Saturday, September 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የዋጋ ንረቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ ልጓም ይበጅለት!

ከዚህ ቀደም በኮሮና ወረርሽኝ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ የምግብና የምግብ ነክ ምርቶች፣ የግንባታ ዕቃዎችና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በየቀኑ ወደ ላይ እያሻቀበ ነው፡፡ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ደግሞ በጤፍና በሌሎች የምግብ ምርቶች ላይ እየታየ ያለው አስደንጋጭ የዋጋ ንረት መግቻ ካልተደረገለት፣ የዜጎች ሕይወት ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ሰብዓዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለዋጋ ንረት መከሰት በመሠረታዊነት ከሚጠቀሰው የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጠም በተጨማሪ፣ ወትሮም ሥርዓተ አልባ የሆነው የግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋለው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የዜጎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡ ይህ ችግር ፍቱን የሆነ የፖሊሲ ውሳኔ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ በበሳል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግራና ቀኙ በሚገባ ተጠንቶ ለመፍትሔ የሚረዳ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው የፖሊሲ ውሳኔ ላይ ከመድረስ በፊት፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምክረ ሐሳብ ስለመገኘቱ ማረጋገጫ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው የገንዘብ ፖሊሲ መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ለበርካታ ዓመታት የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጿል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት የዋጋ ንረት በአማካይ የ16 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተስተዋለው ደግሞ ከዚህ አማካይ የዘለለና ከተጠበቀው በላይ ክስተት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ እንዳለው በማክሮ ኢኮኖሚውም ላይ ሆነ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ጉዳት አለው፡፡ የዋጋ ንረት ቋሚ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ትክክለኛ ገቢ እንደሚቀንስ፣ በድህነት የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እንደሚጎዳ፣ ንረቱ በቆየ ቁጥር ሥር የሰደደ ሥጋት እንደሚፈጥር፣ የዋጋ ንረት ይኖራል የሚለው ዕሳቤ በራሱ አባባሽ ሁኔታ ስለሚፈጥር በጊዜ መገታት እንዳለበት ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው አክሏል፡፡ ለዘለቄታዊ መፍትሔ የቅንጅታዊ አሠራር አስፈላጊነት፣ የአቅርቦት ማሻሻያ ዕርምጃዎች፣ መዋቅራዊ ዕርምጃዎች፣ የፊስካል ፖሊሲና የብሔራዊ ባንክ ልዩ ሚና በማለት በረዥም ጊዜና በአጭር ጊዜ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚረዱ ያላቸውን ውሳኔዎች አብራርቷል፡፡

እንደሚታወቀው ለዋጋ ንረት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው ለረዥም ጊዜ የቆየውን የዋጋ ንረት ችግር ለመቅረፍ የብዙ ወገኖችና ዘርፎች ቅንጅትና ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል በመስኩ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን ተሳትፎ እንዲኖር ከማድረግ በተጨማሪ፣ በተለይ በመንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አካላት አቅምና የአመራር ችሎታም መፈተሽ አለበት፡፡ የግብይት ሥርዓቱን ፈር ማስያዝ ያቃታቸው የዘርፉ መዋቅሮችና አመራሮች ጉዳይ በቅጡ ሳይፈተሽ፣ የእነሱ መቀናጀትና የመሳተፍ ጉዳይ ከፈረሱ ጋሪውን እንደማስቀደም ነው የሚሆነው፡፡ በምግብ እህሎችና በፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦትና ሥርጭት ውስጥ የተሰገሰጉ ሕገወጦች፣ የግብይት ሥርዓቱን እንደፈለጉ ሲፈነጩበት ማንም ሊያስቆማቸው ያልቻለው መንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ በሚታየው ዳተኝነት ምክንያት ነው፡፡ ይህ ዳተኝነት በሁለት ምክንያቶች የሚታይ ሲሆን፣ አንደኛው የጥቅም ተጋሪ በመሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በአቅም አልባነት ነው፡፡ በዚህ መሀል ግን የግብይት ሥርዓቱ ለሕገወጦች መፈንጫ ለሸማቾች ደግሞ ሲኦል ሊሆን ችሏል፡፡

የምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ ነገር መሆኑን በማመን የሚታረስ መሬት መጠን መጨመር፣ የመስኖ እርሻ ማስፋፋት፣ የኩታ ገጠም እርሻ ማበረታታት፣ የሜካናይዜሽን እርሻ ማስፋፋት፣ ቆላማ አካባቢዎችን እርሻ ማለማመድ፣ በስፋት ለፍጆታ የሚውሉ እንደ ስንዴና አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ሰብሎችን ምርታማነት መጨመርና የመሳሰሉ ፍላጎቶችና ዕቅዶች መኖራቸው መልካም ነው፡፡ እንዲሁም በሌሎች ሸቀጦችና አገልግሎቶች፣ በሲሚንቶ፣ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በትራንስፖርትና በመሳሰሉ ዘርፎች ያለውን የአቅርቦት ችግር ለመቅረፍ መታሰቡም ጥሩ ነው፡፡ ከእነዚህ ፍላጎቶች ጎን ለጎን ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን በመግታት መረጋጋት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በሰላማዊ መንገድ ተቋጭቶ፣ የሰዎችና የምርቶች አቅርቦት እንደገና እንዲጀመር ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ግጭቱ በተራዘመ መጠን የምርቶች አቅርቦት እየተስተጓጎለ የሚፈጠረው እጥረት የዋጋ ንረቱን ያባብሰዋል፡፡ ከሌሎች አካባቢዎች የሚገቡ ምርቶች ለሸማቾች በቂ ስለማይሆኑ፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን የከተማ ነዋሪዎች ኑሮ ያመሰቃቅሉታል፡፡ ሕዝባችን ገቢው ሳይጨምር በከባድ የዋጋ ንረት እየተመታ መቀጠል አይችልም፡፡

መንግሥት ከዚህ ቀደም ባጋጠሙ ኮቪድ፣ ግጭትና ድርቅ ሳቢያ በደረሱበት ጫናዎች ምክንያት የወጪ ፍላጎቱ መጨመሩ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ክስተቶች የገቢ ዕድገት በመቀነሳቸው ሳቢያ ከፍተኛ የፊስካል ተግዳሮት ፈጥረው የመንግሥት ገቢ ጉድለት በከፍተኛ መጠን መጨመሩም አይዘነጋም፡፡ የውጭ ብድርና ዕርዳታ መጠን በመቀነሱም መንግሥት ፊቱን ወደ አገር ውስጥ የብድር ምንጮች፣ በተለይም ወደ ብሔራዊ ባንክ አዙሮ ወጪውን ለመሸፈን መገደዱም እንዲሁ፡፡ በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት ግን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ሲባል መርሐዊ አቋም በመያዝ፣ ወጪው በእጅጉ መገደቡ በብሔራዊ ባንክ አማካይነት መገለጹ አይረሳም፡፡ መንግሥት በዚህ ደረጃ ወጪዬን በመቀነስ የበጀት ጉድለቱን እቀንሳለሁ ሲል፣ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ፕሮጀክቶቹ መካከል ግን ሰብዓዊ ፍጡራንን መዘንጋት እንደሌለበት ማሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሰሞኑን እየታየ ያለው የምግብ እህሎች ዋጋ ንረትን በተመለከተ፣ መንግሥት የሚፈለግበትን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ የተዝረከረከው የግብይት ሥርዓት ጥቂቶችን እያደለበ ብዙኃኑን እያስራበ ነው፡፡ የሰሞኑ ተከታታይ የዋጋ ንረት በቁርጠኛ አመራር መርገብ ካልቻለ መዘዙ የከፋ ነው፡፡

ቀደም ሲል ለመጠቆም እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ በአዋጭ ፖሊሲ የተደገፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካልተፈጠረ በስተቀር፣ አሁን ባለው ሁኔታ ወደኋላ እንጂ ወደፊት አንዲት ጋት መራመድ አይቻልም፡፡ በመላ አገሪቱ ሰዎችና ምርቶች በሚፈለገው ልክ ካልተዘዋወሩ የምርቶች አቅርቦት ይገታል፡፡ አቅርቦት ሲያንስ ደግሞ ፍላጎት በጣም ይጨምራል፡፡ በዚህ ላይ የግብይት ሥርዓቱ በወጉ ስለማይመራ ሸማቾች ምክንያታዊ ላልሆነ የዋጋ ንረት ይዳረጋሉ፡፡ መንግሥት ገበያው ውስጥ የሚረጨውን ገንዘብ ለመቀነስ ቃል ሲገባ በተግባር መታየት ይኖርበታል፡፡ በአገሪቱ በርካታ ሥፍራዎች የሰዎችና የምርቶች ዝውውር ሲገታ፣ ሊከተል የሚችለው እጥረት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች መጠን ሲቀንስ የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖር ማንም ይረዳዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ 20 በመቶ፣ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ይሠራል ማለቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን እየታየ ካለው አስፈሪ የዋጋ ንረት ጋር አብሮ የሚሄድ አይመስልም፡፡ የዋጋ ንረቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ ልጓም ይበጅለት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...