- ክቡር ሚኒስትር ጊዜ ሰጥተው ሊያነጋግሩኝ ስለፈቀዱ እጅግ አመሠግናለሁ።
- አንተም ለህዳሴ ግድቡ ስኬት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ትልቅ ምሥጋና አለኝ።
- ክቡር ሚኒስትር የህዳሴ ግድቡ ለእኔ የኃይል ማመንጫ ወይም የውኃ ልማት ጉዳይ ብቻ ባለመሆኑ በትልቅ ትኩረት የምከታተለውና የማጠናው ጉዳይ ነው።
- ልክ ነው። ይህ ግድብ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚከታተሉት ነው።
- ነገሩ ከዚያም በላይ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ከዚያም በላይ ስትል ምን ማለትህ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር የህዳሴ ግድቡ የልማት ጉዳይ ብቻ አይደለም።
- እ…?
- በዕቅዱ መሠረት ከተጠናቀቀ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ሊያሸጋግር የሚችል ዕምቅ ፖለቲካዊ ጉልበት የያዘ ኃይል ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ነው።
- እውነት ነው።
- አዎ። ለዚህ ነው ወደ እርሶ ለመደወል የተገደድኩት ክቡር ሚኒስትር።
- እስኪ ግልጽ አድርግልኝ?
- ክቡር ሚኒስትር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማያቸው እንቅስቃሴዎች አልገቡኝም። ሥጋት ፈጥረውብኛል።
- እንዴት? የምን ሥጋት ነው የተፈጠረብህ?
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት በቅርቡ ከግብፅ ጋር የተፈራረመው ስምምነት ምን እንደሆነ የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪዎች ጭምር የሚያውቁት ነገር የለም። ለምን በሚስጥር መያዙ ሥጋት ፈጥሮብኛል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ…
- በተጨማሪ ምን?
- ሰሞኑን የዩኤኢ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የተገኙበትን ዋና ዓላማ አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች ሥጋቴን የበለጠ አጠናክረውታል።
- ምንድነው የሰማኸው የተለየ መረጃ?
- ፕሬዚዳንቱ ከአሜሪካ መንግሥት ተልዕኮ ወስደው ጉብኝት እንዳደረጉና ዋና ተልዕኳቸውም በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት እንደሆነ የሚጠቁሙ መረጃዎች ናቸው።
- እንዳልከው ልዩነቶችን ለመፍታት ከሆነ ምን ችግር አለው?
- ክቡር ሚኒስትር አሜሪካኖቹ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚያራምዱት አቋም ግልጽ ነው። ግብፅን የሚጎዳ የውኃ ልማት በኢትዮጵያ ውስጥ ማየት አይፈልጉም።
- ግን ሊያስቆሙን የሚችሉበት ዕድል የለም።
- ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን የኢኮኖሚ ቀውስ በደንብ ያውቃሉ። ይህ ችግር አዲስ የውጭ ብድር ካልተገኘ እንደማይፈታም ተገንዝበዋል።
- ቢሆንም እኛ በአሜሪካ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ብቻ አንጠለጠልም። እንደ ቻይና ያሉ ሌሎች የልማት አጋሮች አሉን።
- ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያ አሁን ያለባትን ከፍተኛ የውጭ ዕዳን ማሸጋሸግ ወይም ማቅለል ካልቻለች አዲስ የውጭ ብድር ከቻይናም ሆነ ከሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ማግኘት እንደምትችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለዚህም ነው….
- ለዚህም ምን?
- መንግሥት አዲስ ብድር ለማግኘት የጠየቀውን የውጭ የዕዳ ሽግሽግና ማቃለያ ከህዳሴ ግድቡ ጋር ሳያቆራኙት አይቀርም።
- እንዴት?
- የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ ግብፅን በሚጠቅም መንገድ ካልተፈታ አዲስ ብድር ማግኘት አንችልም። በሩን እየቆለፉብን ነው።
- ቢሆንም መንግሥት ህዳሴ ግድቡን በጭራሽ አሳልፎ ሊሰጥ አይችልም። በእርግጥ አንዳንድ ጥያቄዎቻቸውን በሥልታዊ መንገድ ለማለፍ የተጀመሩ ጥረቶች አሉ።
- ምንድናቸው የተጀመሩት ጥረቶች ክቡር ሚኒስትር?
- ዝርዝር ጉዳዩን ለመናገር እቸገራለሁ። ነገር ግን ውኃ ሙሌትን በተመለከተ የተወሰኑ ማሻሻያ የሚመስሉ ነገሮችን ለማድረግና ለትብብር ያለንን የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ፈቃደኝነት ለማሳየት እንፈልጋለን።
- ክቡር ሚኒስትር ይህንን ነበር የሠጋሁት።
- የሚያሠጋ ነገር የለውም።
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ምክንያቱም ሊኖሩ የሚችሉት ማሻሻያዎች ከውኃ ሙሌት ጋር ብቻ የሚገናኙ ናቸው። በአጠቃላይ ለይምሰል የሚፈጸሙ ናቸው።
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ምን መሰለህ። የውኃ ሙሌቱ ከሞላ ጎደል ሊጠናቀቅ ነው። የዘንድሮ ሙሌት ከአዲሱ ዓመት በፊት ይጠናቀቃል።
- እና ቢሆንስ?
- የዘንድሮ ሙሌት ተጠናቀቀ ማለት በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ትርጉም ያጣል። ምክንያቱም የሚቀረው የውኃ ሙሌት ኃይል እያመነጨ የሚያልፍ እንጂ በግድቡ ውስጥ የሚጠራቀም አይደለም።
- ስለዚህ?
- ቀሪው የውኃ ሙሌት በተራዘመ ጊዜ ቢከናወን በእኛ ላይ ጉዳት አያመጣም። ይህንን በማድረጋችን ግን ካሳ እንጠይቅበታለን።
- ክቡር ሚኒስትር ይህ ጉዳይ ከግድቡ የውኃ ሙሌት አልፎ እንደማይሄድ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
- ከውኃ ሙሌት ውጪ ሊሄድ አይችልም። ወዴት ሊሄድ ይችላል።
- ክቡር ሚኒስትር የውኃ ሙሌት ግብፅን አያስጨንቅም። እነሱ ከህዳሴ ግድቡ ውጪ ሌላ ልማት በዓባይ ላይ እንዳይኖር ማሰር ነው ፍላጎታቸው።
- እሱ የውኃ ክፍፍል ጉዳይን ስለሚቀሰቅስባቸው አይፈልጉትም። ከውኃ ሙሌት ውጪ ከጠየቁ እኛም የውኃ ክፍፍል ጥያቄን አንስተን እንቆልፈዋለን።
- ክቡር ሚኒስትር እሱ ጥሩ መንገድ ነው። ነገር ግን በአሜሪካኖቹ ጫና እንዳንበለጥ ሠግቻለሁ።
- አትሥጋ። አሳልፈን የምንሰጠው ነገር አይኖርም።
- Advertisment -
- Advertisment -