Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉመንግሥት ለሰላም ሲል ራሱን ይጠይቅ!

መንግሥት ለሰላም ሲል ራሱን ይጠይቅ!

ቀን:

በአያሌው አስረስ 

አሁን ሳስበው እጅግ ከፍተኛ ስህተት እንደነበረ ካመንኩበት ጉዳይ ልጀምር፡፡ ጉጀሌ ስብሐት (ትሕነግ) እንደፈለገ የሚያሽከረክረው ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ፣ ከክልሉ ውጪ በሚኖረው አማራ ላይ ተከታታይ ጥቃት ተከፈተ፡፡ ጎልቶ የታየው የአርሲው፣ የአርባ ጉጉውና በሐረር ክፍለ አገር የበደኖው ነበር፡፡ በአማራ ክልል፣ የክልሉን የመንግሥት ሥልጣን ይዘው የሚገኙት የኢሕዴን (የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን) አባላት በየቦታው በሚገኘው አማራ ላይ የሚያደርሰው ጥቃት የሚያሳስባቸውና የሚያስጨንቃቸው ሆኖ አልተገኘም፡፡ አማራው የሚጮህለት በማጣቱ በ1984 ዓ.ም. ላይ የመላ አማራ ሕዝብ ድርጅት (መኢአድ) ተቋቋመ፡፡ የመኢአድን መመሥረትና ለአማራው ድምፅ ሆኖ መቆም ያየው ኢሕአዴግ ኢሕድንን ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በሚል ስም እንዲጠራና በኢሕአዴግ መንግሥት የአማራ ሕዝብ ተወካይ ነኝ ብሎ እንዲቀርብ አደረገ፡፡

አሁን በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለአማራ ቁመናል የሚሉ ሁለት ድርጅቶች ጎን ለጎን ተገኙ፡፡ ይሁን እንጂ በአማራው ላይ የሚደረገው ጥቃት ቢጨምር እንጂ ሊቀንስ አልቻለም፡፡ አማራ ነን ካላችሁ ለምን አማራው ሲጠቃ ዝም ብላችሁ ታያላችሁ? ስለምንስ በአማራው ጥቃት ላይ ተባባሪ ሆናችሁ ትገኛላችሁ? የሚል ጥያቄ ወደ ብአዴን አባላት መሰንዘር ጀመረ፡፡

አበው ‹‹የፍየል ጅራት እፍረት አይከልል ዝንብ አይከለክል›› ይላሉ፡፡ አማራ ነን ብለው በአማራው ስም የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉት ክፍሎች፣ ለአማራው በጎ የሚባል ነገር ባለማሠራታቸው እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ሰዎችን ‹‹ሆዳም አማራ›› የሚል ስም የመኢአድ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ አወጡላቸው፡፡ ‹‹ሆዳም አማራ›› የሚለውን ቃል የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ምናልባትም በአጠቃላይ ሕዝቡ ተቀባበለው፡፡ የብአዴን አባላት ማግለሉ፣ ማጥላላቱ፣ ማሸማቀቁ፣ የበዛ ሆነ፡፡

በዚህ ምክንያት የኦሮሞ የፖለቲካ ሰዎች ምርኮኛ የሚሉትን የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ውስጥ በመግባት የኦነግን አጀንዳ በግልጽም በሥውርም እንዲሸከም እንዳደረጉ ሁሉ፣ በብአዴን ውስጥ የመአሕድን (በኋላ መኢአድ) አጀንዳ ለማስፈጸም የሚያስችል አሠራር ሳይፈጠር ቀረ፡፡ አንዳንድ የብአዴን አባላት በግል ተነሳሽነት በውስጥ ያደረጉት ድርጅታዊ ትግል ከውጭ ድጋፍ እያጣ በተደጋጋሚ እንዲመታ ሆነ፡፡ መአሕድ/መኢአድ የብአዴንን ሰዎች ባለማቅረቡና በእነሱ መሀል ህዋስ ለመትከል ባለመቻሉ ብአዴን ውስጥ ‹‹ሲፋቅ›› መኢአድ የሚሆን ሰው ማፍራት ሳይቻል ቀረ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም አማራውን በዘሩ ማሰባሰብ የጉጅሌ ስብሐትን መንገድ መከተል ነው የሚለው ተቃውሞ እንዳለ ሆኖ፣ በግል ሆነ በመንግሥት ሥራ ላይ የሚገኙ አማራዎች ወደ መኢአድ ቢመጡ በንግድ ሆነ በሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ለጥቃት ሊጋለጡ ስለሚችሉና እየተጋለጡም ስለነበር፣ ወደ ብአዴን ቢሄዱ ደግሞ ‹‹ሆዳም አማራ›› ላለመባል ጥግ ይዘው እንዲቆሙ ተገድደው ኖሩ፡፡

