የኢትዮጵያ ብሔራዊ አዲስ ባንክ ለመመሥረት የሚያስፈልገውን የተከፈለ ካፒታል መጠን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ከወሰነ በኋላ በምሥረታ ሒደት ላይ የነበሩ አብዛኞቹ ባንኮች ሲያከናውኑ የነበረውን አክሲዮን ሽያጭ አቋርጠዋል፡፡
የባንክ መመሥረቻ ካፒታል ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያድግ በተወሰነበት ወቅት በምሥረታ ሒደት ላይ የነበሩ ከ15 በላይ ባንኮች ነበሩ። ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዲስ መመሪያ የባንክ መመሥረቻ ካፒታልን ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር በማሳደግ በምሥረታ ሒደት ላይ የነበሩ ባንኮች አዲሱን የካፒታል መሥፈርት እንዲያሟሉ የጊዜ ገደብ አስቀምጦላቸው ነበር። ይህ የተሰጣቸው ቢሆንም የተጠየቀው አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ቀድሞ ከነበረው በአሥር እጥፍ በመጨመሩና የተቀመጠው የጊዜ ገደብም ይህንን ለማሟላት እንደማያስችላቸው በማመን የምሥረታ ሒደታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል።
በባንክ ምሥረታ ሒደት ላይ ከነበሩት ባንኮች ውስጥ እንደ ዳሞትራ፣ ሰላም፣ ዳያስፖራ፣ ሸገር፣ ጃኖ አፍሮና የመሳሰሉት ባንኮች የጠየቀውን ካፒታል ለማሟላት ባለመቻላቸው የአክሲዮን ሽያጭ መቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከእነዚህ በምሥረታ ሒደት ላይ ከነበሩት ባንኮች መካከል ‹‹ግዕዝ ባንክ›› በሚል ስያሜ ምሥረታ ላይ የነበረው ባንክ ግን ሰሞኑን ምሥረታውን ዕውን ለማድረግ አቋርጦት የነበረውን የአክሲዮን ሽያጭ ዳግም በማስጀመር የአክሲዮን ሽያጭ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል።
የግዕዝ ባንክ አደራጆች ባለፈው እሑድ የባንኩን አክሲዮኖች የገዙ ባለድርሻዎችን በወጋገን ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የስብሰባ አዳራሽ በመሰብሰብ፣ በአዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ካፒታሉን አሟልተው ባንኩን እንደሚመሠርቱ አስታውቀዋል፡፡
ግዕዝ ባንክ በጥቂት ወጣቶች አደራጅነት መጋቢት 2012 ዓ.ም. ወደ አክሲዮን ሽያጭ ቢገባም፣ ቀድሞ በተያዘው ዕቅድ መሠረት ባንኩን ለመሥራት አለመቻሉን የግዕዝ ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ጊዜያዊ ሰብሳቢ አቶ አብርሃ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል።
እንደ አደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገለጻ ባንኩን ለመመሥረት ኅዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀነ ገደብ በማስቀመጥ ለምሥረታ የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሟላት የሚያስችል አክሲዮኖችን ሽያጭ በሚያደርጉበት ወቅት የሰሜኑ ጦርነት መቀስቀሱ ለምሥረታው መዘግየት አንድ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከጦርነቱ ቀደም ብሎ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም የአክሲዮን ሽያጩን በማስተጓጎሉ ብሔራዊ ባንክ አዲስ መመርያ ከማውጣቱ በፊት የሚፈለገውን ካፒታል አሟልቶ ባንኩን ለመመሥረት አዳጋች ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡
የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም የተደረሰው የሰላም ስምምነት ግን ባንኩ የመመሥረት እንቅስቃሴ ደግሞ እንዲያንሠራራና አቅሙን በመጨመር ወደ አክሲዮን ሽያጭ እንዲገባ አስችሎታል፡፡
‹‹ግዕዝ ባንክ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ከመውጣቱ በፊት በወቅቱ የነበረውን 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ለማጠናቀቅ ከጫፍ ደርሶ ነበር፤›› ያሉት አቶ አብርሃ፣ ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው አስከፊ ጦርነት የአክሲዮን ሽያጩ ለማቆም መገደዳቸውን ገልጸዋል። የአክሲዮን ሽያጩ ዳግም ከተጀመረ በኋላ መነሳሳት በመፍጠሩ የካፒታሉን መጠን ከፍ ማድረግ መቻሉንም ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
