Thursday, July 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከፋኖ ቀጥሎስ?

ከፋኖ ቀጥሎስ?

ቀን:

በዳዊት አስማማው

ሰሞነኛው የአማራ ክልል ቀውስ ክስተት አይደለም፣ የሒደት ውጤት ነው፡፡ መጨረሻስ ነው? አይመስለኝም፡፡ ‹‹የባሰ አታምጣ›› ይላል የአገሬ ሰው፡፡ ራስህ የባሰው እንዲመጣ እየሠራህ ፈጣሪን መማፀኑ ምን ያህል እንደሚያዋጣ እንጃ፡፡ የባሰው እንዳይመጣ ምን ይደረግ? ወደኋላ መለስ ብሎ ከመቃኘት ይጀምራል፡፡

እንደ መነሻ ግን የአማራ ጥያቄ ምንድነው? በየዘመኑ ይለያያል፡፡ ይለያያልና ይምታታል የተለያየ ነው፡፡ ከመለያየቱ መምታታቱ ነው የብዙ ችግር ምንጭ፡፡

ያለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ‹‹መሬት ለአራሹን›› ያህል ትልቅ ክስተት የለም፡፡ ታላቁን የኢትዮጵያ አብዮት ያህልም አብዮት በኢትዮጵያ ታሪክ የለም ማለትም ይቻላል፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ምሁራንና ወጣቶች የትግል ቋንቋ ‹‹መሬት ለአራሹ›› ነበር፡፡ በጥቂት መሳፍንትና መኳንንት ባለቤትነትን ሥራ ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ ጭሰኛ የሆነበትን የመሬት ሥሪት ለመቀየር የታገለው አማራ ከሁሉም ይበልጣል ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ የከረፋውን ዘውዳዊ ሥርዓት የገረሰሰው ትግል ውስጥ የአማራ ወጣት ሚና ከማንም ይልቃል፡፡

በትግሉ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው በአብዛኛው ከገዥው መደብ የሚወለዱት የባላባት ልጆች ነበሩ ማለትም ውሸት አይደለም፡፡ ፊውዳሊዝምን ታግለው የመነገሉት መደባቸው ያላሸነፋቸው የሕዝብ ተቆርቋሪነት የበለጠባቸው ወጣት ምሁራን ናቸው፡፡ ባላባታዊውን  ኢፍትሐዊ ሥርዓት ገርስሰው ዴሞክራሲና እኩልነትን ለማስፈን የተንደላቀቀ ኑሮ ያላጓጓቸው የባላባት ልጆች ትግል ዘለዓለም ሲንፀባረቅ ይኖራል፡፡ ይህን አንፀባራቂ ታሪክ ለምናውቅ ዛሬ ተነስቶ ለፊውዳሊዝምና ለዘውዳዊ አገዛዝ ጥብቅና ካልቆምኩ ብሎ መከራ የሚያየውን የገባር ልጅ ስንመለከት፣ ‹‹ወይ ዕድሜ አያሳየው ያለ›› ማለት ብቻ እንዴት ይበቃል? ጣጣው መቼ በዚህ አበቃና ይበቃል?

‹‹ፊውዳሊዝም በክፉ ተነሳ፣ ንጉሣዊው ሥርዓትና ነገሥታቱ ተወቀሱ›› የሚል የትግል አጀንዳ ይዞ ከአገር ከምድሩ ጋር የሚላጋ ትውልድ እንደ ምን አፈራን? ራሳችሁን ለኢትዮጵያዊ ጭቁን ሕዝብ ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ከተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊያን ጋር ድርጅት መሥርታችሁ፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ ስትታገሉ የኖራችሁ የኢሕፓና የመኢሶን ትውልድ ሰዎችስ ዝምታችሁ ስለምን ሰፋ?

ጠማማው ከዚህ ይጀምራል፡፡ ለተጨቆኑ ዜጐች ሁሉ ሲታገል የኖረው የአማራ ወጣት ጭቆናን እያሞካሸ ለጨቋኝ ሥርዓት ጥብቅና ለመቆም ሲዳዳ፣ ምክንያታዊነት ከምንጩ ነጥፎ ሃይ የሚል ጠፋ፡፡ ለመሬት ለአራሹ ትግል በተሰዋ የአማራ ልጅ አጥንት ላይ ‹‹ርስቴ›› የሚል መጢቃ ሲበቅል የሚያርም ጠፋ፡፡ ለእኩልነትና ለአገራዊ ልዕልና ሲታገል ደሙን ባፈስስ የአማራ ልጅ መቃብር ላይ፣ ‹‹ምርጥ ዘር ነን›› የሚል ዋልጌ ሲለፋደድ ‹‹ተው›› የሚል ጠፋ፡፡

ጥፋት በጥፋት ላይ እየጨመረ በቀላሉ መግባባት ሊደርስባቸው የሚችሉ ጉዳቶችን መጣያ እያደረገ ከራስ ጋር መጣላት ሙያ ሆነ፡፡ የፖለቲካ ማይም ሁሉ ኃይል መበተንን ሙያ አደረገ፡፡

የመጀመሪያው ኃይል ብተና እዚያው አማራ በተባለው ክልል ውስጥ ሕዝቡን ያለ ወገን በማስቀረት ነው የተጀመረው፡፡ የወሎ ኦሮሞ፣ ዋግ፣ አገው ምድር የቱነው እስቲ አሁን ከአማራ ጎን የሚቆመው? ለምን ብሎ የሚጠይቅስ አለ? ገፍተህ ገፍተህ ጠላት ልታደርገው የሄድክበትን ርቀት ታውቀዋለህ? በዚህ አማራ በሚባለው ክልል ውስጥ እየኖረ ‹‹የእገሌ ተወላጅ›› አመራር መሆን የለበትም እያልክ ገፍተህ ሌላው ክልል ውስጥ የሚኖረው አማራ ተገፋ ልትል ይዳዳሀል፡፡

የለውጡ ሰሞን ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ነበር፡፡ አማራ ክልልን አማራ ካልሆኑ አመራሮች ለማጥራት ይደነፋ የነበረውን ፉከራ ከትንሹም ከትልቁም እሰማ ነበር፡፡ የብአዴን ሰዎች ድርጅታቸውን የደም ቅልቅል ካለባቸው አባላት ማጥራትን የሞት ሽረት ትግል አድርገው þþ በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ ከአንድ ሁለቱ የዚያን ጊዜ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ለማውራት ያደረግኩት ሙከራ ከሶሻሊስትነት ተቆጠረብኝና ተውኩት፣ ከፊውዳልነት ይሻለኛል፡፡

ወደ መኖሪያዬ ከተመለስኩ በኋላ ‹‹ብሔርተነኝነትን እቃወማለሁ›› ሲል የነበረው ‹‹ምሁር›› ተብዬ ሁሉ፣ የመጨረሻው ብሔርተኛ ሲሆን ማየት የተለመደ ሆነብኝና የዘመኑን እብደት ተለማመድኩት፡፡ የመጨረሻ ውጤቱ የማይለምዱት እንደሚሆን ግን የዚያን ጊዜ አውቀው ነበር፡፡ ብሔርተኝነት ችግር አልነበረውም፣ የፖለቲካ ድድብና ውስጥ እስኪከትህ ሲያውርህ ግን ከችግር በላይ ነው፡፡

የዕድሜውን ሁለት ሦስተኛ በፖለቲካ ያሳለፈ ጎበዝ እንዴት ኃይል መበታተን የፖለቲካ መንገድ አድርጐ ይንበዛበዛል? የሠለጠነው የፖለቲካ ባህል ውስጥ እየኖረ ኋላቀር ዳፈና ውስጥ ከመዘፈቅ በላይ ምን ድድብና አለ?

አሁን ባለንበት ሁኔታ የአማራ ፖለቲካ አጋር ማነው? ሁለት ሦስተኛው መሬት የእኔ ነው እያልክ ሌትና ቀን የምትዛበትበት ቤንሻንጉል ነው? ደም የተቃባኸው ትግሬ ነው? ከግማሽ በላይ ኦሮሙማ መሬት የእኔ ነው የምትለው ኦሮሞ ነው?

