ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም አላቸው፡፡ የሕዝብ ቁጥራቸውም ቢሆን ትልቅ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢኮኖሚያቸውን፣ ፖለቲካቸውንና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው የመሄድ ወኔ አላቸው፡፡
ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ አባል የሆኑበት ብሪክስ ከተመሠረተ ሁለት አሠርታት እንኳን ባያስቆጥርም፣ በዓለም አዲስ አሠላለፍ እየፈጠረ ይገኛል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2001 የጎልድማን ሳክስ ግሩፕ ዋና ኢኮኖሚስት ጂም ኦኔል የጥናት ወረቀት ብራዚልና ሩሲያ፣ ህንድና ቻይና ላላቸው የዕድገት አቅም ትኩረት መስጠቱን ተከትሎ በ2009 እንደተመሠረተ የሚነገርለት ቡድኑ፣ በአሜሪካና በምዕራባውያን አጋሮቿ ተፅዕኖ ሥር ያለውን የዓለም አሠላለፍ ለመገዳደር እንደሆነም ሮይተርስ ይገልጻል፡፡
በአራቱ አገሮች የተመሠረተው ቡድን፣ በ2010 ደቡብ አፍሪካን አካቶ ብሪክስ (BRICS) የተባለ ሲሆን፣ ሁሉም አባላት ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች የተሰባሰቡበት የቡድን 20 አገሮች አባል ናቸው፡፡
በሩሲያ አነሳሽነት የተመሠረተው የብሪክስ አባል አገሮች የዓለምን 40 በመቶ ያህል ሕዝብ የያዙ ሲሆን፣ ከዓለም ኢኮኖሚ አንድ አራተኛውን ይሸፍናሉ፡፡
ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ አርጀንቲና፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ካዛኪስታንን ጨምሮ ከ40 በላይ አገሮች የአባልነት ጥያቄ ለብሪክስ ያቀረቡ ሲሆን፣ ነሐሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ተጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔም በጉዳዩ ላይ ይወያይበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ደቡብ አፍሪካ የአይሲሲ አባል አገር በመሆኗ በጆሀንስበርጉ ጉባዔ ባይሳተፉም የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ተገኝተዋል፡፡ የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ደ ሲልቫ፣ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ እንዲሁም የቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ዲንፒንግ ያልተገኙበት ጉባዔ፣ ዋና ጭብጥ ብሪክስና አፍሪካ የሚል ነው፡፡
በ15ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔዎች እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገላቸው 69 አገሮች ሲሆኑ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲንም በበይነ መረብ መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉ ይሆናል፡፡
የብሪክስ አጀንዳዎች
ብሪክስን ማስፋፋት የ15ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ አንዱ አጀንዳ ነው፡፡ 40 አገሮች ቡድኑን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎም ውይይት የሚደረግ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የኢኮኖሚ ጉዳይ ዋናው የጉባዔው አጀንዳ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ የአምስቱ አገሮች አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ከቡድን ሰባት አገሮች በወቅታዊ የኢኮኖሚ የመግዛት አቅም የበለጠ ነው፡፡
የብሪክስ አገሮች ከዓለም ጠቅላላ ምርት 26 በመቶውን ይይዛሉ፡፡ ይህን ያህል የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው አምስቱ አገሮች፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ውስጥ ድምፅ የመስጠት አቅማቸው 15 በመቶ ብቻ ነው፡፡
በደቡቡ ዓለም የሚስተዋለውን እንዲህ ዓይነቱን አድሎአዊ አሠራር ሚዛን ለመጠበቅና አሜሪካ የዶላር ዝውውር ላይ ማዕቀብ በመጣል እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀሟ፣ የብሪክስ አባል አገሮች በተናጠልም ሆነ በጋራ የአሜሪካ ዶላር ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ እንዲመክሩ አስገድዷቸዋል፡፡ በራሳቸው ገንዘብ እርስ በርስ ለመገበያየት እንዲሠሩም እንደ ምክንያት ሆኗል፡፡
ሆኖም በህንድና በቻይና ድንበር መካከል ያለው ውጥረት ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካና ብራዚል ከቻይናና ሩሲያ ጋር እንዳላቸው በጎ ግንኙነት ዓይነት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላቸው መሆኑ፣ አንድ ሆነው እንዳይጠነክሩ ሊያደርግ እንደሚችል ይነሳል፡፡
እያቆጠቆጠ ያለውን የብሪክስ አማራጭ ኢኮኖሚ ሆኖ መቅረብ ከአሜሪካና ከአጋሮቿ ጋር ያለውን ጂኦፖለቲካዊ ትስስር ማስቀጠል የሚሉ ጉዳዮችም ለብሪክስ የሚነሱ ናቸው፡፡
አልጀዚራ ተንታኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ እያደገ የመጣው ብሪክስ አሜሪካ መሩን የዓለም ሥርዓት ባንድ ጊዜ ከመተካት ይልቅ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ አማራጭ ሆኖ የሚያድግ ይመስላል፡፡ ይህም ቢሆን እየተናጠች በምትገኘው ዓለም ውስጥ ብሪክስ ራሱን የቻለ መንገድ እየተከተለ መሆኑ ምዕራባውያኑን ውጥረት ውስጥ የሚከት ነው፡፡