እኔ የመአሕድ/መኢአድ አባል ስለነበርኩ በአደራጅነትም በአቃቂ፣ በኮተቤና በየካ ክፍለ ከተማ ስላገለገልኩ የቦሌ ክፍለ ከተማ መኢአድ ኮሚቴ ጸሐፊና ሰብሳቢ በመሆን ስለሠራሁ ለተፈጸመው ስህተት ባለድርሻ ነኝ፡፡ ስለዚህም የአማራ ሕዝብን ትግል የጎዳ መንገድ ነበርና ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልለፍ ጉጀሌ ስብሐት በዋነኝነት እንደፈለጉ የሚያስሽከረክሩት ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ገብቶ የመንግሥት ሥልጣን የጨበጠው፣ ዘውዳዊው አገዛዝ ከወደቀና ባላባትነት ከተደመሰሰ፣ በመንግሥት ባለቤትነት ቢሆንም መሬት ለአራሹ ከተደረገ 17 ዓመት በኋላ ነው፡፡ ጉጀሌ ስብሐት በ1968 ዓ.ም. ባወጣው የድርጅቱ ፕሮግራም ከትግራይ ሕዝብ ጠላቶች አንዱ ብሎ የጻፈው ‹‹የአማራ ገዥ መደብን›› አዲስ አበባ ሲገባ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ የታገለው የአሸነፈው የደርግን ወታደራዊ አገዛዝ እንጂ ዘውዳዊውን የአፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት አልነበረም፡፡ የአማራን ገዥ መደብ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያጡት ጉጀሌ ስብሐት አማራውን ለማጥቃት የሚያስችል ነገር ማውጠንጠን ያዙ፡፡

