Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊአቅም ላነሳቸው የታቀደው ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› ነፃ ምርመራ

አቅም ላነሳቸው የታቀደው ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› ነፃ ምርመራ

ቀን:

በጤናው ዘርፍ በተለይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመመርመርና ለማከም የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ መሆን በርካታ ሕሙማንን የሚፈትን ነው፡፡

መላ ሰውነት ውስጥ ያሉ ክፍሎችን ለመመርመርና ችግሮችን ለይቶ ለማውጣት የሚያግዙ የምርመራ መሣሪያዎችም ሆኑ ኬሚካሎች የዚያኑ ያህል ውድ ናቸው፡፡

መንግሥት በጤና መድን ፈንድም ሆነ ከፍለው መታከም ለማይችሉ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ቢያቀርብም፣ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን በነፃ ወይም በዝቅተኛ ዋጋ ማግኘት ግን ቀላል አይደለም፡፡

- Advertisement -

በመንግሥት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በተመላላሽም ሆነ ተኝተው የሚታከሙ፣ ከጨቅላ ሕፃናት እስከ አዋቂ ያሉት የላቦራቶሪ ምርመራ ለማድረግ በየግል ዳያግኖስቲክ ማዕከላት ማቅናታቸውም የተለመደ ነው፡፡

አንድ ጊዜ ወይም በተደጋጋሚ ለሚታዘዝላቸው የተለያዩ ምርመራዎችም በሺዎች የሚቆጠሩ ብሮችን ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ገንዘቡን አግኝቶ ምርመራውን ማድረግ ከሕመማቸው በላይ የሚያስጨንቃቸው ደግሞ ቀላል አይደሉም፡፡ የኪሳቸውን አራግፈው፣ ዘመድ አዝማድ ጠይቀው ምርመራቸውን የሚያከናውኑም አሉ፡፡

የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር)፣ ጤና ሚኒስቴር ባስጀመረው የዘንድሮ በጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት ላይ እንደተናገሩትም፣ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ዜጎች ከፍለው መታከም ባለመቻላቸው በተለያዩ የጤና እክሎች ይቸገራሉ፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሕክምና ባለሙያዎች በሙያቸው፣ የላቦራቶሪ ባለቤቶች ደግሞ ቁሳቁሳቸውንና የሰው ኃይላቸውን ተጠቅመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በተለይ የክረምት ወቅት በመንግሥትም ሆነ በግል በርካቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡበት ነው፡፡

በዓመቱ ወቅት ጠብቀው የበጎ ፈቃድ የሕክምና አገልግሎት ከሚሰጡ የሕክምና ተቋማት ፓዮኒየር ዲያግኖስቲክ ማዕከል፣ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ፣ የሕክምና ባለሙያዎችና ሌሎችም በርካቶች ይገኛሉ፡፡

የእነዚህ ተቋማት ነፃ የበጎ አገልግሎት ተግባር ማከናወን ደግሞ ከፍለው ሕመማቸውን ለማወቅና ለመታከም ለማይችሉ ተስፋ ነው፡፡

በአብዛኛው ፒያሳ አካባቢን መነሻው አድርጎ የታክሲ ኮንትራት አገልግሎት የሚሰጥ ወጣት እንደነገረን፣ በሥራው በርካታ ሕሙማን ለላቦራቶሪ ምርመራ የሚከፍሉት በዝቶባቸው ትተው የሚሄዱበት አጋጣሚ ማየቱን ነግሮናል፡፡ የማይዘነጋቸው ደግሞ የኮንትራት አገልግሎት ሰጥቶ ለላቦራቶሪ ምርመራ ከቤታቸው ያመጣቸውን አንድ ጡረተኛ ነው፡፡

ታክሲው ውስጥ ሲገቡ ቅናሽ እንደሚያደርግላቸው የጠየቁት እኚህ ሰው፣ ለምርመራ ከሄዱበት ማዕከል የታዘዘላቸውን የምርመራ ዓይነቶች ለማግኘት 14 ሺሕ ብር አካባቢ በመጠየቃቸው ሳይመረመሩ መመለሳቸውን ታዝቧል፡፡ ‹ቤቴ አርፌ ተቀም˜ ብሞት ይሻላል ከየትም አምጥቼ ልመረመር አልችልም› ብለውት እንደነበርም ያስታውሳል፡፡