በዚህም ጥረት በአሁኑ ወቅት የባንኩን አክሲዮኖች የገዙ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ13,800 በላይ ሲሆኑ የተፈረመ ካፒታሉን ደግሞ 1.8 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ባለአክሲዮኖች 850 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰብ መቻላቸውን የጠቀሱት አቶ አብረሃ፣ ከዚህ ሌላ አክሲዮኖችን በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲገዙ ለዚሁ ተብሎ በተከፈቱ የውጭ ምንዛሪ አካውንቶች 1.45 ሚሊዮን ዶላር እንደተሰበሰበም አመልክተዋል፡፡
ይህም በወቅቱ ከነበረው የባንክ መመሥረቻ ካፒታል አንፃር መቶ በመቶ ባንኩን ለመሥራት የሚያስችል ቢሆንም፣ በብሔራዊ ባንክ መመርያ ለውጥ ሳቢያ ምሥረታውን ለማካሄድ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
አሁንም ቢሆን ባንኩን ለመመሥረት ሰፊ ዕድል በመኖሩ የባንኩን አደረጃጀት በመለወጥና አዳዲስ አመራሮችን በማከል በአጭር ጊዜ ውስጥ የባንኩን ምሥረታ ዕውን ለማድረግ ያስችላሉ የተባሉ ውሳኔዎች መወሰናቸውን የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጸዋል።
በዚህም ውሳኔ መሠረት ከዚህ በፊት ትልልቅ ተቋሞችን በመምራት ለፍሬ ያበቁ፣ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሰዎች የኮሚቴው አባል እንዲሆኑ እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ይህ የአደራጆቹ ለውጡ ባንኩን ለማቋቋም ከመነሻው ጀምሮ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወጣት አደራጆች የጀመሩትን ሥራ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ታዋቂ ሰዎችና ባለሙያዎች ተረክበው እንዲያስቀጥሉ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ኃላፊነቱን የሚረከቡት ተተኪዎች ቀሪውን ካፒታል በማሟላት ባንኩን ዕውን እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት የገለጹት አቶ አብርሃ፣ ይህንን ራዕይ ለማሳካት አደራጆቹ ከመረጧቸውና አብረዋቸው እየሠሩ ካሉ ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዱ የቀድሞው የገቢዎች ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስቴር አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ መሆናቸውንም አቶ አብርሃ ለባለአክሲዮኖቹ አሳውቀዋል፡፡ የግዕዝ ባንክ ቀጣይ ሥራዎችን በኃላፊነት ዳር ያደርሳሉ ተብለው የተጠቀሱት አቶ ገብረዋህድ ን ሌሎች አመራሮችን ስለመሰየማቸው ለብሔራዊ ባንክ የሚያሳውቁ መሆኑን አደራጆቹ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ የሚካሄደውን የአክሲዮን ሽያጭና ባንኩን ምሥረታ ዕውን ለማድረግ ከፍተኛውን የኃላፊነት ድርሻ ይወስዳሉ የተባሉት አቶ ገብረዋህድ ባንኩን በአጭር ጊዜ ሊመሠረትና ይህንንም ለማድረግ ሊከተሉ ያሰቡትን ስትራቴጂ፣ እንዲሁም አጠቃላይ ግዕዝ ባንክን መመሥረት የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ያዘጋጁትን ሰፊ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የአገሪቱን ወቅታዊ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በመተንተን ሪፖርታቸውን የጀመሩት አቶ ገብረዋህድ ፣ የባንክ ዘርፉ ከሌሎች ቢዝነሶች ሁሉ የተሻለ ትርፍ የሚገኝበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ያመለከቱት አቶ ገብረዋህድ ፣ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የትርፍ ድርሻ የሚከፍሉ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ አገራዊ ጠቀሜታቸውንም በተመለከተ ምሳሌ ይሆናል ያሉት በዓመት እየከፈሉ ያሉት የግብር መጠን ከሌሎች ቢዝነሶች በተለየ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ ወቅታዊ መረጃዎችም ባንኮች በዓመት እየከፈሉ ያሉ ታክስ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አመልክተዋል፡፡
