች ወርቅነህ ልጃቸው ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደታሰረ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹መድኃኔዓለም ሄደን አስቀድሰን አንደተመለስን እባክህ ቁርስ ብላ እያልኩት፣ ቆይ መጣሁ ብሎኝ እንደወጣ በዚያው ጠፋ፡፡ ስልክ ሲደወል ይጠራል ግን አይነሳም፣ ዓርብ ዕለት ዋልኩኝ፣ ጥሪ አይቀበልም ይላል፡፡ ቅዳሜ ዕለት ፍለጋ ሄድኩኝ መንገድ ላይ ሬሳውን ባገኘው ብዬ ስንከራተት፣ ስለፋ ሾላ ፖሊስ ጣቢያ ገባሁኝ የለም አሉኝ፣ አባረሩኝ፤›› ሲሉ የልጃቸውን ዱካ እስኪያገኙ ድረስ ያሳለፉትን ውጣ ውረድ አካፍለውናል።

በኋላ ላይ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት እንዲፈልጉ ተጠቁመው ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ እንደሄዱና በስተመጨረሻ ላይም ከኮተቤ አካባቢ ተጠርጥረው የተያዙ ቤተሰቦች እንዲገቡ ጥሪ ሲደረግ ወደ ግቢው እንደገቡና ልጃቸውን እንዳዩት ለሪፖርተር ገልጸዋል። 

‹‹ወደ ትምህርት ቤቱ ግቢ ገብቼ ልጄን አገኘሁት ነገር ግን በእጄ የያዝኩት 40 ብር ብቻ ነበር። በያዝኩት ገንዘብ አንድ ሊትር ውኃና ደረቅ እንጀራ ገዝቼ በፌስታል አድርጌ አቀበልኩት፤›› ሲሉ ወ/ሮ አበበች ተናግረዋል።

ልጃቸውን ቀድሞ ከነበረበት ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ኮተቤ አካባቢ ወደሚገኘው ሌላኛው ጊዜያዊ እስር ቤት (ደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት) ከተዘዋወረ በኋላ ለሦስት ቀናት ያህል እንዳገኙት፣ ከዚያ በኋላ ግን እንደተከለከሉ የገለጹት ወ/ሮ አበበች፣ ‹‹የቀን ሥራ እየሠራሁኝ ነው ያሳደኩት ልጄን›› ሲሉ እያለቀሱ ተናግረዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘ በርካታ ሰዎች እየታሰሩ ነው የሚባለው ሐሰት እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል። 

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ተጠርጣሪዎች 23 ብቻ መሆናቸውን የገለጸው ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ፣ የታሰሩትን ሰዎች ማንነትም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚሁ መግለጫውም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘ ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ሥልጣን የጠቅላይ መምሪያ ዕዙ እንደሆነና ከዚህ ውጪ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘ ሰዎችን የያዙ ሕግ አስከባሪ ተቋማት ካሉ አጣርቶ ዕርምጃ አንደሚወስድ ገልጾ ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ግን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‹‹የአማራ ተወላጆች›› የሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እንዲሁም ከኤርትራ የመጡ ሕገወጥ ስደተኞች ላይ እስራት በስፋት እየተፈጸመ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ከእስረኞች ቤተሰቦችና ወዳጆች በርካታ ጥቆማዎችና አቤቱታዎች እየተቀበለ መሆኑን፣ ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የእስር ሁኔታዎችን የመከታተል ዕድል እንዳላገኘ ገልጿል።

ኮሚሽኑ የፌዴራል መንግሥት እየተካሄደ ያለውን መጠነ ሰፊ እስራት እንዲያስቆምና ኮሚሽኑን ጨምሮ ሌሎች የቁጥጥርና ክትትል አካላት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በየጊዜው ወደ ማረሚያ ቤቶች ወይም ማቆያ ቦታዎች ገብተው ውጤታማ ክትትል እንዲያደርጉ እንዲፈቅድ ጠይቋል። በተጨማሪም፣ የፌዴራል መንግሥት ያለአግባብ በዘፈቀደ የተያዙትን ወይም የታሰሩትን በሙሉ እንዲፈታና የእስራቸው ሕጋዊነትም በተገቢውና ብቃት ባለው የፍትሕ አካል እንዲመረምር እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ሪፖርተር በተመለከታቸው የታሰሩ ሰዎች ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ከነበሩ የፖሊስ አካላት፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የእስሩን ምክንያት ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...