Monday, July 22, 2024

አገራዊ ኪሳራ ያስከተሉ የመስኖ ግድቦች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በደቡብ ጎንደር ዞን ወደ 20 ሺሕ ሔክታር መሬት እንዲያለማ ታስቦ የተጀመረው ርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት አጋጠመው የተባለው የፕሮጀክት መጓተትና የሀብት ብክነት ችግር፣ ከበስተጀርባው ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮችን የሚያስነሳ ነው፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ‹‹የመንግሥት ትልልቅ ፕሮጀክቶች የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ በ2009 ዓ.ም. ባቀረበው ባለ300 ገጽ ሰነድ፣ የፕሮጀክቱ ችግር ከየት እንደሚነሳ በሚገባ ዘርዝሮታል፡፡

አገራዊ ኪሳራ ያስከተሉ የመስኖ ግድቦች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት

ርብ ግድብ በአራት ዓመት ጊዜ ይጠናቀቃል ቢባልም ተጨማሪ አራት ዓመት ወስዶም ሆነ፣ ፕሮጀክቱ የሚያለማውን የመሬት መጠን ወደ ሰባት ሺሕ በማውረድ ሊጠናቀቅ አለመቻሉን ይህ ሰነድ አመልክቷል፡፡ በተያዘለት የ4.6 ቢሊዮን ብር በጀት የመጀመሪያ ዕቅዱን ወይም ሰባት ሺሕ ሔክታር መሬት ማልማት የሚያስችል የ35 በመቶ ግንባታ ማገባደድ አለመቻሉን ጥናቱ ያነሳል፡፡

የፕሮጀክቱ ጥናት ለእስራኤሉ ታሀል (TAHAL) ኩባንያ መሰጠቱን የሚያወሳው ጥናቱ፣ ይህ ኩባንያ ደግሞ በግብፅም ሰፋፊ ሥራዎች እንዳሉት ነው ያመለከተው፡፡ የመስኖ ፕሮጀክቱ በዋናነት የሚገነባው ደግሞ የታላቁ ዓባይ ወንዝ ገባር በሆነው የርብ ወንዝና የጣና ሐይቅ ላይ መሆኑን ያስረዳል፡፡ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ሲጠየቁ አንዳንዶቹ ጥናቱ በግብፅ በስፋት ለሚንቀሳቀሰው ለእስራኤሉ ታሀል መሰጠቱ፣ የአገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ጥርጣሬያቸውን እንደተናገሩ ጥናቱ አመልክቷል፡፡

ጥናቱ በመደምደሚያው ጉዳዩ ተጨማሪ ማጣራት ቢጠይቅም ፕሮጀክቱ በተደጋጋሚ የዲዛይን ለውጥ የገጠመው መጓተት፣ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን በማየት የሠራተኞቹ ጥርጣሬ መሠረት ቢስ የሚባል አለመሆኑን አካቷል፡፡ በፕሮጀክቱ ምርታማ የሆኑ መሬቶች ተትተው ምርታማ ያልሆኑ መሬቶች እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡ በግድቡ ቁፋሮ ወቅት በጥናቱ ያልተጠቀሰ ከፍተኛ አለት መገኘቱና ለቁፋሮ በሚል ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ለሆነ ወጪ ፕሮጀክቱ ተዳርጓል፡፡ በካናል ሥራ ደግሞ የውኃውን ብክነት የሚጨምሩ ሥራዎች መከናወናቸውን ያወሳል፡፡ ይህ ሁሉ ፕሮጀክቱን የጎተተ ችግር ጥናቱን ካካሄደው ተቋም ማንነት፣ ይህም ከብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ጋር ሊያያዝ የሚችል ችግር እንደሆነ ነው ጥናቱ ያብራራው፡፡

አገራዊ ኪሳራ ያስከተሉ የመስኖ ግድቦች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የከሰም የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት

ከሁለት ወራት ቀደም ብሎ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ደኤታ ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር)፣ ይህንን የቆየ ችግር በሌላ አነጋገር አንስተውት ነበር፡፡ ‹‹የመስኖ ልማትን ስናስብ ዘርፉ በአጠቃላይ እንደ አገር ካላደገ በስተቀር በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መመራቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ሚኒስቴሩ ግድቦችን አይገነባም፡፡ በተቋራጮች ነው የሚሠራው፡፡ ገንቢው ብቻ ሳይሆን አማካሪውም በቂ የመስኖ ግንባታ ዕውቀት ከሌለው ሥራው ፈታኝ ነው፡፡ ከውጭ ገንቢና አማካሪ ለማምጣት ደግሞ የውኃ ፖለቲካው ሌላ ፈታኝ ጉዳይ ነው፤›› በማለት፣ ኢትየጵያ በትልልቅ የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየገጠማት ያለውን መልከ ብዙ ፈተና ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ደኤታው እንደሚናገሩት፣ የርብ መስኖ ግድብ ዛሬ 18 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ነገር ግን ግድቡ አሁንም ቢሆን 76 በመቶ ብቻ ነው መጠናቀቅ የቻለው፡፡ ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የፕሮጀክቱ ችግር የዲዛይን ሥራውን ከወሰደው እስራኤላዊ ኩባንያ የሚጀምር ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ያለማል ተብሎ የታሰበውን 20 ሺሕ ሔክታር ሳይሆን፣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሰባት ሺሕ ሔክታር ወደ ሥራ ለማስገባት ነው ርብርብ እየተደረገ የሚገኘው፡፡

ርብ ግድብ የመስኖ ካናሎችና ውኃውን ለእርሻ የሚያደርሱ ቦዮች ተሠርተው ሳያልቁ ተመረቀ ተብሎ ዜና መሠራቱን ተጨማሪ ችግር የሚሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ይህን መሰል ችግር ደግሞ በጊዳቦና አልዌሮ ግድቦችም ማጋጠሙን ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ርብ ምናልባት ከጎንደር ከተማ መጠጥ ውኃ ጋር ስለተቆራኘና ለከተማም ቀረብ ስላለ ይሆናል ብዙ የተወራለት፡፡ አልዌሮ ግድብን ካየን ግን ብቻውን 200 ሺሕ ሔክታር መሬት ማልማት የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት ሆኖ ነው ወደ ሥራ ሳይገባ የቆመው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት 950 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የዝናብ ውኃ እንደምታገኝ፣ ከዚህ ውስጥ 120 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በሐይቅ፣ በጅረቶችና በወንዞች ዓመቱን ሙሉ የሚቀር መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው ይጠቅሳሉ፡፡ መስኖ ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ ፖሊሲ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች መከተላቸው ተገቢና ጤናማ የፖለቲካ አተያይ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ አሁን መንግሥት ለቆላማ አካባቢዎችና ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን የተናገሩት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በተቻለ መጠን ብዙ የአገር ሀብት ፈሶባቸው ወደ ሥራ ሳይገቡ ለረዥም ዓመታት የቀሩ ግድቦችን ጠግኖና አገባዶ ወደ ሥራ ማስገባት አንዱ የመንግሥታቸው ትኩረት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አገራዊ ኪሳራ ያስከተሉ የመስኖ ግድቦች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የመገጭ – ሰርባ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት

የመስኖ ልማት የአገር ምርትና ምርታማነትን በሁለትና ሦስት እጥፍ በማሳደግ ‹‹የአገርን ሁለንተናዊ ገጽታ በቶሎ የሚቀይር›› ሲሉ የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው፣ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ የተቋማቸው ዋና ግብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከስኳር ፕሮጀክቶች ጋር በተገናኘ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂ 60 ዓመታት ዕድሜ በኢትዮጵያ ማስቆጠሩን ያስታወሱት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን የዕድሜውን ያህል ዘርፉ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂም ሆነ በአገነባብ ጥራት አለማደጉን ገልጸዋል፡፡ በመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታም ሆነ በመስኖ አውታሮች አስተዳደር ዘርፍ አገራዊ አቅም መገንባት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ዕምቅ የመስኖ አቅም በሰፊው ለመጠቀም ብዙ መሠራት አለበት በሚል፣ ባለፉት 20 ዓመታት ትልልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ መጠነ ሰፊ የአገር ሀብት ሲፈስ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በውጭ ኃይሎች አሻጥርና ሸር ብቻ ሳይሆን በግብታዊ ዕቅዶች፣ እንዲሁም በደካማና ኃላፊነት በጎደላቸው የፕሮጀክት ክዋኔዎች የተነሳ ኢትዮጵያ ለግዙፍ የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተባለ ብዙ ሀብት ለመክሰር ተዳርጋለች፡፡

ይህን በማስረጃ አስደግፎ ያቀረበው የ2009 ዓ.ም. የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሪፖርት፣ በወቅቱ የጊዳቦ መስኖ ግድብ ገጥሞት የነበረውን እክል በምሳሌነት ያነሳል፡፡ ከዲላ ከተማ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት የተጀመረው ጊዳቦ ግድብ አጀማመሩ ሰባት ሺሕ ሔክታር ለማልማት ብቻ ነበር፡፡ በትንሽ የዲዛይን ለውጥ ማለትም የግድቡን ቁመት በሦስት ሜትር በመጨመር ብቻ፣ የሚያለማውን መሬት ምጣኔ በ71 በመቶ በማሳደግ 13 ሺሕ ሔክታር መሬት ማድረስ ተችሏል ይላል ሪፖርቱ፡፡ እንዲህ ዓይነት ያለ ዕውቀት፣ ያለ በቂ ጥናትና ያለ ትክክለኛ ዲዛይን ወደ ፕሮጀክት ግንባታ ዘው ብሎ የመግባት ዕርምጃ በተለያዩ ግዙፍ የመስኖ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ የሚደርስባት ኪሳራ እንዲያሻቅብ ማድረጉን ጥናቱ ያስረዳል፡፡

የመስኖ ግድቦች ልማት እንደ ሌሎች ዘርፎች በቀላሉ የውጭ ብድር አይገኝበትም፡፡ ከአገር ውስን ሀብት ተቀንሶ በጀት የሚመደብባቸውን የመስኖ ፕሮጀክቶችን የሚመራ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል የበቃ ተቋምም በአገሪቱ አልተፈጠረም ይባላል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በአብዛኛው እንደ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽንና የያኔው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ባሉ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ነበር ወደ ሥራ የገቡት፡፡ ይህ ሁሉ ወደ ግንባታ ሲገባ በግንባታ ቁጥጥር፣ በፕሮጀክት አስተዳደርና ክትትል ካጋጠሙ ችግሮች ጋር ተዳምሮ አገሪቱ ከባድ ዋጋ እንድትከፍል ማድረጉን የጥናቱ ግኝት ያስቀምጣል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አገር በመስኖ ልማት ከባድ ዋጋ መክፈል የጀመረችው ከረዥም ጊዜ ጀምሮ መሆኑ ይነገራል፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት ወደ አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ለማልማት ታስቦ በጋምቤላ የተገነባው አልዌሮ ግድብ ዛሬም ድረስ የሚገባውን ያህል መጥቀም አለመቻሉ ይነገራል፡፡ ፕሮጀክቱ ለግል ተላልፎ ቢሰጥም ከ1,000 ሔክታር መሬት ያነሰ ነው የሚለማበት ይባላል፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ፣ እንዲሁም በደርግ ዘመን ግንባታቸው ከተካሄዱ ግድቦች መካከል ብዙ ሀብት የወጣባቸው ፕሮጀክቶች ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጡ ቀርተዋል የሚለው ጉዳይ ጎልቶ ይነሳል፡፡ በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ላይ ጎዴ አካባቢ ለ25 ሺሕ ሔክታር ይበቃል ተብሎ የተሠራው ፕሮጀክት ጥቅም ላይ አለመዋሉ ይነገራል፡፡ በአፋር ተንዳሆ ከረዥም ጊዜ በፊት ተጀምሮ የነበረው በስተኋላም ወደ ስኳር ኮርፖሬሽን የዞረው የመስኖ ፕሮጀክት በ2015 ዓ.ም. በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ከሚከናወኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ጋር ተካቶ በጀት ሲጠየቅበት ማየት አስገራሚ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