ስለዚህ ባንኮች ለአገራዊ ግብር ዕድገት፣ ለሥራ ፈጠራና ቁጠባን ለማበረታታት ተተኪ የማይገኝላቸው ተቋማት ናቸው ብለዋቸዋል፡፡ የአገሪቱ ባንኮች በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት እያሳዩ የመጡት ከአሥር ዓመታት ወዲህ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገብረዋህድ ፣ ሆኖም አሁንም ተደራሽነታቸው ገና በመሆኑ እንደ ግዕዝ ያሉ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው ቢቀላቀሉ እንደ ሌሎች ባንኮች አትራፊ ሆነው የሚዘልቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ባንኩን ለመመሥረትና ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችል አቅም ያለ መሆኑን የገለጹት አቶ ገብረዋሃድ የባንኩ ማዕከል ትግራይ እንደሚሆን በመጥቀስ ኅብረተሰቡ ይህንን ራዕይ ያሳካል የሚለውን እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
ግዕዝ ባንክ በዋናነት መሠረቱን በትግራይ ክልል አድርጎ ለመሥራት ያስፈለገበት የተለያዩ ምክንቶች ያሉት መሆኑንም በሰፊው አብራርተዋል፡፡ መሠረቱን ትግራይ ክልል ያደረገ ባንክ እንዲሆን ከተፈለገበት በርካታ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ፣ ክልሉ በቁጠባ ከፍተኛ ባህል ያለው መሆኑ አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም በ2017 የተደረገውን የዓለም ባንክ ጥናት የጠቀሱት አቶ ገብረዋህድ ፣ የኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ክልሎች የበለጠ የቁጠባ ባህል መሆኑን፣ በአኃዝ ጭምር ማስቀመጡን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ባንኩን ክልሉን መሠረት አድርጎ እንዲቋቋም የተፈለገበት ምክንያት በትግራይ ያለው የባንክ ሽፋን ከተሞችን ብቻ ያማከለ በመሆኑና ባንክ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች በርካታ በመሆናቸው የግዕዝ ባንክ መቋቋም ይህንን ክፍተት እንደሚሞላ በመታመኑ ነው፡፡
በቅርብ ጊዜ በትግራይ ክልል የተፈጠረው ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁንም የባንኩን ገበያ ሊያሳድግና ትርፋማ ሊያደርግ የሚችል ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ፣ ባንኩን ለማሳደግ ምቹ መሆኑ ክልሉን ማዕከል ማድረግ እንደተፈለገም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ትግራይን መልሶ ለመገንባት የተዘጋጀ ባለ ራይዕ ባንክ ነውም ብለው ጠቅሰዋል፡፡ የባንኩን አጠቃላይ ራዕይ በተመለከተ የተቀመጠውን ራይዕ አስመልክተው ከሰጡት ማብራሪያ መገንዘብ እንደተቻለው፣ በ2033 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የግል ባንኮች የመጀመርያው ማድረግ ነው፡፡ ከምሥራቅ አፍሪካ አምስት ትልልቅ ባንኮች አንዱ እንዲሆን ለማድረግ ጭምር እየተሠራ መሆኑን አቶ ገብረዋህድ አክለዋል፡፡
ይህንንም ራዕዩን ለማሳካት ያግዛሉ የተባሉ ስትራቴጂዎች እንደሚተገበሩና ዘግይተው ወደ ሥራ መግባታቸው ደግሞ የተሻለ አድቫንቴጅ የሚሰጣቸው መሆኑን ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በባንኩ ምሥረታና ሌሎች ክንውኖች ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአደራጅ ኮሚቴ አባላት ለሪፖርተር እንደገለጹት ደግሞ፣ ግዕዝ ባንክን ለመመሥረት መጀመርያም ጥናት ሲደረግ በዋናነት ትግራይ አካባቢን መነሻ ማድረግ ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት ነው፡፡ በትግራይ ክልል ያለው የባንክ ሽፋን ዝቅተኛ ሲሆን፣ የባንክ ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ታስቦ የተወሰነ ስለመሆኑ ከአደራጆቹ የተሰጠው ማብራሪያ ለመዳት ተችሏል፡፡
ባንኩ በዋናነት ትግራይ ክልል መሠረት ያድርግ እንጂ፣ በመላ ኢትዮጵያ የሚሠራ አክሲዮን፣ ሽያጩም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት የሚደረግ ስለመሆኑ ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በዕለቱ በተደረገው ስብሰባ ላይ ባለአክሲዮኖች የተለያዩ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን፣ በተለይ ባንኩ በቀድሞ መመርያ መሠረት በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሊመሠረት ይገባ ነበር ብለዋል፡፡
