Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዓረቢያ ድንበር ጠባቂዎች መገደላቸውን ሒዩማን ራይትስዎች አስታወቀ

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዓረቢያ ድንበር ጠባቂዎች መገደላቸውን ሒዩማን ራይትስዎች አስታወቀ

ቀን:

  • መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ ውጤቱን እንደሚያሳውቅ ተናግሯል

የየመንን ድንበር አቋርጠው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለመግባት የሞከሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዓረቢያ የድንበር ጠባቂዎች መገደላቸውን፣ ሒዩማን ራይትስዎች ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ ውጤቱን እንደሚያሳውቅ ተናግሯል፡፡

ሒዩማን ራይትሰዎች ሰኞ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከመጋቢት 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ጥገኝነት ለመጠየቅ ድንበር ለማቋረጥ የሞከሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ጭካኔ የተሞላበት የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል ብሏል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ የተሻለ የተባለውን ገጽታዋን ለዓለም ለማሳየት በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ሀብት እንደምታወጣ የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ በተቃራኒው ግን ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ ግፍ የተሞላበት ግድያ እንዲፈጸም እያደረገች መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት እንደ ፖሊሲ ተይዞ ግድያው ተፈጽሞ ከሆነ፣ ድርጊቱ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊባል እንደሚችል በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ሒዩማን ራይትስዎች ያነጋገራቸው ስደተኞች፣ በድንበር ጠባቂዎቹ ተኩስ እንደ ዝናብ እንደወረደባቸው እንደነገሩት አስታውቋል፡፡ ድንበር ጠባቂዎች ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በመጠቀም በቅርብ ርቀት ያገኟቸውን ሴቶችንና ሕፃናትን መግደላቸውን፣ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞችን የትኛው የሰውነት ክፍላችሁ ላይ እንተኩስ በማለት ይጠይቋቸው እንደነበር በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

የድንበር ጠባቂዎቹ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለመግባት የሞከሩትን ብቻ ሳይሆን፣ አምልጠው ወደ የመን ለመመለስ የሞከሩትንም ጭምር ተቀጣጣይ ፈንጂ በመጠቀም እንደገደሏቸው ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች የ17 ዓመት ስደተኛና ሌላ ስደተኛን (ሁለት ሴት ስደተኞችን) እንዲደፍሩ እንዳስገደዷቸውና ታዳጊው ስደተኛ አልደፍርም ያለውን ሌላ ስደተኛ መግደላቸውን መናገሩን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

የጅምላ ግድያው የተፈጸመው ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዕይታ ቅርብ ባልሆነ በረሃ ውስጥ መሆኑን፣ የሒዩማን ራይት ዎች የስደተኞች ጉዳይ ተመራማሪ ናዲያ ሐርድማንን ጠቅሶ ሪፖርቱ ዘግቧል፡፡ ተመራማሪዋ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማውጣት የጎልፍ ባለሙያዎችን የሚቀጥረውና ግዙፍ መዝናኛዎችን የሚያደራጀው የሳዑዲ መንግሥት የሚፈጽመውን አሰቃቂ ግፍ ለመደበቅ መሣሪያ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

ሒዩማን ራይትስዎች 42 ኢትዮጵያውያንን ቃለ መጠይቅ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 38 ያህሉ ጥገኝነት ፈልገው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለማቋረጥ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው ብሏል፡፡ ቀሪዎቹ አራቱ የእነዚህ ስደተኞች የቅርብ ቤተሰቦች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሪፖርቱ በሳዑዲ ዓረቢያ 750,000 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ገልጾ፣ በርካቶች በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የተወሰኑት ደግሞ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሳቢያ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ናቸው ሲል አክሏል፡፡

ሒዩማን ራይትስዎች እ.ኤ.አ. 2014 ጀምሮ የየመንን ድንበር ተሻግረው በሚሄዱ ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ ሲከታተልና ሲመዘግብ መቆየቱን አስታውቋል፡፡ በሪፖርቱ የተመለከተው ግድያም የታቀደና ስደተኞችን ዒላማ ያደረገ መሆኑን ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

ስደተኞች የኤደን ባህረ ሰላጤን በጀልባዎች ከተሻገሩ በኋላ በየመን በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት፣ በሁቲ አማፂያን ሥር የምትገኘውና ለሳዑዲ ድንበር ቅርብ ወደ ሆነችው ሳዳ ግዛት እንደሚያሻግሯቸው ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎች በአስቸኳይ መግደል ማቆም እንዳለባትና የሚመለከታቸው ተቋማትና መንግሥታትም ይህን የግድያ ፖሊሲዋን እንድታቆም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጫና እንዲያደርጉ ሒዩማን ራይትስዎች ጠይቋል፡፡ አክሎም ጉዳዩ ያሳስበናል የሚሉ መንግሥታት በሳዑዲ ዓረቢያና በሁቲ አመራሮች ላይ ማዕቀቦችን መጣል አለባቸው በማለት፣ በስደተኞች ላይ የተፈጸመው ግድያ በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸም ወንጀል ጋር ስለመስተካከሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፍ አጣሪ ቡድን መቋቋም አለበት ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በተመለከተ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ አጠር ያለ ባለአራት አንቀጽ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በዚህ መግለጫው ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ የረዥም ጊዜ ጠንካራና ጥሩ የሚባል ግንኙነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን ጠቅሶ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ በአስቸኳይ የማጣራት ሥራ አካሂዶ ውጤቱን እንደሚያሳውቅ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ አላስፈላጊ ግምቶችን ከመግለጽ ተቆጠቡ ብሏል፡፡ ሚኒስቴሩ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለው መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ሪፖርተር የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ አላስፈላጊ ግምቶች ያላቸውንና በአዲስ አበባ ከሚገኘው የሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ጋር የጀመረው ውይይት ካለ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ቢደውልም፣ የሚኒስቴሩን ቃል አቀባይን ማግኘት አልተቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...