Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአይደር ሆስፒታል በመድኃኒት እጥረት ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

በአይደር ሆስፒታል በመድኃኒት እጥረት ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

ቀን:

ባለፉት ሦስት ወራት በካንሰር መድኃኒት እጥረት ምክንያት ብቻ ከ100 የሚበልጡ ታካሚዎች ሕይወታቸው ማለፉን፣ የትግራይ ክልል የአይደር ሆስፒታል አስታወቀ፡፡

በሆስፒታሉ በተለይም የካንሰር ሕሙማን የቀዶ ሕክምና የሚጠባበቁ የታካሚዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን፣ ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት እጥረት በመኖሩ በየጊዜው የሟቾች ቁጥር ከፍ እያለ መሆኑን፣ የአይደር ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ማዕከል ኃላፊ ዶ/ር ክብሮም ህሉፍ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳን ሆስፒታሉ በጦርነቱ ወቅት ከነበረው ሁኔታ አንፃር የመድኃኒት አቅርቦቱ እየተሻሻለ ቢሆንም፣ ከታካሚዎች ቁጥር አንፃር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

እጥረቱ ከተከሰተባቸው የሕመም ዓይነቶች የጡት ካንሰር መድኃኒት አቅርቦት እንደሌለ፣ በዚህ ሁኔታ እጥረቱ ከቀጠለ የሕመሙ ደረጃና የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊልቅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡  

በማዕከሉ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ከ500 በላይ ተመላላሽ ታካሚዎች እንደነበሩ ጠቁመው፣ በአጠቃላይ ከ1,200 እስከ 1,500 ታካሚዎች ወረፋ የሚጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በካንሰር መድኃኒት እጥረት ምክንያት ባለፉት አራትና አምስት ወራት ውስጥ በትንሹ 100 ሰዎች መሞታቸውን ነው ዶ/ር ክብሮም የገለጹት፡፡

የአይደር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብርሃ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው፣ በሆስፒታሉ ከጦርነቱ በኋላ የመድኃኒት አቅርቦት መሻሻል አሳይቷል ብለዋል፡፡ ከእነዚህም መድኃኒቶች ውስጥ የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ፣ የቲቢና የኢንሱሊን አቅርቦት እየተሻሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

‹‹ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የመድኃኒት አቅርቦቱ ያለውን እንሰጣለን ከማለት ውጪ፣ ምን ያህል እንደሚቀርብ እንኳን አናውቅም፤›› ሲሉ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ከጦርነቱ በፊት የመድኃኒቶች ዝርዝር ወጥቶ ለሁለትና ለሦስት ወራት የሚያስፈልገው የሚታወቅ መሆኑን፣ ይሁንና ከጦርነቱ በኋላ ምን ያህል እንደሚቀርብ እንደማይታወቅ አክለዋል፡፡

ለሰኔና ለሐምሌ  2015 ዓ.ም. የሚያስፈልጉ መድኃኒቶችና በሕክምና ግብዓቶች አስፈላጊዎቹ የትኞቹ ናቸው ብለው ቢጠይቁም መረጃ ማግኘት አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዚያ ውጪ የሚቀርቡት መድኃኒቶች በሪፈራል ሆስፒታል ደረጃ በቂ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተኝቶ መታከም አገልግሎት ፅኑ ሕክምና ክፍል (የአዋቂ፣ የሕፃናት) ውስጥ በአጠቃላይ 24 አልጋዎች እንዳሉ ያስረዱት ዶ/ር አብርሃ፣ 45 ጨቅላ ሕፃናት የሚታከሙባቸው 45 ክፍሎች በርካታ መድኃኒቶች የሚያስፈልጋቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ድንገተኛ ክፍል በዓላትን ጨምሮ ለ24 ሰዓታት የሚሠራ በመሆኑ፣ ለእነዚህ ሁሉ ክፍሎች የሚያስፈልጉ መድኃኒቶች በበቂ ሁኔታ አሉ ተብሎ የሚኮራባቸው አይደሉም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተያያዘም የጓንት እጥረት መኖሩን ገልጸው፣ ይህም ለባለሙያዎችም አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በደም ሥር የሚሰጡ መድኃኒቶች፣ የጨቅላ ሕፃናት፣ የእናቶችና ሌሎችም የመድኃኒት ዓይነቶች በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በእንክብል የሚወሰዱ የስኳር፣ በአጠቃላይ የልብና የሚጥል በሽታ መድኃኒቶች ከፍተኛ እጥረት እንዳለም አስታውቀዋል፡፡

በተለይ ለቀዶ ሕክምና የሚያገለገሉ የሰመመን መድኃኒቶች እጥረት መኖሩን ገልጸው የጓንትና የሕመም ማስታገሻዎች የአቅርቦት ችግሮች የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ወላድ እናቶች መውሰድ ያለባቸው መድኃኒቶች ከዚህ ቀደም ሲቀርቡ እንደነበር፣ ከጊዜ በኋላ አቅርቦቱ እየሳሳ ሲመጣ ደም ለሚፈሳቸው ብቻ እየተሰጠ ለማብቃቃት እየተሞከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቫይታሚን ‹ኬ› ሁሉም ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ መሰጠት ያለበት ቢሆንም፣ ባለው ከፍተኛ እጥረት ሳቢያ ማድረስ አለመቻሉም ተመላክቷል፡፡ የጭንቅላት ውስጥ ኢንፌክሽን ሲፈጠር፣ በአከርካሪ አጥንቶች የሚያጋጥሙ ኢንፌክሽኖች በእንክብልና በሽሮፕ የሚታከሙበት አማራጭ አለመኖሩን ገልጸው፣ ለእነዚህ ሕመሞች የሚሆኑ መድኃኒቶች ሲጠፉ ታካሚዎች እንደሚሞቱ ገልጸዋል፡፡

ለኩላሊት ዲያሌሲስ አገልግሎት ግብዓቶች ባለመኖራቸው ሕሙማን ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውንም አክለዋል፡፡ በምሳሌነት ያነሱትም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ከጦርነቱ በኋላ ያሉ ሦስት አራተኛ ታካሚዎች መሞታቸው ተገልጿል፡፡ ተኝቶ መታከምንና የፅኑ ታካሚዎች የሞት ምጣኔ በወሩ የሚሠላ መሆኑን፣ ከጦርነቱ በፊት ተኝቶ መታከም ስድስት በመቶ ያነሰ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ከጦርነቱ በኋላ ግን ተኝቶ መታከሚያ ክፍል የሚሞቱ የታካሚዎች ቁጥር አሥር በመቶ በላይ ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡ የፅኑ ታካሚዎች ከጦርነቱ በፊት የነበረው የሞት ምጣኔ 22 በመቶ እንደነበር፣ ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ 40 በመቶ እንዳለፈ ዶ/ር አብርሃ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና በአብዛኛው ከጦርነቱ በፊት 11 በመቶ የሞት ምጣኔ እንደነበረ፣ ከጦርነቱ ወዲህ ደግሞ ወደ ከ20 በመቶ በላይ ከፍ ማለቱንም አስታውቀዋል፡፡  

በሔለን ተስፋዬና በኢዮብ ትኩዬ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...