ባንኩ በቀደመው መመርያ መሠረት የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሟላት ጫፍ ደርሶ የነበረ በመሆኑ፣ ባንኩን በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዲቋቋም አሁንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላይ የሚያደርጉትን ግፊት እንዲቀጥሉም ተሰብሳቢው አሳስቧል፡፡
ይህንን ሐሳብ አደራጆቹ እንደሚጋሩት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ባንክ መመሥረቻ ካፒታሉ 500 ሚሊዮን ብር በነበረ ጊዜ አክሲዮን ሽያጩ ሲካሄድ ባለአክሲዮኖች የመመሥረቻ ካፒታሉ 500 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተረድተው የገዙ መሆናቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ስለዚህ እነዚህ ባለአክሲዮኖች የባንክ መመሥረቻ ካፒታል ወደ አምስት ቢሊዮን ብር አድጓል ሲባሉ በቀጥታ የእነዚህን ባለአክሲዮኖች መብት የሚነካ ስለሆነ፣ ጥያቄው የሕጋዊነትንም ጉዳይ የሚያስነሳ ስለመሆኑ ያምናሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ ግዕዝ ባንክን ጨምሮ ሌሎች በመደራጀት ላይ የነበሩ ባንኮች አዲሱ መመርያ ሊመለከታቸው የማይገባ በመሆኑ፣ ጉዳያቸውን ዳግም እንዲያጤንላቸው የሚሹ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ቀደም ቢሆን ይህንኑ ሐሳብ በመያዝ የግዕዝ ባንክ አደራጆች ከዚህ ቀደም በምሥረታ ላይ የነበሩ ባንኮችን በማስተባበር ጭምር ቢያንስ በምሥረታ ሒደት ላይ የነበሩ ባንኮች በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባንክ እንዲያቋቁሙ ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ በጋራ በተደጋጋሚ ያቀረቡት አቤቱታ ከብሔራዊ ባንክ ተቀባይነት ሊያገኝ እንዳልቻለ የግዕዝ ባንክ አደራጆች ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ በቀድሞው መመርያ ይጠየቅ የነበረውን ካፒታል ለማሟላት ያልተቻለበት ዋነኛ ምክንያት አስገዳጅ ሁኔታ (ፎርስ ሜጀር) በመፈጠሩ፣ በተለይ በትግራይ ክልል አክሲዮን ለመሸጥ የሚያስችል ሁኔታ ስላልነበረ ይህ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ በቀድሞ መመርያ መስተናገድ ይገባው ነበር በማለት ይሞግታሉ፡፡
አሁንም የግዕዝ ባንክ አደራጆች ከአክሲዮን ሽያጩ ጎን ለጎን ብሔራዊ ባንክ በቀድሞው የባንክ መመሥረቻ ካፒታል መጠን ባንኩን እንዲመሠረት እንዲፈቀድላቸው ጥያቄያቸውን የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ደግሞ አሁን ካሉ ባንኮች ውስጥ አንዳንዶቹ ግዕዝ ባንክ ካሰባሰበው የተከፈለ ካፒታል ያላቸው ባንኮች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አንስተው፣ በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባንክ ለመመሥረት ዕድል የነበራቸውን ባንኮች የግድ አምስት ቢሊዮን ብር ካልሞላችሁ ማለት ተገቢ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ መመሥረቻ ካፒታል መጠን ወደ 5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ሲወሰን፣ በምሥረታ ሒደት ላይ ያሉ ባንኮች 500 ሚሊዮን ብሩን ካፒታል እንዲያሟሉ እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ ጊዜ ሰጥቶ ነበር፡፡ በወቅቱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ በምሥረታ ሒደት ላይ ያሉ ባንኮች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ካፒታላቸውን ማማሟላት ካልቻሉ ግን ከጊዜ ገደቡ በኋላ ባንክ ማቋቋም የሚችሉት በአዲሱ መመርያ መሠረት እንደሚሆን ተናግረው ነበር።
በየትኛውም መንገድ ግዕዝ ባንክ ቀሪውን ካፒታል በአጭር ጊዜ አሟልቶ ወደ ገበያ የሚገባ መሆኑን የሚገልጹት አደራጆቹ፣ አዲስ ባወጣው የአክሲዮን ሽያጭ አፈጻጸም መሠረት፣ አንድ ባለአክሲዮን ዝቅተኛ መግዛት የሚችለው 100 ሺሕ ብር ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ 250 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ገልጿል፡፡ የባንኩ ለሽያጭ የቀረበው የአክሲዮን መጠን አምስት ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አምስት ሚሊዮን አክሲዮኖችን ነው፡፡