ከኢትዮጵያዊት ማማ ተፈጥፍጠህ ጎጥ ውስጥ ከተወሸቅክ በኋላ የኢትዮጵያ ‹‹ዋና ባለቤት እኛ ነን›› ማለት እንዴት ጤንነት ሊሆን ይችላል? ያሳበደህን ነገር ነው መመርመር ያለብህ፡፡

ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የኤርትራ ኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ እያለ፣ ‹‹የኤርትራዊያንን ኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚጎዳ ትግበራ እየተፈፀመ ነው›› እያለ ደርግን ሲያማ አንድ ወዳጄ አልኩት ያለኝን አስታውሳለሁ፡፡ ‹‹አንተ አይደለህም ወይ አስተዳዳሪው?›› ነበር ያለው፡፡ ከደርግ የከዳ ሰሞን፣ ‹‹ባሪያ አሳዳሪነታችን ቢቀር እንዴት በባሪያ እንተዳደር?›› እያለ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ላይ ሲጎነፋ ነበር፡፡ ያኔ ያመነዠገውን ማግሳት አሁን በአደባባይ ተፈቶታል፡፡ የእሱን ቅርሻት እንደ ጠበል እየተራጨ የሚናውዘው ወጣት እንጂ የሱስ ዕዳው ገብስ ነበር፡፡ ልደቱ ከሚባለው ልጅ በስተቀር ይህንን ሲጠየፍ የሰማሁት የአማራ ተወላጅ ፖለቲከኛ ያለመኖሩ ነው የበለጠውን የሚያሳዝነኝ፡፡ ምን እየተሆነ ነው?

ምን ይደረግ?

የመጀመሪያውና መሠረታዊው ጉዳይ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መበየን ነው፡፡ ባለንበት ደረጃ ‹‹የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ምንድነው?›› ከሚለው በላይ፣ ‹‹ምን አይደለም›› የሚለውን መመለስ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ዘውዳዊ ሥርዓት ወይም ፊውዳሊዝም አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ንግሥና ወይም ባላባትነት አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ እኩልነት ፍቅርና አንድነት ነው፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በእኩልነትና በኅብረት በአንድነት መኖር፡፡ ከዚህ በተለየ የሚጠፈጠፈውን ያረጀ፣ የደደረውና የተሳሳተ አስተሳሰብ ማረምና ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ የተበላሸ አስተሳሰብ ምንጭ ‹‹የተሳሳተ ትርክት››፣ ‹‹ስዑት ሁከት›› ትርክት እየተባለ ሌላው ላይ ጣት እንደሚጠቆመው አይደለም፡፡ ራሱ የአማራ ልሂቅ ነው ዋናው ምንጭ፡፡ ራሱን የዘውድ ጠበቃና የፊውዳሊዝም ወኪል አድርጎ የግፉአንን ቁስል ሲደነቁል የሚውለው ደነዝ ነው ምንጩ፡፡ በአፄያዊና በፊውዳላዊ አገዛዝ ተጨቁነናል፣ ተገፍተናል የሚሉ ኅብረተሰቦችን ሕመም መረዳትና ይህንኑ መግለጽ ብቻ ነው መድኅኑ፡፡

የአፄዎች ጭቆናና በደል ከአማራ ሕዝብ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም፡፡ የአማራ ሕዝብ ነው የጨቆነኝ ብሎ ሲከስ የሰማሁትም የለም፡፡ ራሱ የአማራ ልሂቅ ነው ባልተጠራበት ‹‹አቤት›› እያለ ባልተወከለበት እየተሰየመ ወደ ራሱ የሚስበው፡፡

በተረፈ የአማራ ሕዝብ እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በባለሀብቶች ሲገፋ፣ በገባርነት ሲማቅቅ የኖረ ደሃ ሕዝብ ነው፡፡ የድህነቱና የጉስቁልናው መጠን ይበዛ እንደሆነ እንጂ አያንስም፡፡ ፊውዳሎቹና ዘውዳውዊያኑ አማርኛ ከመናገራቸው በቀር ከአማራው ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ጉዳይ የለም፡፡ ይህንን ማመንና በሌሎችም ዘንድ እንዲታመን ማድረግ ዋናውና ቀዳሚው ተግባር ነው፡፡ የአማራ ጭቁን ሕዝብ ውግንና ከተቀረው የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝብ ጋር ነው፡፡  

