Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከመስከረም መጨረሻ ጀምሮ ሊሰጥ ነው

በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከመስከረም መጨረሻ ጀምሮ ሊሰጥ ነው

ቀን:

በዳንኤል ንጉሤ

በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ፈተና በአራት የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በአክሱም፣ መቀሌ፣ አዲግራትና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚሰጥ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ኪሮስ ጉዑሽ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከመጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ ናቸው፡፡ ‹‹ወረርሽኙን እየተከላከልን መማርና ማስተማር ይቀጥል በሚል ዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት፣ በትግራይ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት አራት ዓመት ሳይፈተኑ ቆይተዋል፤›› ብለዋል። አክለውም ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታቸው መራቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት አደጋ ከደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ እንደነበሩም ጠቁመዋል።

የፕሪቶሪያውን ስምምነት መነሻ በማድረግ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት እንዲጀመር በወሰነው ውሳኔ መሠረት፣  ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ ለተከታታይ አምስት ወራት በተወሰነ ደረጃ ትምህርት መሰጠቱን ኃላፊው ገልጸው፣ የፈተናዎች ኤጀንሲ ከመስከረም 29 ቀን ጀምሮ ለአራት ቀናት ፈተናው እንደሚሰጥ ማሳወቁን አስረድተዋል፡፡

የአሁኖቹ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀው እንደ መቆየታቸው መጠን  የክልሉ ትምህርት ቢሮ የተቻለውን ድጋፍ እያደረገላቸው ቢሆንም ፣ ነገር ግን በክልሉ ካጋጠመው ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ በተጨማሪ፣ በቂ የትምህርት መገልገያ ቁሳቁስና በቂ መምህራን ባለመኖራቸው ምክንያት፣ ማግኘት የሚገባቸውን ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

‹‹የትግራይ ትምህርት ቢሮ በተማሪዎችና በቤተሰቦቻቸው ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ፣ ተማሪዎችን ከነሐሴ 1 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ለአንድ ወር ያህል የሚፈተኑባቸው አራት ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፤›› ያሉት አቶ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ ይህም የተደረገበትን ምክንያት ሲያብራሩ ተፈታኝ ተማሪዎች በቂ መጻሕፍት፣ የኤሌክትሪክና የምግብ አቅርቦት እንዲያገኙ ታስቦ ነው ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር በ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በተለየ ጊዜ መርሐ ግብር ፈተና ለማዘጋጀት ፈቃደኛ መሆኑን ኪሮስ (ዶ/ር) ገልጸው፣ ነገር ግን ተማሪዎቹ ብቁ እንዲሆኑ ከመጻሕፍት ጀምሮ የቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነና ለተፈታኞቹ ወጪ እያደረገ ያለው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሆነ ጠቁመዋል።

‹‹የፈተናዎች ኤጀንሲ የተማሪዎቹን ፈተና በተለየ ርብርብ በፍጥነት አርሞ ውጤታቸውን እንደሚያሳውቅ ነግሮናል፤›› ብለው፣ ይህም የዩኒቨርሲቲ ድልድል እንዳይጓተትባቸው ይረዳቸዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹በትግራይ በትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ውድመቱ በትግራይ ሕዝብ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩና በፌዴራል መንግሥት ብቻ የሚፈጸም ባለመሆኑ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና አቅም ያለው ሁሉ በሚደረገው መልሶ ግንባታና ተማሪዎችን ለማብቃት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...