- ብሔራዊ ባንክ የሚሰጠው ቀጥታ ብድር ከ25 በመቶ በላይ እንዳያድግ ተወስኗል
በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ከፍተኛ የበጀት እጥረት ገጥሞት የነበረው መንግሥት፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ቀጥታ ብድር (Direct Advance)፣ ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ታወቀ፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ባስከተሉት የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ ወጪው በመጨመሩ ምክንያት ከፍተኛ የበጀት እጥረት ውስጥ ገብቶ የነበረው መንግሥት፣ ከብሔራዊ ባንክ በከፍተኛ መጠን መበደርን ጨምሮ በርካታ የገቢ ማስገኛ መንገዶችን ሲጠቀም እንደነበር ይታወሳል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት በቀጥታ (ገንዘብ በማተም) ሲያበድር የቆየ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው ሙሉ የበጀት ዓመት የሰጠው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ሪፖርተር የተመለከታቸው ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡
ገንዘቡን ከሚያበድረው ብሔራዊ ባንክና ለመንግሥት ሥራ ማስፈጸሚያ ከሚበደረው የገንዘብ ሚንስቴር የሪፖርተር ምንጮች የተገኘው መረጃም ይህንን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ከብሔራዊ ባንክ በተገኘው መረጃ መሠረትም የገንዘብ መጠኑ በአሥር ቢሊዮን ብር ከፍ ሊል እንደሚችል ነው፡፡
የበጀት ዓመቱ ከተጀመረ በኋላ የመጀመርያው ሩብ ዓመት እኪጠናቀቅ ድረስ 60 ቢሊዮን ብር ቀጥታ ብድር መወሰዱን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት አመላክቶ ነበር፡፡
ከዚህ 60 ቢሊዮን ብር ጋር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተጠራቅሞ የነበረው 236.5 ቢሊዮን ብር በቀጥታ ብድር የተገኘው ገንዘብ ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ በጥቅምት ወር ተቀይሮ እንደነበርም፣ መገንዘብ ሚኒስቴር ሁለተኛው ሩብ ዓመት የብድር መግለጫ ሪፖርት ላይ ተካቶ ነበር፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ላይ ግምገማ አድርጎ ነበር፡፡ ሪፖርተር የተመለከተው የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያመላክተው፣ በጥቅምት ወር ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ ከተቀየረው በተጨማሪ፣ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ከሁለተኛው ሩብ ዓመት ጀምሮ 120 ቢሊዮን ብር በቀጥታ ብድር ወስዷል፡፡
ይህም በመጀመርያው ሩብ ዓመት ወስዶ ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ ከለወጠው 60 ቢሊዮን ብር ጋር የዓመቱን የቀጥታ ብድር ዕዳ 180 ቢሊዮን ብር ያደርሰዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ከሁለት ወራት በፊት አውጥቶት የነበረው የሦስተኛው ሩብ ዓመት የብድር መግለጫ ሪፖርትን ጨምሮ ሦስቱም የብድር መግለጫ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት፣ እስከ ሦስተኛው ሩብ ዓመት መገባደጃ ድረስ 140 ቢሊዮን ብር በቀጥታ ብድር መወሰዱን ነበር፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ምንጭ እንደገለጹት፣ በአራተኛው ሩብ ዓመትም ተጨማሪ 40 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወስዷል፡፡ የአራተኛውን ሩብ ዓመት የብድር መግለጫ ሪፖርትም በቅርቡ ይፋ ሲደረግ፣ ይህም እንደሚታወቅ ከምንጩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከብሔራዊ ባንክ ምንጮች ለመረዳት እንደተቻለው፣ ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ ከተቀየረ በኋላ ወደ 130 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የቀጥታ ብድር መጠን ክምችት እስከ ሰኔ መጨረሻ ተመዝግቧል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት እየሰጠ ያለው የቀጥታ ብድር መጠን እየጨመረ መሆኑን፣ ይህም ከሌሎች ምክንያቶች ጋር፣ ለኑሮ ውድነት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን በማመን፣ ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. አዳዲስ አሠራሮችን ሲያስተዋውቅ የቀጥታ ብድርን በሚመለከት ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ ለመንግሥት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር መጠን ከ25 በመቶ በላይ ማደግ እንደማይችል መወሰኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በ2014 ሙሉ በጀት ዓመት ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት ሰጥቶት የነበረው የቀጥታ ብድር 76 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህንንም በ140 በመቶ በማሳደግ ነው በ2015 በጀት ዓመት ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ የሰጠው፡፡ ከዘንድሮ በጀት ዓመት ጀምሮ ግን ከ25 በመቶ በላይ ማደግ እንዳይችል ለማድረግ ነው የባንኩ ቦርድ ውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