የአማራ ሕዝብ በ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዙሪያ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ጥያቄ የለውም፡፡ ይልቁንም የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች በተለይ በሕገ መንግሥቱ በይፋ የተደነገጉት የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች በተሟላ ሁኔታና በትክክል እንዲተገበሩ ነው ጥያቄው፡፡ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የመዘዋወር፣ የመሥራት፣ ደኅንነቱ በተጠበቀ አካባቢ የመኖር መብቱ ይከበርለት ዘንድ ነው ጥያቄው፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደ ባዕድ (ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው የውጭ አገር ዜጋ ሊኖረው የሚገባው መብት እንኳን እየተነፈገ) ውጣ እየተባለ መሰደድ፣ መዘረፍና መገደል ይቅር ነው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ፡፡

በተረፈ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ሌላውን ተጠቃሚ አማራን ተጎጂ ያደረገ የሕገ መንግሥት አንቀጽ ያለ ይመስል፣ የሚሰማው አደንቋሪ ጩኸት የአማራን ሕዝብ አይመለከትም፡፡ የአማራ ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ የሚያስከብረው ጥቅም ወይም ተለይቶ የሚጠይቀው ልዩ መብት የለውም፡፡ ጥያቄው እኩልነት፣ መተጋገዝ፣ መደጋገፍና አንድነት ነው፡፡

ይህን የመሰሉ ብዥታዎች ይካሄዳል የተባለው አገራዊ የምክክር መድረክ ተግባራዊ ሲሆን እንደሚጥሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የአማራ ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ሕገ መንግሥታዊ የመብትና የጥቅም ጥያቄ የለውም እየተባለ፣ ስለምን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የመዘዋወር፣ የመሥራት፣ የመኖር መብት በተለየ ይጠይቃል ከተባለ በተለይ ስለሚመለከተው ነው፡፡ የተደበቀ ወይም የሚደበቅ ጉዳይ የለውም፡፡ በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች የአማራ ሕዝብ ዛሬ ‹‹አማራ›› ከተባለው ክልል ውጪ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በስፋት ተሠራጭቶ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ስህተት አልነበረም፣ አሁንም ስህተት አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመኖርና የመሥራት መብት ነበረው፣ አሁንም አለው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡

ስህተቱ ሦስት አራት ትውልድ ከሚኖርበት አካባቢ እንደመጤ ተቆጥሮ ‹‹ውጣ›› መባሉ ነው፣ መገፋቱ መገደሉ ነው ስህተት፡፡ መንግሥት እንዲህ ያሉ ወንጀሎችን በአስቸኳይ ማስቆምና ሕግን ማስከበር አለበት፡፡ ‹‹በዚህ መንገድ አታልፍም››፣ ‹‹እዚህ ከተማ አትገባም›› ዓይነት አስፀያፊ ድርጊቶችን ከመሠረታቸው መግታት አለበት፡፡ ወንጀለኞችን እየተከላከልን ነው የሚሉ አካላት የሕዝብ እንቅስቃሴ ያልገደበ ፖሊሲ መጠቀም የእነሱ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት ዛሬ ጽንፈኛ ለሚላቸው ወገኖች ምክንያት እየሰጠ ያለው እሱ ራሱ መሆኑን ተገንዝቦ የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡

ዛሬ አማራ ክልል ውስጥ ለተፈጠረው ትርምስ ከላይ የተጠቀሱት ህፀፆች በቂ ምክንያት ናቸው እያልኩ አይደለም፡፡ ከመሠረታቸው መታረም አለባቸው ያልኳቸው መሠረታዊ መዛበቶች ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ናቸው፡፡ የአማራ ሕዝብ የዘውድና የባላባትነት ጥያቄ የለውም፡፡ ውግንናው እንደ እርሱ ሲጨቆን ከኖረው የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝብ ጋር ነው፡፡