እንደነዚህ ዓይነት ክፍተቶች ለመሙላት በተለያዩ ጊዜያት በበጎ ፈቃድ ነፃ የላቦራቶሪ ምርመራ ከሚሰጡ ተቋማት አንዱ ውዳሴ ዳያግኖስቲክ ማዕከል ነው፡

ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› በሚል በጳጉሜን ነፃ የምርመራ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ማዕከሉ፣ ዘንድሮም ለ5,000 ሰዎች ነፃ የሲቲስካን፣ የኤምአርአይ፣ የአልትራሳውንድና የላቦራቶሪ ምርመራዎችን የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ማዕከሉ ለ5,000 ሰዎች ነፃ የላቦራቶሪ ምርመራ የሚሰጥ መሆኑን አስመልክቶ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ፣ የምርመራው ተጠቃሚ የሚሆኑት ከመንግሥት የሕክምና ተቋማት በሐኪም የተጻፈ ማዘዣ ያላቸውና በማዕከሉ የሚሰጡ ምርመራዎችን ለማድረግ በአቅም ማነስ ምክንያት ማድረግ የማይችሉ ናቸው፡፡

ሕሙማኑ ምርመራውን ለማግኘት ከነሐሴ 16 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በ9888 ወይም በ0940040404 ወይም በ0940050505 መመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታትም ለ52 ሺሕ ዜጎች ነፃ የምመራ አገልግሎት የተሰጠ መሆኑን ማዕከሉ ያስታወቀ ሲሆን፣ ዘንድሮ ጤና ሚኒስቴር የግል ጤና ተቋማት ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ነፃ ምርመራውን ለማድረግ ዝግጅት መጨረሱን ገልጿል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት የሚመጡ ሰዎች የሚመረመሩትን የምርመራ ዓይነት በዝርዝር ይዘው እንዲመጡ፣ ዓምና ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ‹ጠቅላላ ምርመራ› የሚል ማዘዣ ይዘው የሚመጡ እንደነበር የማዕከሉ የአድቫንስድ ላቦራቶሪ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

‹‹የነፃ ሐክምናው ዓላማ ነፃ ሕክምናን ለመስጠት ሳይሆን አቅም ለሌላቸውና ምርመራውን ከፍለው ለማግኘት ለማይችሉ ነፃ ምርመራ ማድረግ ነው፤›› ያሉት ደግሞ የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት ኃይሉ ናቸው፡፡

ከመንግሥት ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ለሚመጡት ቅድሚያ እንደሚሰጥ፣ ‹እኔ አልችልም› ብለው የሚናገሩ ሰዎችም አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሐኪም ማዘዣ ይዞ መምጣትም እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

አብዛኛው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን ለማድረግ እንደሚቸገር በማስታወስም፣ በጣም የሚቸገሩ ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ነፃ ምርመራው በጳጉሜን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ወራት እንደሚቀጥል ነገር ግን ተመርማሪዎች ቀድመው በተሰጠው ጊዜ መመዝገብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ከማዕከሉ ባገኘነው መረጃ መሠረት፣ የሲቲስካን ምርመራ ትንሹ የሚጀምረው ከ2,600 ብር፣ የኤምአር አይ ከ5,300 ብር፣ የአልትራሳውንድ ከ550 ብር ነው፡፡

ጤና ሚኒስቴርም ከቅዱስ ጳሎሎስ ሜዲካል ኮሌጅ ጋር በመተባበር የበጎ ፈቃድ የጤና ምርመራ አገልግሎት ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. አስጀምሯል፡፡

ለሳምንት የሚቆየውና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ራስ ኃይሉ ስፖርት ማዕከል የተጀመረው ምርመራ፣ የዓይንና የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር፣ የጡት ካንሰርና የተለያዩ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ምርመራ የሚሰጥ መሆኑን ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...