Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጤፍ ዋጋ በመጨመሩ በልተው ለማደር መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

የጤፍ ዋጋ በመጨመሩ በልተው ለማደር መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ከጤፍ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የእንጀራ ዋጋ በመጨመሩ በልተው ለማደር መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ሰሞኑን የአንድ እንጀራ ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረበት 17 ብር ወደ 22 እና 24 ብር ከፍ በማለቱ፣ ገዝተው ለመጠቀም ተቸግረዋል፡፡

እንጀራን ጋግረው ለመጠቀም ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን የተናገሩት እንዲት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እናት፣ የሚከፈላቸው የ3,000 ብር ደመወዝ ከወር ስለማያደርሳቸው በብድር እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

እንጀራን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪም እንዳማረራቸውም እኚሁ እናት አክለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የእንጀራ ዋጋ በአንድ ጊዜ ከአምስት እስከ ሰባት ብር መጨመሩን የተናገረው ወጣት ሻምበል ቢሆነኝ፣ ወጣቱ እንዳለው ከሆነ እንጀራን በቤት እንኳን ለማስጋገር አከራዮች ‹‹መብራት ይቆጥርብናል›› በማለት ፈቃደኛ ስለማይሆኑ እየገዛ ለመብላት መገደዱን ተናግሯል፡፡

በዚህም ሰሞኑን በእንጀራ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ከሚከፈለው የወር ደመወዝ ጋር ፈፅሞ የማይመጣጠን ነው ሲል አብራርቷል።

እንጀራ ሻጮችን ዋጋ ለምን እንደጨመሩ ሲጠይቃቸው፣ ‹‹ጤፍ ጨምሯል ስለተባልን ነው፤›› እንደሚሉት ገልጿል።

በአንዳንድ የእንጀራ መሸጫ ሱቆች ሪፖርተር ተዘዋውሮ ምልከታ ባደረገበት ወቅት፣ የእንጀራ ዋጋ ከ14 ብር ጀምሮ 17፣ 22 እና 24 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። የእንጀራ መሸጫ ዋጋ በዚህን ያህል የዋጋ ልዩነት ለምን እንዳሳየ ነጋዴዎች ሲጠየቁ የእንጀራው መወፈርና መሳሳት፣ እንዲሁም በጤፉ ላይ የሚቀላቀለው እህል መብዛት እንደሆነ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ስለዋጋው ጭማሪ ደግሞ የጤፍ ዋጋ ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ እንደሆነም ጠቁመዋል። ተደረገ የተባለው የዋጋ ጭማሪ በመርካቶ እህል በረንዳ ባሉ መጋዘኖችም እንደታየ የሪፖርተር ጋዜጠኞች ቅኝት ባደረጉበት ወቅት ለመታዘብ ችለዋል።

ብዙ የጤፍ አቅርቦት እንደሌለና የሚመጣው ጤፍ ደግሞ ዋጋው እየጨመረ መሆኑን አንዳንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነጋደዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በተለይ በቢሾፍቱና በዱከም አካባቢ ወደ አዲስ አበባ የሚገባውን ጤፍ፣ በአካባቢው ያሉ ሆቴሎች አርሶ አደሮችም ሆኑ ነጋዴዎች አዲስ አበባ አምጥተው ከሚሸጡበት ዋጋ በላይ ስለሚገዟቸው በአቅርቦቱ ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ ግጭት ከጎጃምና አካባቢው ወደ መዲናዋ የሚገባው ጤፍ መቅረቱ ደግሞ አሁን ለታየው የዋጋ ጭማሪ ሌላው መንስዔ መሆኑን ነጋዴዎቹ አብራርተዋል።

ሰኞ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም፣ በእህል በረንዳ በነበረው ወቅታዊ ግብይት ማኛ ነጭ ጤፍ 13,500 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ሠርገኛ ጤፍ ከ10,000 ብር እስከ 10,700 ብር፣ እንዲሁም ቀይ ጤፍ ከ9,500 ብር እስከ 10,000 ሺሕ ብር ሲሸጥ መቆየቱን ለመመልከት ተችሏል።

ሌሎች ነጋዴዎች እንዳሉት ከሆነ ደግሞ በጎጃም በኩል የሚገባው ጤፍ መቅረቱ የተወሰነ እጥረትን ቢያስከትልም፣ ከአርባ ምንጭና ከባሌ፣ እንዲሁም ከሌሎች አካባቢዎች የሚገባው ጤፍ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፣ አከፋፋዮችም የቻሉትን ያህል እየጫኑና እየወዱ ነው። በዚህም የምርት እጥረት አለ የሚባለውን እንደማያምኑበት ነው የተናገሩት።

የምዕራብ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ኃላፊ የሆኑት አቶ በላይ ቶሌራ እንዳሉት ደግሞ፣ በአሁኑ ወቅት በመጋዘናቸው ቀድሞ የገባ 3,000 ኩንታል ጤፍ መኖሩን ተናግረው፣ በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ እየታየ ባለው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት፣ እንዲሁም ከማዳበሪያ ዋጋ መወደድ ጋር ተዳምሮ የጤፍ ዋጋም መጨመሩን ተናግረዋል።

በየአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር የሚመረተው ምርት በወቅቱ እንዳይደርስ እያደረገው እንደሚገኝ አቶ ቶሌራ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከአርሶ አደሩም ሆነ ከአቅራቢዎች ነጭ ጤፍ በ8,600 ብር ገዝተው በ9,200 ብር እየሸጡ እንደሚገኙ፣ ቀይ ጤፍ ደግሞ 7,700 ብር እየተሸጠ ይገኛል ብለዋል። በአማካይ ከ700 እስከ 800 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ነው የተናገሩት።

‹‹ገበያው ቢጨምርም ምርቱ እንዳይጠፋ እየሠራን ነው፤›› ያሉት አቶ በላይ፣ በመንገድ ላይ እህል የጫኑ ተሳቢ መኪኖች መኖራቸውን አክለው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ እየተባለ ባለው ልክ የዋጋ ጭማሪ ስለመኖሩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግሯል።

የእሑድ ገበያ የሸማቾች ኅብረት፣ እንዲሁም መንግሥት ያስገነባቸውና የሚቆጣጠራቸው የገበያ ማዕከላት ላይ ብቻ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ የቢሮው ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሰውነት ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ የነፃ ገበያ እንደመከተላችን መጠን ‹‹ይህ ጨመረ፣ ይኼኛው ቀነሰ›› ብለን የምንከታተልበት አግባብ የለም ብለዋል።

ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ካሉ ለምሳሌ ያላግባብ ምርትን የመከዘንና የማከማቸት እንቅስቃሴ ካለ እሱን ልንከታተል እንችላለን እንጂ በእያንዳንዱ ምርት የዋጋ ቁጥጥር ልናደርግ አንችልም ብለዋል።

ጨመረ በተባለው ልክ መረጃ እንደሌላቸው የተናገሩት አቶ ሰውነት፣ ነገር ግን ከፀጥታና ሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ እንደ ልብ እየሆነ አይደለም ብለዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ክትትል እያደረግን ነው ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...