Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በወር እስከ 1,000 ብር የሚከፈላቸው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች ኑሮውን መቋቋም አቅቶናል አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ ካሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኩባንያዎችና ሠራተኞችን የያዘው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች ሲያቀርቡ የነበረው የደመወዝ ማስተካከያ ጥያቄ፣ አሁንም ምላሽ ሊያገኝ እንዳልቻለ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ለየትኛውም አገልግሎት ዘርፍ ሲከፈል የማይታይና እጅግ ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈልበት ነው የተባለው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ሠራተኞች፣ በኢትዮጵያ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን በኩል ሳይቀር ቢያቀርቡም፣ ሰሚ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሠራተኞች አመልክተዋል፡፡

የኢንዱትሪ ፓርኩ አብዛኛዎቹ ሠራተኞች በወር እስከ አንድ ሺሕ ብር ደመወዝ የሚከፈላቸው ሲሆን፣ በዚህ ደመወዝ ለዓመታት በመቆየታቸው ኑሯቸውን በእጅጉ እንዳከበደባቸውም ተናግረዋል፡፡ በወር 750 ብር ይከፍሉ የነበሩ ኩባንያዎች እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የሠራተኞች ማኅበራት ካቋቋሙ የማኅበር መሪዎች መረዳት እንደተቻለውም፣ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄውን ለአሠሪዎቻቸው ቢያቀርቡም፣ ምንም ዓይነት አዎንታዊ ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ያለውን ጥያቄ ማንሳት ከሥራ የሚያስባርር መሆኑን በምሬት ገልጸዋል፡፡ በተለይ ጥያቄውን የሚያነሱ የሠራተኞች መሪዎች በተለያዩ መንገዶች ከሥራ እንዲለቁ ሲደረግ መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡ አንዳንድ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች፣ የሠራተኛ ተወካዮችን ደመወዝ በመጨመርና በተለያዩ ማባበያዎች ዕድገት በመስጠት ጭምር የሠራተኛው ድምፅ እንዲዳፈን እያደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

አንድ ሠራተኛ በወር እስከ አንድ ሺሕ ብር እየተከፈለው መሆኑና መንግሥትም ይህንኑ እያወቀ ዕርምት እንዲወሰድ ያለመደረጉ እንዳሳዘናቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማኅበር መሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከደመወዝ ጥያቄው ባሻገር የተለያዩ የመብት ጥሰቶችም የሚፈጸም መሆኑንም አክለዋል፡፡

በዚህ አነስተኛ ደመወዝ ክፍያ ዙሪያ እየተነሳ ያለውን ጥያቄ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንቨስተሮች ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሽመልስ ነጋ፣ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ የሚነሳ ጥያቄ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ጥያቄው ሳያቋርጥ መቀጠሉንም አስታውሰዋል፡፡ ደመወዙ አንሷል የሚለውም ነገር እነሱም የሚቀበሉት ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ከእነሱ አቅም በላይ ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት ግን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ምጣኔን ለመወሰን ሊወጣ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው ሕግ ችግሩን ሊፈታው ይችላል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ሽመልስ፣ ጉዳዩም እስከ ተወካዮች ምክር ቤት የደረሰ በመሆኑ፣ በዚያ የሚሰጠው ውሳኔ ችግሩን ሊፈታ ይችላል ብለው እንደሚምኑ፣ ይኼው የመጨረሻ ውሳኔም እየተጠበቀ እንደሆነ ከገለጻው ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹በአንፃሩ ግን ከባዶ አንድ ይሻሻል፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ያለ ሥራ ቤት ተቀምጠው የነበሩ በተለይም ሴት እህቶቻችን የዚህ ፓርክ መከፈት ሥራ ለማግኘት እንዳስቻላቸው መታሰብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ሥራ እየለመዱም በመሆኑ፣ ደመወዙ አነስተኛ ነው ቢባልም የሥራ ዕድል መፈጠሩ በራሱ እንደ መልካም ዕድል መታየት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ሌላ እነዚህ ሠራተኞች  ከደመወዛቸው ሌላ ተጨማሪ ክፍያዎችን የሚያገኙበት ዕድል አለም ይላሉ፡፡ ብዙዎቹ ኩባንያዎች በተለያዩ መንገዶች ለሠራተኛ ተጨማሪ ክፍያ የሚያገኙበት አሠራር ስለዘረጉ፣ ክፍያቸው አነስተኛ ሊባል የማይችል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ያነሱትም የትራንስፖርትና የምግብ አበል ስላላቸው፣ ይህ ሲደማመር የሚያገኙትን ገቢ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ከኑሮ ውድነት አንፃር ግን ሲታይ ግን የሚያንስ መሆኑን አቶ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩቸው፣ ችግሩ ያለው በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ነው ብለዋል፡፡ ኢሰማኮ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አጥብቆ እየወተወተበት ያለው አንዱ ምክንያት ይሄ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለው የደመወዝ ክፍያ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚሀ የኑሮ ውድነትን የሚመጥን ደመወዝ ቢያንስ ዝቅተኛ ወለል እንዲበጅለት የምንሻ በመሆኑ፣ በአስቸኳይ ተፈጻሚ እንዲሆን አሁንም ግፊት እየተደረገ መሆኑን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት በኩልም አንዳንድ ተስፋ ሰጪ ነገሮችን እያዩ በመሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ጉዳዩ ዕልባት እንዲያገኝ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ማስቀመጥ ለሠራተኛው ብቻ ሳይሆን ለአገርም ጠቃሚ መሆኑን ያስረዱት አቶ ካሳሁን፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አገሮች ዝቅተኛ ‹‹የደመወዝ ወለል ሕግ ከሌለው አገር የሚመጡ ምርቶችን አንገዛም›› እያሉ በመሆኑ ይህም ጉዳይ አብሮ ሊታሰብበት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ካሉት 52 ሼዶች ውስጥ ሥራ ላይ የሚገኙት 22 ሼዶች ናቸው፡፡ በዋናነት የጨርቃ ጨርቅና የጋርመንት ሥራዎች ላይ ያተኮረው ይህ ኢንዱስትሪ፣ ባንክ ከያዛቸው 22 ኩባንያዎች ውስጥ አራቱ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት 30 ሺሕ ሠራተኞች የያዘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚ በነበረችበት ወቅት እስከ 35 ሺሕ ሠራተኞችን የያዘ ነበር፡፡ ፓርኩ 140 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ አጠቃላይ ይዞታው ግን ሦስት ሺሕ ሔክታር ነው፡፡ ከካልሲ እስከ ሱፍ ልብሶች የሚመረትበት ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ የጀመረው እ.ኤ.አ. ጥር 2017 ነው፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች