ጊዜው ራቅ ቢልም አሁን ካለንበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ገጠመኝ አለኝ፡፡ እኔና ወንድሜ የሁለተኛ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታችንን አጠናቀን ዘመዶቻችን ዘንድ ክረምቱን ለማሳለፍ ወደ ድሬዳዋ ለመሄድ ዕቅድ ነበረን፡፡ ጊዜው ደግሞ አፍላው የአብዮት ወቅት 1969 ዓ.ም. ነው፡፡ ድሬዳዋ ለመሄድ እየተዘጋጀን ሳለ የሶማሊያ ወራሪ ጦር ገፍቶ ድሬዳዋና ሐረር በመቃረቡ፣ የታሰበው ጉዞ ተቋርጦ እዚሁ አዲስ አበባ ለመቆየት ተገደድን፡፡ በምሥራቅ የሶማሊያ ወራሪ ጦር፣ በኤርትራ ሻዕቢያ፣ በመሀል አገር ኢሕአፓ በቀጥታና በሽምቅ በከፈቱት ውጊያ ምክንያት ኢትዮጵያ ፈተና ውስጥ ገባች፡፡ እንደ እኛ ያሉ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ፣ በኢሕአፓ አባልነት ወይም ደጋፊነት እየታደንን ነው፡፡ በወቅቱ ወጣት መሆን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያስመታ ከባድ ፈተና ነበረ፡፡
እናታችን እኔም ሆንኩ ወንድሜ እንዲሁም እህቶቻችን ከቤት እንዳንወጣ ጥብቅ ማሳሰቢያ በመስጠት ተሳስረን ተቀመጥን፡፡ ሰሜን ጦር ግንባር ያለው አባታችን በየቀኑ ስልክ እየደወለ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድናደርግ ወታደራዊ ትዕዛዝ ይሰጠናል፡፡ የሐረር ጦር አካዴሚ ምሩቅ የነበረው በጊዜው ሻለቃ የነበረው አባታችን፣ በወቅቱ በኤርትራ ክፍለ ሀገር አስመራ ከተማ የዕዙ ዘመቻ መኮንን ሆኖ ያገለግል ስለነበር የስልክ ክትትሉ ከባድ ነበር፡፡ እኛ ልጆቹ ከትምህርታችን በስተቀር የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል እንዳንሆን ያስጠነቅቀን ስለነበር፣ እኛም በአባልነት የተመለመልንበት ድርጅት ባይኖርም ኢሕአፓን በስሜት እንደግፍ ነበር፡፡
አንድ ቀን ብዛት ያላቸው የታጠቁ ሰዎች አሰሳ ለማድረግ ወጥተው ሠፈራችንን እንደ ሰፌድ እያንቀረቀቡ እየፈተሹ እኛ ቤት ሲደርሱ፣ ቤቱ የማን እንደሆነ ከደጅ ሲነገራቸው በመጡበት ፍጥነት ተግተልትለው መመለሳቸውን በዋናው በር ቀዳዳ አሾልኬ ካየሁ በኋላ መፍራት ጀመርኩ፡፡ ወንድሜ ግን በአንድ ዓመት የምበልጠው ቢሆንም ድፍረቱ ከሚታሰበው በላይ ነበር፡፡ አንድ ቀን፣ ‹‹እኛ እዚህ እንደ ፈሪ ቤት ውስጥ ተቀርቅረን ጓደኞቻችን ስንት ታሪክ ሲሠሩ አናሳፍርም ወይ…›› ብሎኝ አደፋፍሮኝ ወጥተን አራዳ ጊዮርጊስ ዶሮ ማነቂያ ውስጥ ድል አድራጊው የሚባል ካፌ በራድ ሻይ እየጠጣን ሙዚቃ ስናጣጥም፣ ድንገት በጥቆማ በመጡ ብዛት ያላቸው የደኅንነትና የአብዮት ጠባቂዎች ተይዘን ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድን፡፡
እዚያ ካፌ ውስጥ ከእኛ ጋር ከሃምሳ የሚበልጡ ወጣቶች የነበሩ ሲሆን፣ ከእኛ በስተቀር ብዙዎቹ የሚተዋወቁ እንደነበሩ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሲሰጣጡ አይቻለሁ፡፡ እኔና ወንድሜ ግን ለአካባቢውም ሆነ ለወጣቶቹ እንግዳ ስለነበርን በምን ምክንያት አፈሳው እንደተካሄደ ለጊዜው አልገባንም ነበር፡፡ ሦስተኛ ደርሰን ወደ ማዕከላዊ ተላልፈን ሜዳው ላይ በዱላ የታጀበ ማጋለጥ እንዲካሄድ ሲነገረን፣ ባልሳሳት አምስት ያህል ወጣቶች ወደፊት ወጥተው መፈክር ማሰማት ሲጀምሩ ግራ ገባን፡፡ ‹‹ፋሽስቱ ደርግ ይውደም፣ ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ፣ ኢሕአፓ ለዘለዓለም ይኑር…›› እያሉ በኅብረት ሲያስተጋቡ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ደነገጥኩ፡፡
አምስቱ ተለይተው በጠመንጃ ሰደፍ እየተቀጠቀጡና የወይራ ክትክታ በሚመስል ዱላ እየተዠለጡ ወደ ሌላ ቦታ ሲወሰዱ፣ የተቀረነው በአንዴ ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ጠረንገሎ ወታደሮች በቦክስ፣ በጫማ ጥፊና በአጫጭር ዱላዎች መሬት ለመሬት እያንከባለሉ ለግማሽ ሰዓት ያህል አቅላችንን እስክንስት ነረቱን፡፡ ወንድሜ ከአፉና ከአፍንጫው ከሚዝረበረበው ደም በተጨማሪ በአንዴ ፊቱ አባብጦ ሌላ ሰው መስሏል፡፡ እኔም ራሴን ባላየውም ልክ እንደ እሱ ሆኛለሁ፡፡ ያ ሁሉ ውርጅብኝ ካበቃ በኋላ በሰዎች የተፋፈገ አንድ ክፍል ውስጥ አስገብተው ቆለፉብን፡፡
እዚያ ክፍል ውስጥ ከታዳጊ እስከ አዛውንት በደረሰባቸው የግፍ ዱላ የሚያነክሱ፣ የሚንፏቀቁ፣ መንቀሳቀስ አቅቷቸው ግድግዳ ተደግፈው የተቀመጡ ወይም በሰው ድጋፍ ጋደም ያሉ፣ ውስጥ እግራቸው በግርፋት የነፈረ፣ ጥርሳቸው የወለቀ፣ አፋቸውና አፍንጫቸው የተጣመመ፣ ዓይናቸው በጥቁረት የበለዘና በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከደረሰብን የጅምላ ድብደባ በኋላ የማሰቃያ ክፍል ውስጥ ገና በማንጠልጠያ ቶርች እንደምንደረግ ተነግሮን የሥነ ልቦና ዝግጅት እንድናደርግ ወዲያው ነበር ማሳሰቢያ የተሰጠን፡፡ ወንድሜን ስለአባታችን ማንነት ተናግረን ከዚህ ቦታ ነፃ ካልወጣን እንዳለቀልን ስነግረው፣ ‹‹በል የአባታችንን ስም አንስተህ ሌላ ጣጣ እንዳታመጣብን…›› ብሎኝ ዝም እንድል ማስጠንቀቂያ ሰጠኝ፡፡
በየተራ እየተወሰድን የተባለው ማሰቃያ ሲጀመር ከማንም በፊት ቀድሜ የሄድኩት እኔ ነበርኩ፡፡ በሕይወቴ እንደዚያ የሚያስጠላ በሰዎች ደም የተጨማለቀ ቦታ ዓይቼ ስለማላውቅ ሥቃዩ ከመጀመሩ በፊት ለገራፊው፣ ‹‹እኔ እኮ የሻለቃ… ልጅ ነኝ፣ ከወንድሜ ጋር ሻይ እየጠጣን ሙዚቃ ስናዳምጥ ነው ተይዘን የመጣነው…›› ብዬ መናገር ስጀምር ከኋላዬ ምንነቱን በማላውቀው ነገር ተመትቼ በአፍንጫዬ ተደፋሁ፡፡ ከስንት ጊዜ በኋላ እንደሆነ አላውቅም ስነቃ ልብሴ በውኃ ርሶ መሬት ላይ ተዘርግቻለሁ፡፡
ሁለት ሰዎች መንቃቴን አረጋግጠው እየጎተቱ ወስደው መስቀያው ላይ ሲያወጡኝ ሦስተኛው ሰው ደገፍ አድርጎ ገለበጠኝ፡፡ ከዚያ በኋላማ መፈጠሬን እስክጠላ ድረስ በደም የራሰ የሚተነፍግ ካልሲ አፌ ውስጥ ገብቶ እግሮቼ የተቆረጡ እስኪመስሉ ድረስ ተደበደብኩ፡፡ የማላውቃቸው ሰዎች ስም እየተጠሩ በማላውቀው ጉዳይ የጎን አጥንቴ እስኪሰበር ተሰቃየሁ፡፡ ከዚያ የማሰቃያ ነገር ወርጄ መቼ መታጎሪያችን እንደገባሁ ሳላውቅ፣ በወንድሜና በሌሎች ወጣቶች በቫዝሊን እየታሸሁ ነቃሁ፡፡ ወንድሜ እንደ በፊቱ ቀጥ ብሎ ሳይሆን የሚራመደው አጎንብሶ ስለነበር እሱም እንደ እኔ ተሰቃይቶ ነበር፡፡
ማዕከላዊ ከእኛ በላይ የተሰቃዩ ወንዶችና ሴቶችን ዓይቻለሁ፡፡ ለመግለጽ የሚያዳግቱ ብርቱ መከራ የደረሰባቸው ታዳጊዎችና አዛውንቶችም ነበሩ፡፡ እኔና ወንድሜ ከስድስት ወራት በኋላ በከባድ ማስጠንቀቂያ ብንለቀቅም፣ የእዚያ ቤት መከራ ግን እስካሁን በህሊናዬ ውስጥ አለ፡፡ በማዕከላዊ ቆይታችን የተገነዘብኩት በቀላሉ በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ልዩነቶች የአንድ አገር ልጆችን ማጋደላቸውና ደም ማቃባታቸው ነበር፡፡ አንድ ሙስሊም አባት፣ ‹‹ልጆች በፅሞና መነጋገር ቢቻል እኮ ይህ ሁሉ መከራ አይደርስብንም ነበር…›› ሲሉ እሰማቸው ነበር፡፡ ከስንትና ስንት ዓመታት በኋላ በፅሞና መነጋገር አቅቶ ጦር ሰብቀን ስንፋጅ ድንቅ ይለኛል፡፡ ይህ ነገር እርግማን ይሆን ወይ እያልኩ ሰዎችን ብጠይቅ መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የሆነስ ሆነና ምን ይሻለናል? ወገኖቼ በፅሞና ለመነጋገር ስክነት አያሻን ይሆን?
(ህዝቅኤል ዮሐንስ፣ ከሰሚት)