Sunday, October 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች አቋም ይይዙበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጉባዔ

የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች አቋም ይይዙበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጉባዔ

ቀን:

አፍሪካውያን ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ያላቸው አስተዋጽኦ ኢምንት ቢሆንም፣ በከፍተኛ ሁኔታ የችግሩ ተጋላጭና ተጎጂ ሆነዋል፡፡ ሆኖም ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰትና መባባስ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት በኢንዱስትሪና በኃይል የበለፀጉ አገሮች፣ የአፍሪካውያንን ችግር ከሥር መሠረቱ ለመፍታት የሚያደርጉት ዕገዛ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ከነሐሴ 8 እስከ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. እየተካሄደ ባለው በ19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባዔ፣ ሚኒስትሮች ውሳኔ ከማሳለፋቸው አስቀድሞ በተወያዩት የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች የተነሳውም፣ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰባት ያለውን ችግር ለመቋቋም ፈተና ውስጥ መሆኗ ነው፡፡

ነሐሴ 12 ቀን ከሚመክሩት የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች አስቀድሞ፣ ነሐሴ 8 ቀን በስካይላይት ሆቴል ውይይት ያደረጉት የአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች፣ አፍሪካውያን በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በመሬት መንሸራተትና በሌሎችም የተፈጥሮ መዛባት አደጋዎች እየተጎዱ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የአፍሪካ ብዝኃ ሕይወት እየተጎዳና አኅጉሪቱ የተለየ ፈተና እየገጠማት መሆኑን በመግለጽም፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከዓለም አቀፍ ዕርዳታ ከሚገኘው በተጨማሪ የውስጥ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

 በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገችው አፍሪካ የታዳሽ ኃይል አቅሟ ዓለም በ2040 ያስፈልገዋል ተብሎ ከተቀመጠው የኤሌክትሪክ ኃይል 50 እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ‹‹ጀስት ትራንዚሽን፣ ኤ ክላይሜት፣ ኢነርጂ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ቪዥን ፎር አፍሪካ›› ሪፖርት ላይ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ አስፍረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፣ አኅጉሪቷ ለባትሪና ሐይድሮጅን ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ከ40 በመቶ በላይ መጠባበቂያ ቁልፍ ሚኒራሎችም አሏት፡፡

አኅጉሪቷ ሰፊ የሚታረስ መሬትና ወጣት የሰው ኃይል ቢኖራትም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተጋረጠባት ያለው ፈተና አኅጉሪቷን ለአየር ንብረት ለውጥ ካላት አስተዋጽኦ ባልተመጣጠነ መልኩ እየጎዳት ነው፡፡

‹‹የአፍሪካ የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት ዕድሎችን መጠቀም፣ ትብብርን ማጎልበት›› በሚል ጭብጥ እየተካሄደ ባለው ጉባዔም፣ አፍሪካ እየተፈተነችበት ካለው የአየር ንብረት ለውጥ ለመውጣትና ችግሮችን ተቋቁማ ለመኖር፣ ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ወጥ አቋም ይይዙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጉባዔውን አስመልክተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ከጉባዔው በመጪው መስከረም ለሚደረገው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ግብዓት ማሰባሰብና የጋራ አቋም መያዝ ይጠበቃል፡፡

ለ28ኛው የኮፕ (ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ) ለአየር ንብረት ለውጥና በቀጣይ ለሚኖረው በረሃማነትን የመከላከል ጉባዔ ግብዓት ማግኘትም ከጉባዔው የሚጠበቅ ነው፡፡  የኬሚካልን ወይም ኬሚካሎችንና ጎጂ ቆሻሻዎችን ማስወገድ ላይ ለሚደረገው ጉባዔም ከአፍሪካውያን የአካባቢ ሚኒስትሮች የጋራ አቋም ይጠበቃል፡፡

ብዝኃ ሕይወት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የፕላስቲክ አወጋገድና ሌሎችን በተመለከተም ምክክር የሚደረግበትና አቋም የሚያዝበት ነው፡፡

በተለይ የፕላስቲክ ቆሻሻን በተመለከተ፣ ዓለም አቀፍ አስገዳጅ ሕግ እንዲወጣ በአምስተኛ ዓለም አቀፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካባቢ ሸንጎ መወሰኑን ተከትሎ፣ ከሚደረጉት አራት ጉባዔዎች ሁለቱ መካሄዳቸውን፣ ለሦስተኛውና ለአራተኛው መግባባት እንዲቻል አፍሪካውያን የጋራ አቋም የሚይዙበት እንደሆነም ጌታሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘ አፍሪካ የችግሩ አመንጪ ባትሆንም፣ ተጠቂ በመሆን እየተቸገረች ነው ያሉት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ ብዙ ጊዜ በኮፕም ሆነ በሌሎች የአካባቢ ጉባዔዎች ውሳኔዎች ቢወሰኑም፣ ቃሎች ቢገቡም ተግባራዊ የመሆን ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም እየተካሄደ ባለው 19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባዔ በኮፕ የተወሰኑ ውሳኔዎች እንዲተገበሩ አቋም የሚያዝበት ይሆናል፡፡

ለአየር ንብረት ለውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው የበለፀጉ አገሮች፣ አፍሪካ ችግሩን እንድትቋቋም ገንዘብ ፈሰስ እንደሚያደርጉ በየጊዜው በተደረጉ ጉባዔዎች ተናግረዋል፡፡ ሆኖም  ተግባራዊ አያደርጉም፡፡

ይህም በ27ኛው የኮፕ ጉባዔ ዋና ችግር ሆኖ ተነስቷል፡፡ ችግሩን ተቋቁሞ ለመኖር የሚያስችል ገንዘብ ማግኘትም ለአፍሪካ አጀንዳ መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ቃል ከሚገባው ገንዘብ 50 በመቶ ያህሉ ችግሩን ተቋቁሞ ለማለፊያ እንዲሆንና ቃል የተገቡ ገንዘቦች መሬት እንዲወርዱም በተደጋጋሚ ተጠይቋል፡፡ እየተካሄደ ባለው ጉባዔም ይህ ከመሬት እንዲወርድ አቋም የሚያዝበት ይሆናል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ከዚህ በፊት እንደነበረው የፖለቲካና የንግግር መሆኑ ቀርቶ የልማት አጀንዳ ነው ያሉት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ቀደም ብላ በመገኘት የአየር ንብረት ለውጥን በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሥር ማድረጓንና ሁሉም የልማት ሥራዎች ውስጥ ገብቶ እንዲከናወን መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

የአፍሪካ ሲቪክ ማኅበራትና የባለድርሻ አካላትም ከሚኒስትሮች ጉባዔ አስቀድመው የመከሩ ሲሆን፣ በዚህም በአፍሪካ የአካባቢ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የጋራ አኅጉራዊ ፖሊሲ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ለአካባቢያዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል አኅጉራዊ ትብብር እንደሚያስፈልግና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ የመጡትን አካባቢያዊ ተግዳሮቶች ለመቀልበስ ሲቪል ማኅበራት ስለሚኖራቸው አበርክቶም መክረዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝኃ ሕይወት መመናመን፣ የአካባቢ ብክለትና ብክነት፣ የአፈር ለምነት መቀነስ እንዲሁም ሌሎች አካባቢያዊ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ የሲቪክ ማኅበራቱና ባለድርሻዎች የበኩላቸውን ለመሥራት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...