Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየበጎ ፈቃድ የሕክምና አገልግሎትን በቋሚነት

የበጎ ፈቃድ የሕክምና አገልግሎትን በቋሚነት

ቀን:

ጎዳናው ቤቴ፣ ድንጋዩ ትራሴ ብለው ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ በርካታ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ 50 ሺሕ ገደማ የሚሆኑ ወገኖች ኑሯቸው ጎዳና ላይ እንደሆነም ይነገራል፡፡ ከእነዚህም እናቶችና ሕፃናት፣ አረጋውያንና ወጣቶችም ጭምር ይገኙበታል፡፡ የጎዳናው ኑሮ ከረሃብና ከጥማቱ፣ ከብርድና ከፀሐዩ ባሻገር፣ የአዕምሮ ሕሙማንን ጨምሮ የበርካታ ዓይነት ሕመም መገኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይ ደግሞ አረጋውያን ከዕድሜያቸው ከመግፋት ጋር ተያይዞ የመቋቋም አቅማቸው ዝቅ ያለ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

 በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሰዎች ከቤታቸው የሚወጡበትን በርካታ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ በቤተሰባቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ከቤታቸው ወጥተው፣ ለሁለት ዓመታት ጎዳና ላይ የነበሩ ባለ ታሪክና በጎዳና ቆይታቸው የገጠማቸውን ችግርና በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡                            

‹‹ትውልድና ዕድገቴ አቦ ነው፣ ዘመዶቼ ጠሉኝና አባረሩኝ፡፡ ወንድሞቼም የአባቴን መሬት ከልክለው ለጎዳና ኑሮ ዳረጉኝ፤›› የሚሉት አቶ ውድሳ ገቢሳ፣ በዚህም ለሁለት ዓመታት ገደማ ጎዳና ላይ ሲቆዩ በቆዳ በሽታ ተለክፈው ሲሰቃዩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ መቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማኅበር እንደተቀላቀሉ ይናገራሉ፡፡

ማኅበሩ ለሁለት ዓመታት ያህል በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተኝተው እንዲታከሙ ስላደረጋቸው፣ በአሁኑ ጊዜ ሲሰቃዩበት ከነበረው የቆዳ በሽታ ተፈውሰው ቆዳቸውም ወደ ቀድሞ ጤንነቱ መመለሱን ይናገራሉ።

በበሽታው ‹‹ከአገልግሎት ውጪ ሆኜ ነበር፤›› የሚሉት አቶ ውድሳ፣ ወደ ተቋሙ ከገቡ በኋላ ጤናቸው እንደተመለሰላቸው ተናግረው፣ ነገር ግን የደም ግፊት እንደሚያስቸግራቸውና ለዚህም ቢሆን በድርጅቱ ሕክምና እያገኙ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ከዚህም በላይ ‹‹በቀን ሦስት ጊዜ ይመግቡናል፣ ከታመምን ያሳክሙናል፣ እግዚአብሔር ይመሥገን የከፋኝ ነገር የለም ከዘመዶቼ በላይ ነው የረዱኝ፤›› ሲሉ ምሥጋናቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ ውደሳን ያገኘናቸው ለደም ግፊታቸው መድኃኒት ለማግኘት በመቄዶኒያ ቅጥር ግቢ ተሠልፈው ነበር። ከእሳቸው ጋርም ቁጥራቸው በርከት ያሉ ታማሚዎች ተሠልፈው የነፃ ሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ነበሩ። ነፃ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት ደግሞ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የክረምት በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች ናቸው።

ሆስፒታሉ ከነሐሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት አራት ቀናት ለሁለት ሺሕ የመቄዶኒያ ታማሚዎች የተለያዩ ሕክምናዎችን ሰጥቷል።

የደም ግፊት፣ የስኳር ሕመም፣ የማኅፀን በርና የጡት ካንሰር ምርመራ፣ የነርቭ ሕክምና፣ የውስጥ ደዌ ሕክምናን ጨምሮ፣ የሌሎችንም በሽታዎች የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጡ የተናገሩት የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር  አንዱ ዓለም ደነቀ (ፕሮፌሰር) ናቸው።

‹‹የሕክምናና የጤና አገልግሎት ከልብ የመነጨ በጎነት ከሌለበት የተሟላ አገልግሎት ነው ብለን አናምንም፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር አንዱ ዓለም፣ በመቄዶኒያ የሚሰጧቸው የጤና ሕክምና አገልግሎት ቋሚና ቀጣይነት ያሏቸው እንዲሆኑ ውይይት እያደረጉ እንደሆነም አክለዋል።

በሌሎች ቦታዎችም አገልግሎቱን እየሰጡ መቆየታቸውን ተናግረው፣ አሁንም ቢሆን ሕክምና በሚያስፈልገው ቦታ ሁሉ በመንቀሳቀስ እየሰጡ እንደሆነም ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቋሚ መሆንና ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ መሆን አለበት የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት በሌሎች አገሮች ለተማሪዎች ስኮላርሽፕ የሚያሰጥ ሲሆን፣ ለሌሎች ደግሞ ትልቅ ዋጋን የሚያሰጥ በመሆኑ መለመድ አለበት ባይ ናቸው።

በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌላው ዘርፍም በንቃት መሳተፍ ለአገር ዕድገት ጠቃሚ ነው ብለዋል።

በየቀኑ ከ40 እስከ 60 የሚሆኑ የተለያዩ ሕሙማንን ወደ ሆስፒታል እንደሚልኩ የተናገሩት ደግሞ በመቄዶኒያ የበጎ አድራጎት ማኅበር በነርስነት ሙያ እያገለገሉ የሚገኙት ዮናስ ሙሉጌታ ናቸው።

ድርጅቱ በቂ የሕክምና ባለሙያ የለውም የሚሉት ነርስ ዮናስ ሙሉጌታ፣ አብዛኛው ሕክምና የሚሰጠው በሪፈራል ወደ ሌሎች የሕክምና ተቋማት በመላክ ነው ብለዋል።

አንዳንዶቹ ለረዥም ዓመታት ጎዳና ላይ የቆዩ ሰዎች በመሆናቸው፣ ለተደራራቢ በሽታዎች ተጋላጭ ሆነው ወደ ተቋሙ ስለሚመጡ፣ ከፍተኛ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሌሎች የሕክምና ተቋማት ርብርብ ያስፈልጋል ተብሏል።

የደም ግፊት፣ የልብና የስኳር ሕመም አለብኝ የሚሉት ደግሞ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ሲጠባበቁ የነበሩት አቶ ዳንኤል ማሞ ናቸው።

ከዚህ በፊትም ክትትል ያደርጉ እንደነበር ያወሱት አቶ ዳንኤል፣ የሕክምና አገልግሎት ሰጪዎቹ ካሉበት ድረስ መምጣታቸው የበለጠ አመቺ እንደሆነላቸው ተናግረዋል።

በመቄዶኒያ በነበራቸው የሁለት ዓመታት ቆይታ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው፣ በተለይ ደግሞ በሕክምና በኩል የሚደረግላቸው እንክብካቤ በጣም ጥሩ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በመቄዶኒያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከ7,800 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...