Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት አሥር ፕሮጀክቶቹ መጓተታቸውን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የድርጅቱ የተፈቀደ ካፒታል 20 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል

ባለፉት ዓመታት እየተከናወኑ ነበሩ ከተባሉ 50 ፕሮጀክቶች መካከል 40 ያህሉ ዘንድሮው ቢጠናቀቁም፣ አሥሩ በተለያዩ ችግሮች መጓተታቸውን፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ሰኞ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፣ አሥሩ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ችግሮች መጓተታቸውን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በሪሶ (ዶ/ር) በሰጡት ገለጻ፣ እየተሠሩ ከነበሩ 50 ፕሮጀክቶች ውስጥ በዘንድሮው ዓመት 40ዎቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል፣ አሥር የተጓተቱ ፕሮጀክቶች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

ተጓተቱ የተባሉት ፕሮጀክቶች የት እንደሚገኙ በተመለከተ፣ ‹‹ወሮታ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቦታዎችም ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ ሞጆና ቃሊቲ ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ ፕሮጀክቶቹ በጊዜ ማለቅ አለባቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቶች የተጓተቱበት ምክንያት ‹‹አንዱ በማኔጅመንት ችግር ሊሆን ይችላል፤›› ብለው ድርጅቱን ወክሎ የሚሠራ የአማካሪ ድክመት፣ የገበያ ወጣ ገባ ማለት፣ የዕቃዎች ዋጋ መጨመር፣ የሲሚንቶ እጥረትና የመሳሰሉት ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ምክንያት መሆናቸውን በሪሶ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በወቅቱ መፍትሔ ሰጥቶ በጊዜ መሥራት ላይ ችግር ስላለብን፣ እዚህ ላይ መሥራት አለብን ብለን ዓይተናል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በትኩረትና በክትትል እንዲጠናቀቁ እንደሚደረጉ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በአጠቃላይ ሥራዎቹ ሲመዝኑ አፈጻጸሙ 97 በመቶ መሆኑን፣ አሥሩን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ችግሮቻቸውን ለቦርድ እንዳቀረቡ፣ ምን መደረግ እንዳለባቸው እንደተለዩና ድጋፍ በማድረግ የሚያስቀጥሏቸው እንዳሉም አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የድርጅቱ የተፈቀደ ካፒታል 20 ቢሊዮን ብር እንደሆነና ከዚህ በላይ ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሒሳቦችን በጊዜ መዝጋት አስፈላጊ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጉሙሩክ ማስተባበሪያ ጂቡቲ ቅርንጫፍ አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት፣ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ቶን በኮንቴይነርና ከኮንቴይነር ውጪ (containerized and non-containerized) ደረቅ ጭነት፣ በጂቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

ከዚህም ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት (84 በመቶ) በዩኒ ሞዳል፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቶን በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓት እንደተጓጓዘ ሪፖርቱ ያትታል፡፡

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ወደ አገር ውስጥ ከኮንቴይነር ውጪ (non-containerized) ከተጓጓዘው ከአምስት ሚሊዮን ቶን በላይ ደረቅ ጭነት ውስጥ ማዳበሪያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቶን (19.9 በመቶ)፣ ስንዴ ከ810 ሺሕ በላይ ቶን (15.7 በመቶ)፣ ብረት ከ427 ሺሕ በላይ ቶን (8.3 በመቶ)፣ እንዲሁም ሌሎች ጭነቶች ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ (56 በመቶ) ነው ተብሏል፡፡

ማዳበሪያ በወቅቱ ባለመቅረቡ በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ቅሬታ እንዳቀረቡ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ማዳበሪያ በማጓጓዝ ረገድ የገጠመው ችግር ካለ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡

ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት በሪሶ (ዶ/ር)፣ ‹‹በጊዜ ያለ መምጣቱና ያለ መገዛቱ በእኛ ላይ በመጨረሻ መጣደፍና የትራንስፖርት ሥራን የተጣበበ ያደርጋል፡፡ ክልሎች ማዳበሪያውን የሚጠብቁት በክረምት ነው፣ እኛም ደግሞ በዚያው ልክ ማድረስ አለብን፡፡ ግን በእኛ በኩል ሲመጣና ጂቡቲ ሲራገፍ ወዲያውኑ እንዲደርስ ከፍተኛ ርብርብ አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በጊዜ ባለመገዛቱና ባለመቅረቡ ትራንስፖርት ላይ ችግር ይፈጥርብናል፡፡ ለዚህም መንግሥት ያስቀመጠው አቅጣጫ አለ፣ አሁንም የጋራ ውይይት ጀምረናል፡፡ በ2016 ዓ.ም. እንዴት በጊዜ ማቅረብ አለብን የሚል ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ስለሆነ ችግሩ ይቀረፋል ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል ለአምራችና ላኪዎች የሚያግዝ 30 ባለፍሪጅ ኮንቴይነሮች ተገዝተው ዝግጁ መደረጋቸውን፣ በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬ ላኪዎች ቢጠይቁ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 47 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን፣ ከ41 ቢሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ ወጪ እንዲደረግ ታቅዶ ከ36 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን፣ ከአምስት ቢሊዮን በላይ ትርፍ ለማግኘት ታቅዶ፣ 6.06 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት መቻሉም ተብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች