- እና ሕዝቡ ሥራችንን አልወደደውም እያልክ ነው?
- እኔ ባሰባሰብኩት መረጃ ያስተዋልኩት እንደዛ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- እስኪ ምሳሌ ጠቅሰህ አስረዳኝ? ምን ዓይነት ትችት ነው የሚቀርበው? ምን እየተባለ ነው?
- መንግሥት የነዋሪውን የመኖሪያ ቤት ችግር ይፈታል ሲባል የቀበሌ ቤት ጣሪያ ይጠግናል እየተባለ ነው።
- እንዴት? ድሆች በክረምት ወቅት እንደሚቸገሩ መንግሥት እያወቀ ዝም ብሎ ማየት ነበረበት?
- እንደዚያ ለማለት ተፈልጎ አልመሰለኝም።
- እና ምን ለማለት ተፈልጎ ነው የሚመስልህ?
- መንግሥት ትናንሽ ጉዳዮችን ለማኅበረሰቡ ትቶ በሚመለከተው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኩር ለማለት ይመስለኛል።
- እሺ ሌላስ ምን ይባላል?
- መንግሥት ከሚሠራው ይልቅ ታይታ ላይ ያተኩራል ይባላል።
- ምን ማለት ነው?
- የመንግሥት ፕሮጀክቶች ለማኅበረሰቡ ካስገኙት ፋይዳ ይልቅ ባለሥልጣናት ያገኙት ይበልጣል ይባላል።
- ባለሥልጣናት ምን አገኙ?
- ባለሥልጣናት ሥራ የሠሩ መስለው ታይተውባቸዋል ይባላል፡፡
- እንዴት?
- ደጋግመው በመጎብኘት እና…
- እና… ምን?
- በማስጎብኘት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲደርሱ ባለቤታቸው የሞባይል ስልካቸውን አቀርቅረው እየተመለከቱ አገኟቸው]
- ምን ሆነሽ ነው?
- ደህና ነኝ፣ ምንም አልሆንኩም።
- ታዲያ ለምን አቀረቀርሽ?
- እ… የዩቲዩብ መረጃዎችን እየተመለከትኩ ነው።
- እንዴት የሚኒስትር ባለቤት ሆነሽ ዩቲዩብ ትመለከቻለሽ?
- እናንተማ በአገራችን ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ልትነግሩን አልቻላችሁም።
- እና የዩቲዩብ መረጃ ነው የሚነግርሽ?
- የተጋነነ ቢሆንም እሱ ይሻላል።
- ፍፁም ተሳስተሻል።
- ለምሳሌ ለውጡ አደጋ ላይ መሆኑን እናንተ ነግራችሁን ታውቃላችሁ?
- ይኸው…?
- ምን?
- ማን ነው ለውጡ አደጋ ላይ ነው ያለው። አደጋ ላይ ስለመሆኑ ምንድነው ማሳያው?
- ከፓርቲ ለቀው እየሄዱ፣ ከአገር እየወጡ ነዋ።
- እነማን?
- የለውጡን ፍኖተ ካርታ የነደፉት ናቸዋ?
- እነሱ እነ ማን ናቸው?
- ምን እንደማታውቅ ትሆናለህ?
- የእውነት አላውቅም። እነማን ናቸው? ወዴት ወጡ?
- አንደኛው ኦሮሞ ናቸው።
- እሺ?
- እሳቸው ከወጡ ቆይተዋል።
- እሺ ሌላኛውስ?
- ሌላኛው አማራ ናቸው።
- እሺ?
- እሳቸውም ሰሞኑን በፓርላማ ያደረጉት ንግግር እየለቀቁ መሆኑን ያሳያል።
- እሺ እነዚህ ናቸው?
- ሌላም አሉ።
- ሌላኛው ደግሞ ማን ናቸው?
- ሌላኛው ደግሞ እንግሊዛዊ ናቸው።
- እንግሊዛዊ?
- አዎ፡፡
- ማን ናቸው?
- አልሰማሁም እንዳይሆን ብቻ?
- የእውነት አልሰማሁም፣ ማን ናቸው?
- ሰሞኑን በቃኝ ብለው ከአገር መውጣታቸውን፣ ወደ እንግሊዝ መመላሳቸውን ይፋ ያደረጉት ናቸዋ።
- እ… እሱን ነው እንዴ?
- ታዲያ ማን ቀረ? የለውጡን ፍኖተ ካርታ የነደፉት እነዚህ አይደሉም።
- ይላሉ።
- ይላሉ ማለት?
- ያው እነሱ ይላሉ ማለቴ ነው።
- ይላሉ እንጂ እነሱ አይደለም የቀረፁት ማለትህ ነው።
- ምኑን?
- ለውጡን ነዋ።
- እስኪ ተይኝ።
- እንዴት? ለምን?
- ስለዚህ ነገር ማንም የሚያውቅ የለም።
- ማንም የሚያውቅ ስትል ምን ማለትህ ነው?
- ምን እንደሆነ የሚያውቅ የለም ማለቴ ነው።
- ምኑ?
- ለውጡ፡፡
- እኮ ይኸው?
- ምን?
- ለውጡ ምን እንደሆነ የሚያውቅ የለም አልክ።
- እና ብልስ?
- ለውጡ ምን እንደሆነ ማንም ሊያውቅ ያልቻለው ለምን እንደሆነ ግልጽ ነዋ?
- ለምንድነው?
- ይዘውት ሄደው ነዋ?
- ምኑን?
- ፍኖተ ካርታውን!