ወደ ወቅታዊው ትርምስ ስንመለስ ከዚህ ስሜታዊ ቀውስ ጀርባ ያላቸሁ ወገኖች ሁሉ ቶሎ ወደ ቀልባችሁ ተመልሱ፡፡ ‹‹ቶሎ›› የምለው መመለሳችሁ ስለማይቀር ነው፡፡ የተያዘው ዕብደት ማንንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ፖለቲካም አይደለም ‹‹የአማራ ሕዝባዊ ትግል›› የሚባለው ወለፈንድ ራስ ላይ መቀለድ ነው፡፡ ታጥቀህና ሕዝብን ሰብዓዊ ጋሻ አድርገህ እየተኮስክ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ብሎ ቋንቋ የለም፡፡ የትጥቅ ትግል ነው፡፡ እንደ እሱም እንዳይባል ከተማ ተሸጉጦና ሰላማዊ ሕዝብ መሀል ተደብቆ የትጥቅ ትግል የለም፡፡ ለኢሕአፓም አልበጀ፡፡ አምባገነንነት ከመዋለድ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ሕዝብንና አገርን ማድቀቅ ብቻ ነው ትርፉ፡፡ ለዚያውም የሚታገስ ወገን ሲኖርህ ነው፡፡ ቁርጡን ልንገርህ አይታገስህም፡፡ መሠረታዊ አቅርቦቱን ዘግተህ፣ የሚሠራውና የሚሸምተው አሳጥተህ አንተን የሚሸከም ሕዝብ የለም፣ መሸከምም የለበትም፣ ስለምንስ ይሸከምሀል?

እዚህ አሜሪካ ተቀምጠው ትግሉን እየመራን ነው የሚሉ ወለፈንዲዎች ስለሥርዓት ለውጥና አራት ኪሎ የሚያውሩትን እየሰማህ አትለቅ፡፡ ከድፍን ኢትዮጵያ ጋር እያጣሉህ ነው፣ ሊያቆራርጡህ እየተጉ ነው፡፡ እነሱ የሚጎድልባቸው የለም፣ ምናልባትም ይሞላላቸዋል፣ ዶላር ይሰበስቡበታል፣ እያወሩ ይኖሩበታል፡፡ እንዲህ ያለው ሆዳምነት ነው የአማራን ሕዝብ ዘመድ እያሳጣው ያለው፡፡

በተጨባጭ የሚታየውንና ሁሉም የተረዳውን እውነት ደብቆ የትም አይኖርም፡፡ ተጨባጩ እውነት ይህ አሁን አማራ ክልልን እያተራመሰ ያለው ወጀብ ፖለቲካዊ አመራር የለውም፡፡ ከዘጠኝ ቦታ ዘጠኝ ነገር የሚናገሩ ደላሎች አመራር አይደሉም፡፡

ከመሩትም ወደ ዘጠኝ ገደል ነው እየመሩት ያሉት፡፡ ‹‹ጅጅጋ ርስታችን ነው፣ ወለጋ መሬታችን ነው›› እያሉ በአደባባይ የሚጎፈሉ ነፈዞች ሌላ ውጤት ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ክልሉን አልፎም አገሪቱን ቁልቁል እያምዘገዘገ መሆኑ ብቻ ነው እውነት፡፡ ስለሆነም በአስቸኳይ መቆም አለበት፣ ሁሉም ወደ ቀልቡ ይመለስ፡፡

በመጨረሻም…

ታላቁ የኢትዮጵያ አብዮት 50 ዓመት እየሞላው ነው፡፡ ታላቅ ምዕራፍ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም. ይህንን 50ኛ ዓመት በሚገባ ብንዘክረው ብዙ ነገር ልንማርበትና ልንታረምበት እንችላለን፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከአገራዊ ምክክሩ ጎን ለጎን አዲሱ ትውልድ የዚያን ዘመን ወጣቶች አንስተውት የነበረውን ጥያቄ አገራዊነት ስፋት እንዲማርበት ብንዘክረው መልካም ነው፡፡ ከመንደርና ከሠፈር የወጣ ዕሳቤ ምን ማለት እንደሆነ ልቆ ይስተማርበታል፡፡

በወታደራዊ ደርግ ተጠልፎ በተወሰነ ደረጃ ቢደናቀፍም ታላቁን የኢትዮጵያ አብዮት መካድ ኢትዮጵያን መካድ ነው፣ ግን አይቻልም፡፡ ያንን ወርቃማ ትውልድ መካድ አይቻልም፣ ልንማርበትና ልንታረምበት የሚገባ ብዙ እውነት በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አለ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...

የዘንድሮ ነገር!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ፡፡ ከእንጦጦ በኩል ቁልቁል እያስገመገመ...