ከ1928 ዓ.ም. የጣሊያን ወረራ በፊት ኢትዮጵያ በንጉሠ ነገሥት፣ በንጉሥ፣ በመሳፍንትና በራስ፣ በደጃዝማች፣ በፊታውራሪ፣ ወዘተ በምትገዛበት ጊዜ እያንዳንዱ ንጉሥ፣ መሳፍንት፣ ራስ፣ ወዘተ ራሱ የሚያዘውና የሚመራው ጦር ነበረው፡፡ ‹‹ነፍጠኛ›› እየተባለ የሚታወቀው ይህ ኃይል በአማኑ ቀን የተሰጠውን መሬት እያረሰ የሚኖር ሲሆን፣ ችግር በተፈጠረ ጊዜ የአገር ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ጀምሮ የፖሊሲን ሥራ እየሠራ ሕግ ሲያስከብር ወንጀለኞችን ለሕግ ሲያቀርብ፣ እስር  ቤቶችን ሲጠበቅ ኖሯል፡፡ በ1933 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ነፃነቷን መልሳ ከተቀዳጀች በኋላ፣ ‹‹የተጠቃነው ዘመናዊ የጦር ኃይል ስለሌለን ነው›› ከሚል እምነት የተነሱት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጠንካራ ዘመናዊ የጦርና የፖሊስ ሠራዊት መሠረቱ፡፡ የፖሊስ ሠራዊት መቋቋም አራሽና ሕግ አስከባሪ ሆኖ ለብዙ ዘመናት የቆየውን ነፍጠኛ አስፈላጊነቱን ዜሮ አገባው፡፡ በመጨረሻም በተፈለገ ጊዜ የሚጠራ አንድ የጦር ክፍል ሆኖ ‹‹ብሔራዊ ጦር›› ተብሎ በደጃዝማች ከበደ ተሰማ የሚመራ ጦር ሆነ፡፡ ብሔራዊ ጦር ደርግን ከመሠረቱት የጦር ኃይሎች አንዱ መሆኑ ነፍጠኛ የሚባለው ክፍል መጥፋቱን የሚያስረዳ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እውነታው የመሬት ባለቤትነትም ነፍጠኝነትም የሌሉ መሆናቸው እያሳየ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ውጪ ከሆነ ወደ ሃያ ዓመት የተጠጋውን የመሬት ባለቤትነትና ከእሱ ብዙ ዓመታት ቀድሞ የሞተውን ነፍጠኝነት ከመቃብር አውጥቶ አማራ ሕዝብ ላይ ከመጫን ጉጀሌ ስብሐትን ያገደው ነገር አልነበረም፡፡ እሱ ነፍጥ አንግቦ ተዋግቶ አዲስ አበባ መግባቱ እየታወቀ አማራን ነፍጠኛ በማለት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን በስፋት ታያያዘው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ለሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ቀዳሚ ጠላት ነፍጠኛ ነው ተባለ፡፡ ከክልሉ ውጪ የሚገኘው አማራ በአንድ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር የሚሰደድ፣ በክፉ ዓይን የሚታይ፣ የሚፈናቀልና የሚገደል ሕዝብ ሆነ፡፡ ሲታሰር፣ ሲፈናቀል፣ ግፋ ተብሎ ሲገደልም የሞተው ‹‹ነፍጠኛ›› ነው እየተባለ እየተንኳሰሰ ሰው ነው ብሎ የሚያዝንለት እንዲያጣ ተደረገ፡፡ ይህን ችግር በማባባስ ከገዥው ፓርቲ እኩል በብሔር የተደራጁ ተቋዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ በአንጽኦት መታወስ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ የቀን ሠራተኛ አማራ ሳይቀር ነፍጠኛ እየተባለ እንዲሸማቀቅ በተደረገበት በዚህ የፖለቲካ ሴራ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ጉዳት ፈጣሪ ይመልከተው ቤት ይቁጠረው ማለቱ ይቀላል፡፡

ጉጀሌ ስብሐት ለአማራው ትምክህተኛ፣ ለኦሮሞውና ለሌላውም ብሔረሰብ ጠባብ የሚል ስያሜ የሰጡት በተቀራረቢ ጊዜ ነው፡፡ ኦሮሞዎችም ሆኑ የሌሎች ብሔረሰቦች አባላት ለአካባቢያቸው ሕዝብ የሚቆረቆሩ ከሆኑ ይህ ጉዳይ የሚመለከተው እኛን ነው፣ ቅድሚያ ለእኛ ለሕዝባችን ሊሰጠው ይገባል፣ ክልላችን በዚህ መንገድ ተገፍቷል፣ ወዘተ የሚሉ ከሆነ ጠባቦች ይባላሉ፡፡ ትምክህት ግን…

ብአዴን ‹‹ትምክህት ማለት የብሔር ህልውና የሚክድ፣ የሕዝቦችን ማንነትና ልዩነት የማይቀበል፡፡ አንድ አገር አንድ ሕዝብ የሚል፣ የብሔርን የዴሞክራሲ መብት የማይቀበል፣ ማንኛውምንም ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በአገር ህልውና ላይ የተጋረጠ አደጋ አድርጎ የሚወስድ፣ የራሱን ቋንቋና ባህል ወግ በሌሎች ላይ በመጫን የሌሎችን ቋንቋ ወግ ባህል በማንቋሸሽና በማሸማቀቅ ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ የሚሠራ›› ነው የሚል ትርጉም ከሰጠ በኋላ፣ ይህ ደግሞ ፀረ ሕዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ላላቸው አማራዎች መገለጫ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ብአዴን ባለው ልክ የብሔረሰቦችን እኩልነት የሚጠላ አማራ አለ ለማለት ይቸግረኛል፡፡ ይህን ፍረጃ የነደፈውና የተቀበለው ብአዴን የአማራ ልሂቃን በነፃነት ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ ሲያፍንና ሲያሳድድ መኖሩ እውነት ነው፡፡

ጽንፈኛ እኔ እስከማውቀውና እስከምረዳው ድረስ በአንድ ክልል ከእኔ ብሔረሰብ ውጪ ማንም ድርሽ ማለት የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም በኢትዮጵያ አካባቢ ሀብት በማፍራት መብት ቢኖረውም፣ በእኔ ክልል አይፈጸምም ውጣ ብሎ መግፋት አካባቢና ከሌላ ብሔረሰብ ማፅዳት ነወ፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ለአማራው ጽንፈኛ የሚል ፍረጃ ተሰጥቶ በዚህ የፖለቲካ ቃል ምክንያት ከመሸማቀቅ ጀምሮ በአማራው ላይ ልዩ ልዩ በደሎች እየተፈጸሙ ናቸው፡፡

አማራው ስትራቴጂካዊ ጠላታችን ነው ብለው በአደባባይ የተናገሩት የጉጀሌ ስብሐት፣ ከአንድም ሁለት ጊዜ የትግራይን ሕዝብ አስልፈው ሰሜንና ደቡብ ወሎንና ሰሜን ሸዋንና በከፊል ጎንደርን የጦር ሜዳ አድርገው ቤት ንብረቱን አውድመዋል፡፡ ሴት እህቶቻችንና እናቶችን መነኩሴ ሳይቀር ደፍረዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት ድርጅቶችን ንብረት ዘርፈው ጭነው ወስደዋል፡፡ አልጫን ያላቸውን ንብረት አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርገው ሰባብረዋል፡፡ የገበሬውን ከብቶች አርደው በልተዋል፡፡ ለመበላት ያልቻሉትን በጥይት ደብድበው ገድለዋል፡፡ ይህን እንዲደረግ ያደረጉት እነ ጉጀሌ ስብሐት ናቸው፡፡ ወንጀሉን መሬት ላይ የሠራው ግን እነሱ ያሠለፉት የትግራይ ወጣት ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ በ2014 ዓ.ም. ረሃብ በገጠመው ጊዜ ወደ አማራ ክልል ሲገባ አማራው፣ ‹‹አንተማ ይህን ይህን በደል የፈጸምክብኝ ነህ የአካባቢዬን መሬት መርገጥ የለብህም፤›› ብሎ ወደ መጣበት ሲመልሰው አልታየም፡፡ የታየው ያለውን ሲያካፍል በተጎዳ ጎጆው ውስጥ አስጠግቶ ሲረዳ ነው፡፡ እንዴት ነው ይህ ሕዝብ ጽንፈኛ የሚባለው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ፋኖ ለአማራም ለኢትዮጵያም ኩራት ነው ብለው ያደነቁት ኃይል እንዴት ከመንግሥት ጋር ወደ መጋጨት ገባ?

አበው ነገርን ከሥሩ ማየት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ የነገሩ መነሻ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የጉጀሌ ስብሐት ጦር በትግራይ ክልል በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈቱ ነው፡፡ በሠራዊቱ ላይ የተከፈተውን ጥቃት ለመከላከል ከሠራዊቱ ጎን ቀድሞ የተሠለፈው በቅርብ የሚገኘው የአማራ ልዩ ኃይል ነው፡፡ መንግሥት በመልሶ ማጥቃት በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀሌ ከተማንና ትግራይን በመያዝ ጊዜያዊ አስተዳደር ዘረጋ፡፡ አስተዳደሩን እንዲመሩ ያደረጋቸው የጉጀሌ ስብሐት ደጋፊዎችን ስለነበሩ እነ ጉጀሌ ስብሐት መልሰው ማንሰራራት ቻለ፡፡ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ በመለወጣቸው መንግሥት ጦሩን ከትግራይ ለማውጣት ተገደደና አወጣ፡፡

የጉጀሌ ስብሐት ጦር ከመከላከያ የገፈፈውን፣ በየቦታው የቀበረውን የጦር መሣሪያ ይዞ አዲስ ወረራ ከፈተ፡፡ የአፋርና የአማራን አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎችን የጦር ሜዳ አደረጋቸው፡፡ ደሴን አልፎ ደብረ ሲናም ደረሰ፡፡ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ‹‹ጦርነቱ አልቋል እጃችሁን ስጡ›› የሚል መልዕክት ወደ አዲስ አበባ ላኩ፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ለውጊያ አቅም ያለው አማራ፣ ክልሉን ከጥፋት እንዲታደግ ጥሪ አቀረበ፡፡ ሌተና ጄኔራል ባጫ ደበሌ፣ ‹‹እናቱ፣ እህቱና ሚስቱ ስትደፈር ዝም ብሎ የሚያይ አማራ ባይወለድ ይሻላል፤›› በማለት ጥሪውን አጠናከሩ፡፡ የአማራ ፋኖ ከየአካባቢው እየተነሳ ወደ ጦርነቱ ገባ፡፡ ወረራው ተቀለበሰ፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ወደ አሸናፊነቱ ተሻገረ፡፡ የጦርነቱ ማለቂያም እየቀረበ እየመጣ እያለ ‹‹ፋኖ ዘራፊ ነው›› የሚል ክስ ተከፈተበት፡፡ አሥራ አንድ ሺሕ ፋኖዎች ወደ አስር ቤት ተወረወሩ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ አንድም ፋኖ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቶ ተቀጣ ሲባል አልሰማሁም፡፡

ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ‹‹ፋኖ ጥቁር ክላሽ የታጠቀው መከላከያ እየነጠቀው ነው፤›› የሚል ውንጀላ ተጀመረ፡፡ ውንጀላውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠናከሩት፡፡ ይሁን እንጂ ፋኖ መሣሪያ የታጠቀው ከጉጅሌ ስብሐት ማርኮ መሆኑን ቢገልጽም ሰሚ አላገኘም፡፡ ችግሩን ይበልጥ ያባባሰው ደግሞ በመንግሥትና በጉጀሌ ስብሐቶች መካከል በደቡብ አፍሪካና በኬንያ የተደረጉት ስምምነቶችና አተገባበር ነው፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ፣ እንዲሁም የራያ አላማጣ ሕዝብ በጉልበት ወደ ትግራይ ተከልለናል አማራነታችን ታውቆ በአማራ ክልል ውስጥ መግባት አለብን የሚል የቆየ ጥያቄ እንዳለው፣ ከጦርነቱ በኋላ በአማራ ክልል ሥር የሚገኝ መሆኑ፣ የአካባቢን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ቦታ ጉዳዩ እንዳለው የመንግሥት ተደራዳሪዎች ልብ ያሉበትና የተዘጋጁበት ነበር ለማለት አይቻልም፡፡

የደቡብ አፍሪካውን ስምምነት ተግባራዊ የሚደረግበትን ዝርዝር ዕቅድ ለማውጣት ናይሮቢ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጉጅሌ ስብሐት ጦር ትጥቅ የሚፈታው፣ በክልሉ ያሉ ሌሎች ኃይሎች ከክልሉ ከመውጣት ጋር ጎን ለጎን ነው የሚል ውል መግባታቸው የጉዳዩን አስቸጋነሪት ያለ መገንዘባቸው ማሳያ ከመሆኑ በላይ፣ መንግሥትን ለምዕራባውያን ግፊት እንዲጋለጥ እንዳደረገው ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ይህ የስምምነቱ ክፍል በአጎራባቹ የአማራ ሕዝብ ዘንድ በበጎ እንዳልታየም መታወቅ አለበት፡፡ በትግራይ የጊዜያዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቶ ጌታቸው ረዳ አሳልፈው መስጠታቸውና ጉጅሌ ስብሐት እንዲያንሰራራ ያደረገ ሲሆን፣ የህልውና ሥጋት ላይ ወድቄያለሁ ብሎ ለሚያምነው የአማራ ሕዝብ የበለጠ ሥጋት የሚደቅን ሆነ፡፡

አማፂ እስካልሆነ ድረስ በአንድ አገር መንግሥት ከመከላከያና ከፖሊስ ውጪ የታጠቀ ኃይል መኖር እንደሌለበት ይታመናል፡፡ ይህ ለአማራ ልዩ ኃይልና ለፋኖ ያጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ሆኖም ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ስምምነቱ ተፈርሞ በመጋቢት ወር ከሌሎች ክልሎች በፊት የመጀመርያ ሆኖ የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖ ከፈለገ ወደ መከላከያ፣ ወደ ፌዴራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ እንዲገባ ካልፈለገም ወደ አካባቢው እንዲመለስ መመርያ ተላለፈ፡፡ ክልሉ የህልውና ሥጋት አለበት ብለው የሚያምኑት ፋኖዎች ትዕዛዙን በቅንነት ለማየትና ለመተግበር ተቸገሩ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች አማራ በዞኑ እየተለየ ሲገደል፣ አዲስ አበባ መግቢያ ጎሀ ጽዮን አካባቢ እየታፈነ ገንዘብ ሲጠየቅበት፣ መክፈል ያልቻለው ደሃ አማራ ሲገደል፣ አጣዬ በተደጋጋሚ ስትወረር፣ ስትገፋ ምንም ያላደረገው የፌዴራል መንግሥት ክልሉንና ሕዝቡ ከአንድ ዓይነት አደጋ ይታደገዋል ብሎ ለማመንና ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል አልሆነም፡፡ ፋኖዎች ለወገናችን መቆም ያለብን እኛ ነን ብለው ፀኑ፡፡ ውሳኔውን በኃይል ለማስፈጸም በተነሳው መንግሥትና በፋኖ መካከልም ግጭት ተከሰተ፡፡ አንደኛው ሌላውን ለማስጠላትና ለማጥላላት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈተ፡፡ መንግሥት ፋኖን ዘራፊና ቀማኛ አድርጎ በመቁጠር ‹‹ጃዊሳ›› የሚል ስም ሰጠው፡፡ ከወዲያ በኩል ደግሞ መከላከያ ላይም ‹‹የኦሮሙማ ጦር›› የሚል ስም ተጫነበት፡፡፡ ሁለቱም ለእኔ ልክ ያልሆኑ ተግባራት ናቸው፡፡ ማጥላላቱና ስም ማጥፋቱ ችግሩን ቢያባብሰው እንጂ እንደማያቃልለው የታወቀ ነው፡፡

መንግሥት ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ፣ ፅንፈኛ የሚሉ ስሞች በአማራው ላይ ያደረሱትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ አዕምሮ ጉዳት መለስ ብሎ ማየት አለበት፡፡  ‹‹ጃዊሳ›› ምን እያስከተለ እንደሆነ ደግሞ እያየን ነው፡፡ ከመከላከያው ጎን ተሠልፎ በአንድ የጦር ግንባር የተዋጋውን ፋኖን እንዴት ጠላት እንዳደረገው መንግሥት ራሱን ደግሞ ደጋግሞ መጠየቅም ይኖርበታል፡፡ በኃይል ለመፍታት የሚያደርገውን መጣደፍም መግታት ይገባዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ ከየተማ ከነዋሪዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር የሚያደርገው ውይይትና ስብሰባ፣ ቢሆን ከዚህ ቀደም በሌሎች አካባቢዎች ተደርጎ ውጤት እንዳላመጣ ሁሉ በአማራ ክልልም ያመጣል ብዬ እኔ አላምንም፡፡

በየቀኑ የሚጠፋውን የሰው ሕይወት የማዳን ኃይል ያለው መንግሥት ነው፡፡  ሰላም እጁ ላይ ነች ያለችው፡፡ መንግሥት ለሰላም መቆሙን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡

የአገር ሽማግሌዎች ሆኑ የሃይማኖት አባቶች ችግሩ በመግለጫ ሊፈታ እንደማይችል ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ወደፊት መጥተው አንተም ተው አንተም ተው ቁጭ ብላችሁ ተነጋገሩ፣ ተደራደሩ ማለት አለባቸው፡፡ መንግሥት ልብ ይገዛ ዘንድ ሊመክሩት ግድ ነው፡፡

ደርግ የወደቀው ‹‹ጥቂቶች ወንበዴዎች›› እያለ ሲያናንቅ ነው፣ ብልፅግናም ሆነ  ዓብይ (ዶ/ር) ከእርሱ መማር ይኖርባቸዋል፡፡

ፈጣሪ ሰላሙን ያምጣልን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...