Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹የሴቶች የነፃነት ጊዜ›› ክብረ በዓል

‹‹የሴቶች የነፃነት ጊዜ›› ክብረ በዓል

ቀን:

የተጠሙ አበቦች በእጅጉ ይናፍቁታል፡፡  የሰማይ ወፎችም ቢሆኑ ተሰናድተው  ይጠብቁታል  ቤታቸውን ይሠራሉ ቀለባቸውን  ያከማቻሉ  የምድር አራዊትም ጎሬአቸውን አርቀው  በመማስ  አድፍጠው  መምጣቱን ያማትራሉ፡፡ ከብቶችም በመስኩ ይቦርቃሉ ሰዎችም የቻሉትን ያህል ከእህሉም ከእንጨቱም አሰባስበው  የራቀውን አቅርበው  ወራት ቆጥረው  በየዓመቱ ይዘያየራሉ።  በውኃ ጥም ላንቃቸው የደረቀና ከፀሐዩ ብዛትም የተሰነጣጠቁ  ማሳዎች  ናፍቆታቸው የጉድ ነው። ከሚነደው በረሃ እስከ  ላይኛው ተራራ  ከሸለቆ እስከ  ሜዳው ከደጋ እስከ ቆላው  ከገጠር እስከ ከተማው ከገበሬ እስከ እረኛው  ይወዱታል። ከዚህም በመነሳት በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን  በልዩ ዝግጅት ከሚጠብቁት ወራት ውስጥ ክረምት አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም ክረምት ለኢትዮጵያ አርሶ አደርም ሆነ አርብቶ አደር  የጀርባ አጥንት  ነው። ገበሬው ማሳውን አለስልሶ ማረሻውን አሥልቶ የሚጠብቅበት ወቅት ነው፡፡ ከተሜውም ቢሆን  የመኖር ዋስትናው በገበሬው ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የክረምቱ መምጣት  ያስደስተዋል፡፡

ክረምቱም ቢሆን ቀጠሮውን አክብሮ ወቅቱን ጠብቆ በጉጉትና በናፍቆት የሚጠብቁትን ፍጥረት ሁሉ  የልባቸውን መሻት  ለመከወን ከመምጣት አይቦዝንም። የተጠሙ ጠጥተው ይረካሉ፣  የጎደሉ ወንዞች ይሞላሉ፣ ተራሮችም አረጓዴ ይለብሳሉ፣  ሞተዋል ጠፍተዋል የተባሉ ዕፀዋት አንሰራርተው ይነሳሉ፡፡ ደርቀዋል የተባሉ ሐይቆች ይሞላሉ። ማሳ ላይ የተበተኑ ሰብሎች ሥራቸው ወደ ታች ይጠልቃል፣ ጫፋቸው ወደ ላይ ይዘልቃል።

ክረምት ይዞት የማይመጣው ነገር የለም፡፡ ሰኔ አጋማሽ ላይ አቀባበል  የተደረገለት ክረምት ነሐሴ አጋማሽ ላይ የአሸኛኘት ዝግጅቱ ይጀምራል። ክረምቱ ተጠናቆ ቦታውን ለብራው ለመፀው (የአበባና የነፋስ ወቅት) ሊያስረክብ እንደሆነ የሚጠቁሙ ተፈጥሯዊና ማኅበረሰባዊ  ምልክቶች ጉልተው ይንፀባረቃሉ።

- Advertisement -

 የደፈረሱ ወንዞች መጥራት ይጀምራሉ፣ በየጫካው የወፎች ጩኸት ይበረክታል፣  ጥጆች በመስኩ ይቦርቃሉ፣ በሮችም ያገሳሉ፣ ተራሮች ባረንጓዴ ተክል ያጌጣሉ፣ አበቦች  ለመፈንደቅ ቀን ይቆጥራሉ፣ ሰብሎች ሁሉ እርግዝና ላይ ናቸው።

የሰው ልጆችም በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በተራቸው የክረምቱን መገባደድ  ለማብሰር፣ ችቦ ይዘው ብርሃን ልናይ ነው ሲሉ፣ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ዘንድ  የምትጸመውን ‹‹የጾመ ፍልሰታን›› መጠናቀቅ  በማስመልከት የብርሃን ችቦ ለኩሰው  ሙልሙል ዳቦ ጋግረው  በሆያ ሆዬ ጭፈራ አጅበው  ይሸኙታል።

ሌላው  የክረምቱን  መገባደድ  ከሚያበስሩት ክዋኔዎች መካከል  በሴቶች በተለይ ደግሞ በልጃገረዶች  ዘንድ  ተወዳጅና ተናፋቂ የሆነው  የአሸንዳና ሻደይ  እንዲሁም  የአሸንድየና ሶለል በዓል አንዱ ነው። በዓሉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ክረምቱ ሊገባደድ ሲቃረብ ከቡሄ በዓል ቀጥሎ ከወርኃ ነሐሴ አጋማሽ  በትግራይ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በላስታ፣ በሰቆጣና በቆቦ  አካባቢዎች  በውብ ልጃገረዶች ደምቆ የሚከበር በዓል ነው። ይህም በዓል እንደየቦታው ልዩነቶች አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶሎልና ሻደይ የሚል ስያሜ ይዞ በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ይከበራል።

በክረምት ከሚበቅለው ረዥም ለምለም ሳር ስያሜው እንዳገኘ የሚነገርለት ይህ በዓል በትግራይ አሸንዳ፣ ዓይኒ ዋሪ፣ ማሪያ፣ በሰቆጣ ሻደይ፣ በላሊበላ አሸንድዬ፣ በቆቦ ሶለል ተብሎ ሲጠራ የወል ትርጉሙ ለምለም (እርጥብ ሳር) ማለት እንደሆነ ይነገርለታል።

በዓሉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ሕዝቦችን  በአንድነት ፈትል የሚያጋምድ፣  ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን  የሚዘምር  ባህልና ወጋቸውን የሚያሳይ  ታሪካዊ በዓል እንደሆነ ይነገርለታል።

በዓሉ ልጃገረዶች ባደባባይ ነፃነታቸውን የሚገልጹበት ፍላጎትና ምኞታቸውን  የሚተረጉሙበት፣ ከመቼውም በላይ አምረውና ተውበው ከእኩዮቻቸው ጋር  የሚቦርቁበት ድንቅ የነፃነት በዓል ነው።

በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 21 ባሉት ቀናት የመንደሩ ሴቶች አምረውና ተውበው በቡድን በቡድን በመሆን በየሠፈሩ እየዞሩ ሲጨፍሩ የሚውሉበት፣ ያላገቡት ሴቶች በውበታቸውና በአጨዋወት ችሎታቸው ከጎረምሶች ዓይን ገብተው ለትዳር የሚታጩበት፣ ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጭ የሚሆኑበት የነፃነት ጊዜ ነው፡፡ ይህ የአሸንዳ ሰሞን።

ዝናብ የጠገበው ምድር አረንጓዴ ለብሶ፣ ሳር ቅጠሉ አብቦ፣ የደፈረሱ ወንዞች ጠርተው፣ ሰማይ ብሩህ ሲሆን ወጣት ሴቶችና ወንዶች አምሮባቸው አደባባይ ይወጣሉ።

በሰቆጣና አካባቢው የሚገኙ ልጃገረዶች ፀጉራቸውን ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ሳዱላና ቀጫጭን ሹሩባ ተሠርተው ሲዘጋጁ፣ ሴቶቹን አጅበው የሚውሉት ወንዶች ደግሞ ፀጉራቸውን ቁንጮ ተላጭተውና በባህል ያጌጠ ልብስ  ለብሰው ጅራፋቸውን  እያጮሁ   ያከብሩታል። ሕፃናት  ደግሞ ጆሯቸው ላይ ትላልቅ ክብ ቀለበት ጆሮ ጌጥ፣ መሀል ፀጉራቸው ተላጭቶ ዳርዳሩ ያሳድጋሉ ይህም  ‹‹ጋሜና ቁንጮ›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በሰሜን ወሎ ላስታ ላሊበላና በዙሪያው ያሉ ሴቶች ደግሞ ለአሸንድዬ ፀጉራቸውን ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ሳዱላና በቀጫጭኑ ሹሩባ  አምረውና ተውበው ሲውሉ፣ የትግራይ ሴቶችና ልጃገረዶች ለአሸንዳ  በዓል የሚዋቡበት  የፀጉር  አሠራር  ደግሞ አልባሶ፣ ጋሜና ድርብ ነው፡፡ ጋሜና ቁንጮ፣ ጎበዝና ቆንጆ ፣ አንድግራና አፈሳሶ በሚባሉ የፀጉር ሥሪቶች አምረውና ተውበው  ሶለልን ለማክበር ብቅ የሚሉት ደግሞ የራያ ቆነጃጅት ናቸው፡፡ 

በበዓሉ ላይ የሚለብሷቸው አልባሳት እንደ አካባቢው ቢለያይም በአብዛኛው ሴቶች የሐበሻ ቀሚስ፣ የሻማ ጨርቅ ወይም ሽፎን የሚባለውን ሽንሽን ቀሚስ ለብሰው ይታያሉ።

ለመድመቂያነት በጆሯቸው ላይ ጉትቻ፣ ለእጃቸው አንባር፣ እግራቸው ላይ አልቦ፣ በአንገታቸው ላይ መስቀል፣ አሽንክታብ፣ ድሪና ሌሎች ጌጣ ጌጦችን ይጠቀማሉ። በዋዜማው ነሐሴ 15 ልጃገረዶች በቅቤና በኩል መዋብ ይጀምራሉ። የክረምቱ ዝናብ ያለመለመውን የአሸንዳ ተክል ቆርጦ ለወገብ እንዲመች ተደርጎ በማዘጋጀት እንደ አንቀልባ በወገባቸው ዙሪያ ያደርጉታል።

በክብረ በዓሉ ሴቶች ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ያለቤተሰብ ተፅዕኖ እየተጫወቱ የሚውሉበት፣ ከቤት ሥራ ነፃ የሚሆኑበት፣ እንደውም ቤተሰብ አልባሳትና ጌጣ ጌጦችን በመግዛት ልጆቹን አስውቦ ወደ በዓሉ የሚልኩበት ሳምንት በመሆኑ ‹‹የሴቶች የነፃነት ጊዜ›› በመባል ይታወቃል፡፡

የልጃገረዶቹ ዜማና ግጥም እምነትን፣ አመለካከትን፣ ፍቅርንና ተስፋን በውስጡ ይዞ በጭፈራና በእልልታ  ታጅቦ ይቀርባል። በየደረሱበት ጨፍረው በዘፈንና በግጥም አወድሰው ለሰጣቸው ሰው ሙገሳቸውን፣ ላልሰጣቸው ደግሞ በአሽሙር  ትዝብታቸውን ይገልጻሉ። እናቶች የበዓሉ አካል ሆነው ባህሉ ከጥንት ጀምሮ ይዞ የመጣውን የበዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ለትውልድ እንዲተላለፍ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። ሕፃናት ሴቶች የዕለቱ ተጨማሪ ድምቀት ሆነው ባህሉን ከታላላቆቻቸው በመማር ለቀጣይ አደራ ይቀበላሉ።

ሴቶች ተጠራርተው ለጭፈራ ሲወጡ  ከመካከላቸው ያገባች ጓደኛቸው በበዓሉ ላይ ያልተገኘች እንደሆነ ሰብሰብ ብለው ወደ ቤቷ በመሄድ

 ‹‹ዓለሜ ትተሽው ነይነይ፤

 ባል ጉዳይ ነው ወይ››

 ሲሏት ባለትዳሯ ሴት ደግሞ

 ‹‹ትቼውስ አልመጣም፤

 ባል ጉዳይ ነው በጣም››

 የሚል ምላሽ ትሰጣቸዋለች፡፡

በዚያን ጊዜ ባሏ ከፈቀደላት ወደ ቡድኑ ትቀላቀልና በአካባቢው ባሉ መንደሮች እየተዟዟሩ፤

 አሸንዳዬ

አሃ አሸንዳ ሆይ፣

 ሽርግፍ አትይም ወይ፣

 አሸንዳ ሙሴ፣

 ፍስስ በይ በቀሚሴ።

 አበሙሴ አንቺ አበሙሴ፣

 ሽርግፍ በይ በቀሚሴ።

 አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ፣

ጠብ እርግፍ እንደ ወለባ።

 ምድር ጭሬ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ፣

 እሰይ የእኔ እመቤት ድልድል ወይዘሮ።

 ከሰፌድ ላይ አተር ኮለሌ ኮለሌ፣

 የኔማ እሜቴ አንገተ ብርሌ።

እያሉ ማንጎራጎር ሲጀምሩ ቤቱ ተከፍቶላቸውና ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ የቤቱን ባለቤት ግጥም አውራጇ 

‹‹እሜቴ አሉ ደህና ወይ››

 ስትል ተቀባዮቹ በአንድነት ድምፅ

‹‹አሉ እንጂ ግቡ ይላሉ እንጂ›› ይላሉ በማለት በኅብረት ያዜማሉ።

እንዲህ እያሉ ሲጨፍሩ በራቸውን ዘግተው ከተቀመጡ  በግጥም የተዋዛ  ስድብን መከናነባቸው አይቀርም። 

 ‹‹መጫኛ ሲሰቀል ተጠቅልሎ ነው፣

 ልጅ የረገመው ሰው መዳኛም የለው።

 እናንተን አይደል ወይ የማወሳሳው፣

 ቀና ብለው እዩን የሰው ጡር አለው›› በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

 በአንፃሩ ደጃቸውን ከፍተው ያላቸውን አነሰ በዛ፣ ቀላ ጠቆረ ሳይሉ ለሚሰጡ ደግሞ፡-

 ‹‹ትሻል እሜትዬ ትሻል፣

ይሻል ጌትዬው ይሻል››

በማለት አወድሰው ይሄዳሉ።

በወገባቸው ዙሪያ ሳር በማድረግ ወዲያና ወዲህ ማዟዟር ዋናው የበዓሉ ምልክትና የጭፈራው አካል ነው፡፡ በአሸንድዬ ክብረ በዓል ወቅት የክረምቱ ዝናብ እየቀለለ ስለሚሄድና መስኩ በልምላሜ የተዋበ መሆኑ፣ የአሸንድዬው ጨዋታ፣ ከሆያሆየው ድግስ ጋር ተደምሮ ልዩ ጊዜ ያደርገዋል። ልጃገረዶች በየመንደሩ እየዞሩ ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ሁሉም ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ በዘፈንና በዜማ ውድድር ያደርጋሉ።

በዚህ ውድድር ላይ ጎረምሳው ዓይኑ ያረፈባትን ቆንጆ ጎንተል (ነካ) በማድረግ እንደወደዳት ምልክት ያሳያታል። ሴቷ ከፈቀደች ወደሱ ሄዳ አብራው ትሆናለች። ከዚያም ሽማግሌ እንዲልክ ይመካከሩና ለጋብቻ ይተጫጫሉ። ልጃገረዶች በዓሉ አልቆ ሊለያዩ ሲሉ የዕድሜ ባለፀጋ ሰው ቤት በመሄድ ምርቃት ይቀበላሉ።

‹‹ከርሞ እንገናኝ ላመት፣ እኛም ሳንሞት››

‹‹ያላገባም ያግባ፣ ያገባም ይውለድ ዘራችሁ የበዛ ይሁን›› በማለት የዕድሜ ባለፀጋዎቹ ለልጆች ዕድሜ ለምነው የቀጣዩን ዓመት እንዲናፍቁ አጓጉተው ይሸኛሉ።

በዚህ መልክ ይህ በዓል ለብዙ ዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ሲከበር ቆይቷል።

የአሸንዳ በዓልን በተለይ በትግራይ ክልል በአደባባይ ክብረ በዓል ደረጃ በማክበር ለማስተዋወቅና በቅርስነት ለማስመዝገብ ሙከራ እየተደረገ፣ በመቀለና በአዲስ አበባ  ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እየተሳተፉበት በድምቀት ይከበር እንደነበር ይታወሳል። በአማራ ክልልም እንዲሁ በየዓመቱ በድምቀት እየተከበረ  ያለ  በዓል ነው፡፡

ይሁንና  በ2013 እና በ2014 ዓ.ም. በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በዓሉ በድምቀት ሳይከበር ቀርቷል።

በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩና በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳትና ስቃይ የደረሰባቸው  ሴቶች ያለፈውን ሐዘንና እንግልት በመርሳት መጭውን ተስፋና ምኞታቸውን ይዘው የዘንድሮውን በዓል በድምቀት በተለያዩ አካባቢዎች አክብረዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር 600 የሚሆኑ የባህሉ ተጫዋቾች    በዓሉን በዞኑ ዋና ከተማ  በሆነችው ሰቆጣ  ላይ  ከነሐሴ 16 እስከ  18 ቀን 2015 ዓ.ም.  በድምቀት እየተከበረ መሆኑን፣ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምርያ ኃላፊ ዲያቆን መሳይ ፀጋው መግለጫ ሰጥተዋል።

በኮሮና ወረርሽኝና በጦርነት ለሁለት ዓመታት በድምቀት ሳይከበር የቆየው የአሸንዳ በዓል በ2015 ዓ.ም.  በትግራይ በታየው ሰላምና መረጋጋት በመቀለና በተለያዩ  የክልሉ ከተሞች በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር  ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም.  በሚሊኒየም  አዳራሽ በድምቀት እንደሚከበር ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...