አገራዊ ኪሳራ ያስከተሉ የመስኖ ግድቦች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የተንዳሆ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት

ውኃ የያዙ ነገር ግን አገር ሳይጠቅሙ የቀሩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን እንደ አዲስ ወደ ሥራ መመለስ ዋና ዕቅዱ እንደሆነ የሚናገረው አሁን ዘርፉን በበላይነት የሚመራው የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር፣ ከተንዳሆ ውጪ ጣና በለስና ከሰም ፕሮጀክቶችን ሥራ አስጀምራለሁ የሚል ዕቅድ በበጀት ዓመቱ አቅርቦ ነበር፡፡ ለረዥም ዓመታት ከወጪ በስተቀር አንዳችም ጥቅም ሰጥተው የማያውቁት እነዚህና ሌሎች ግዙፍ ነባር የመስኖ ፕሮጀክቶች ዘንድሮስ ወደ ታለመው ልማት ይገቡ ይሆን ወይ የሚለው ጉዳይ ከወዲሁ እያጠያየቀ ነው፡፡

በ2014 ዓ.ም. እንደ አዲስ ተዋቅሮ ሥራ የጀመረው የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር፣ በአገሪቱ በአጠቃላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል 157 ሺሕ ሔክታር ውኃ ገብ መሬትን መለየቱን ይገልጻል፡፡ በድምሩ 17 አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶችን መጀመሩንና ነባሮቹን ጨምሮ በአጠቃለይ 27 ፕሮጀክቶችን አከናውናለሁ የሚለው ሚኒስቴሩ፣ 29 ያህል ደግሞ በጥናትና ዲዛይን ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

ሽንፋ፣ በለስ፣ ጊሎ፣ ታችኛው ገናሌ፣ ወይብ፣ አንገረብ፣ ሞርሞራ፣ ወይጦ፣ ቡልዶሃ፣ ኤረር፣ ራሚስ፣ ዋልጋ፣ ጋሙና፣ ሎቆ አባያ፣ አይማ፣ ደቡብ ጎዴ፣ አቦና፣ ጊሎ፣ ተላ፣ ማኩዌ፣ እንዲሁም በኮሪያ መንግሥት ድጋፍ አደአ በቾ የተባሉ ግድቦች ጥናትና ዲዛይን ሥራቸው የተጀመረ፣ በግዥና አቅርቦት ወይም በግንባታ ሒደት ላይ ያሉ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ይገልጻል፡፡

ነባርና ዳግም ሥራቸው የሚጀመር በሚል ደግሞ መገጭ፣ ጊዳቦ፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ርብ፣ ወልመል፣ ጨልጨል፣ ላይኛው ጉደር፣ እንዲሁም ጣና በለስ፣ ተንዳሆና ከሰም ግድቦች በቅርቡ ለፓርላማ በቀረበው በሚኒስቴሩ ዓመታዊ የሥራ ክዋኔ ሪፖርት ላይ ተዘርዝረዋል፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በሚል አጀማ፣ ግልገል ዓባይና መገጭ (ለሁለተኛ ጊዜ) ቀርበዋል፡፡

ወደ 208 ሠራተኞች እንዳሉት፣ 615 ሚሊዮን ብር መደበኛ በጀትን ጨምሮ 15 ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት እንዳለው የሚገልጸው የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አነስተኛ የመስኖ ሥራዎችንም ትኩረት እንደሚሰጥ በዕቅዱ አስቀምጧል፡፡ ወደ ሰባት ሚሊዮን ሔክታር በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት አገሪቱ እንዳላት በጥናት መለየቱን የሚጠቅሰው ሚኒስቴሩ፣ 1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት መሸፈን መቻሉን ይጠቅሳል፡፡ በዓለም ባንክ 400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በሰባት ክልሎች፣ በ100 ወረዳዎች ለስድስት ዓመታት የሚተገበር ‹‹የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ›› ፕሮጀክት እየተገበረ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ደግሞ የሰብል ምርት ብቻ ሳይሆን፣ የግጦሽ መሬትና የመኖ ልማት ጭምር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የተቋማቸውን ዋና ዋና የሥራ እንቅስቃሴ ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) እንደተናገሩት፣ ተቋማቸው የመስኖ ፕሮጀክቶችን ማከናወን ብቻ ሳይሆን በትክክል ለልማት መዋላቸውንም የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዋና ግባችን የመስኖ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ማስተዳደር፣ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና ፍትሐዊ የውኃ ሥርጭት እንዲኖር ማድረግ ነው፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በአዳማ ከተማ የቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት ደግሞ የተቋማቸው የመስኖ ልማት መርሐ ግብሮች ‹የሌማቱ ቱሩፋት›፣ ‹የበጋ ስንዴ ልማት› እና ‹አረንጓዴ አሻራ› ከተባሉ አገር አቀፍ የልማት ጥንስሶች ጋር በቀጥታ መተሳሰራቸውን ተናግረው ነበር፡፡

ሚኒስትሯ አይሻ (ኢንጂነር) በወቅቱ 70 እና 80 በመቶ ያህል ተገንብተው ያልተጠናቀቁ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በቀጥታ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ሚኒስትሯ ይህን ቢሉም በአንዳንድ ፕሮጀክቶች የታየው የሥራ ክንውንም ሆነ የቅርብ ጊዜ ልምድ ፕሮጀክቶቹን ለልማት ማዋሉ ቀላል እንደማይሆን ያመለክታል፡፡

ጊዳቦ ግድብ በምዕራብ ጉጂ ኦሮሚያ ክልልና በሲዳማ ክልል መካከል በ1.6 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በ2002 ዓ.ም. ተጀምሮ በ2011 ዓ.ም. መጠናቀቁ ይነገራል፡፡ ወደ 62.5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ መያዙ ይነገራል፡፡ በኦሮሚያ 8,374 ሔክታር መሬት፣ በሲዳማ ደግሞ 5,000 ሔክታር መሬት በመስኖ ማረስረስም ይችላል፡፡

ጊዳቦ ግድብ በ2011 አለቀ ይባል እንጂ ከአንድ ዓመት በፊት በመንግሥት ሚዲያዎች በቀረበ ዶክመንተሪ ግን ሥራው አለማለቁ ተመላክቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል መሠራት ከነበረበት 12.2 ኪሎ ሜትር ካናል ውስጥ 8.6 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው አገልግሎት መስጠት የጀመረው፡፡ በሲዳማ ክልል በኩል ደግሞ መገንባት ከነበረበት 12.8 ኪሎ ሜትር ካናል ውስጥ ወደ 400 ሔክታር ብቻ የሚያለማ 2.5 ኪሎ ሜትር ካናል ነው መገንባቱ የተነገረው፡፡

ከጊዳቦ የመስኖ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ጊዳቦ የተቀናጀ የመስኖ እርሻ ልማት አብሮ መገንባቱ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ በሙዝ፣ በፓፓያና በአቮካዶ የተሸፈነው 700 ሔክታር ብቻ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በ1.6 ቢሊዮን ብር በጀት ተገነባ የተባለው ጊዳቦ አምና ግንባታው 91 በመቶ መድረሱና ለዚህም 2.1 ቢሊዮን ብር እንደፈሰሰበት ነው የተረጋገጠው፡፡ ከግንባታው ጎን ለጎን 22 ሜትር የሚረዝም ሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎችን የሚያገናኝ ድልድይ በ54 ሚሊዮን ብር መገንባቱ ተነግሯል፡፡ ያም ቢሆን ግን ለግንባታው የወጣው ወጪ፣ እንዲሁም የፈጀው ጊዜ፣ ሰጠ ከሚባለው አገልግሎት ጋር በተነፃፃሪነት ፕሮጀክቱ የተሳካ ነው የሚያስብል ነገር አለመኖሩ ይነገራል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ1997 ዓ.ም. የተጀመረው የተንዳሆ ግድብ በ2007 ተጠናቋል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ደግሞ 8.56 ቢሊዮን ብር በጀት የወጣበት ሲሆን፣ በአጠቃላይ 30 ሺሕ ሔክታር መሬት ያለማልም ተብሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዛሬ ዘጠኝ ወር ለፓርላማው የዕቅድ ሪፖርቱን ሚኒስቴሩ ሲያቀርብ፣ ይህንን ፕሮጀክት እንደ አዲስ የሚጀመሩ ካላቸው ፕሮጀክቶች አንዱ አድርጎ ነበር ያቀረበው፡፡

በአፋር ክልል 4,000 ሔክታር ለማልማት ያስችላል ተብሎ በ1997 ዓ.ም. የተጀመረው ከሰም ግድብ በ2007 ዓ.ም. መጠናቀቁ ተነግሯል፡፡ ወደ 2.75 ቢሊዮን ብር በጀት እንዳለው የተነገረው ግድቡ አለቀ ከተባለ ከብዙ ዓመት በኋላ፣ እንደ አዲስ የግንባታ ዕቅድ ተብሎ ዘንድሮም መቅረቡ ብዙ አነጋግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት እጅግ ብዙ የአገር ሀብት እየፈሰሰባቸው የሚጀመሩ ፕሮጀክቶት በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ብዙ ዓመታትና ብዙ የአገር ሀብት ፈጅተው ግን በቅጡ ለአገልግሎት መብቃት አልቻሉም መባሉ የተለመደ ይመስላል፡፡ በአገሪቱ በየጊዜው በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀቁ እየባለ የምርቃት ድግስ ሲካሄድ ይታያል፡፡ ጥቂት ቆይቶ ግን የግድቦቹ የመስኖ ሥራዎች አላለቁም ወይም ግድቦቹን የሚጠቀም ጠፋ የሚል ዜና በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ አልዌሮ ግድብ የገጠመው ይህ መሆኑ ይነገራል፡፡

ይህን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ደኤታው ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ‹‹አንድ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀቀ የሚባለው ውኃው በካናል ተጓጉዞ ለእርሻ ልማት ሲውል ብቻ ነው፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

በአገር ደረጃ የመስኖ ግንባታ የአገር ገጽታን የሚቀይር በሚል ልዩ ትኩረት ማግኘቱን ይናገራሉ፡፡ የአገር ህልውና መሠረት ሊሆን እንደሚችልና በዘርፉ ያለውን የተዛባ ዕይታ ለመቀየር መታቀዱን ያስረዳሉ፡፡ አሜሪካ ከእንግሊዝ ነፃ በወጣችበት ወቅት ሀሚልተን የተባሉ የገንዘብና የኢኮኖሚ ባለሥልጣኗ፣ ‹‹በምግብ ራሳችንን ካልቻልን በስተቀር ከእንግሊዝ ተገዥነት ሙሉ ለሙሉ ነፃ ወጣን አይባልም፤›› ብለው ጠንካራ አቋም እንዲያዝ ያደረጉትን ጥረት መለስ ብለው ያስታውሳሉ፡፡

ከዚህ በመነሳት፣ ‹‹ምግብ አንዱ አገር በሌላው አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበት ትልቅ የፖለቲካ መሣሪያ ነው፤›› ሲሉ የሚገልጹት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያም የምግብ ሉዓላዊነቷን ማስከበር አለባት ሲሉ ሞግተዋል፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን ግን በኢትዮጵያ የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች በፕሮጀክት አፈጻጸም ብቻ ሳይሆን፣ በፕሮጀክት አስተዳደርም ውጤታማና ከአገር ሀብት ብክነት የፀዳ አካሄድን መከተል እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -