Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች ታጣቂዎች ጋር ድርድር እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

መንግሥት ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች ታጣቂዎች ጋር ድርድር እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

መንግሥት በአማራ ክልል የሚካሄደውን ግጭት አስቁሞ ድርድር እንዲጀመርና ከኦነግ ሸኔ ታጣቂ ጋር ጀምሮ ያቋረጠውን ድርድር እንዲቀጥል ተፎካካሪ ፓርቲዎች  ጥሪ አቀረቡ፡፡

የአፋር ነፃነት ፓርቲ፣ ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ሌሎችም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህን ያሉት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው።

ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት ወቅታዊ መግለጫ፣ ‹‹የኃይል ዕርምጃም ሆነ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም፡፡ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ኃይሎች ውይይት አስፈላጊነት አሌ የሚባል አይደለም፤›› ብለዋል።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው የአማራ ክልል መንግሥትና የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ግጭት እንዲቆምና ድርድር እንዲጀመር፣ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ኃይልና በመንግሥት መካከል ተጀምሮ የተቋረጠው ድርድር በግልጽና አካታች ሁኔታ እንዲቀጥል፣ የትግራይ ክልል ጉዳይ በስምምነቱ መሠረት እንዲፈጸምና መፍትሔ እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡

በመንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተጀመረው ውይይት ግልጽና አካታች ባይሆንም ተጀምሮ መቋረጡ በሕዝብ ዘንድ አጭሮ የነበረውን ተስፋ ያጨለመ መሆኑ፣ ሕዝብ በውይይትና በድርድር ላይ ያለውን እምነት አመልካች ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ‹‹በመሆኑም እየተወሰዱ ያሉ የኃይል ዕርምጃዎችንና የመሣሪያ ግጭቶችን አጥብቀን እናወግዛለን፤›› ሲሉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከዚህ በፊት በነበሩ ግጭቶችና ችግሮች፣ እንዲሁም ከእነዚህ ግጭቶች ጋር በተያያዘ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት በኃይል ዕርምጃ መፍትሔ ለማምጣት›› እንደሞከረ የጠቀሰው የፓርቲዎቹ መግለጫው ‹‹ፖለቲካዊ አለመረጋጋቱንና ውጥረቱን፣ ኢኮኖሚያዊ ጥፋትና ውድመቱን፣ ዕልቂቱንና ማኅበራዊ ቀውሱን ከማስፋትና  ከማባባስ  አልፎ ዘላቂ መፍትሔ አላመጣም፤›› ብሏል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በትግራይ ክልል የነበረው ሁኔታ በተመለከተ በመግለጫው የጠቀሱት፣ ‹‹የስምምነቱ ተግባራዊነት በመዘግየቱ ወይም በስምምነቱ መሠረት ባለመፈጸሙ ችግሩ እንዳያገረሽ ሥጋት ቢኖርም ጥፋቱ፣ ዕልቂቱና ቀውሱ የቆመው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተከተለው የኃይል ዕርምጃ ሳይሆን በውይይትና በድርድር ስምምነቱ መሠረት መሆኑን በተጨባጭ ዓይተናል፤›› ሲሉ ነው፡፡

በመሆኑም መንግሥት በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ግጭቶችን በኃይል ዕርምጃ ለመፍታት ያደረገው ሙከራ ዘላቂ መፍትሔ እንዳላመጣ በመጥቀስ ከታጣቂዎች ጋር አካታችና ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲደረግ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡

በአብዛኛው ቦታዎች የስልክ ግንኙነትና የትራንስፖርት አገልግሎት የተስተጓጎሉበት፣ የወጣቱ ሥራ አጥነት ተንሰራፍቶ ከምርታማነት ይልቅ በግጭት የተሰማራበት የሚባልበት፣ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለፈተና መደረጉን የጠቀሰው መግጫው፣ ‹‹በመሆኑም ሕዝብ መንግሥትን ‹በቃልህ ተገኝ› እያለ ነው፤›› ብሏል፡፡

‹‹ከዚህ ጋር ተያይዞ ኮከሳችን ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው የአገራችን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ግምገማ፣ አገራችንና ሕዝባችን በእጅጉ አሳሳቢና አፋጣኝ የዘላቂ መፍትሔ ዕርምጃ የሚጠይቁበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን በመረዳት አቋም ወስዷል፣ የመፍትሔ ምክረ ሐሳብ አስቀምጧል፤›› ሲሉ በመግለጫቸው አስረድተዋል፡፡

በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች በሚያስብል ደረጃ ግጭቶችና የሕዝብ ጥያቄዎች በሕዝቦች የዕርካታ ዕጦትና ተስፋ መቁረጥ ስሜት ታጅበው በመንግሥትና ሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ከጥያቄ አልፎ መተማመን እንዲሸረሸር ማድረጉን፣ አልፎ ተርፎም በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው መተባበርና መተማመን ጥያቄ ውስጥ እንደወቀደ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

‹‹በመሆኑም አገራችን ከዚህም ለበለጠ የህልውና አደጋ፣ ሕዝባችንም ከዚህ ለከፋ ሥቃይና እንግልት፣ በአጠቃላይ ቀጣይ የአገራችን አንድነትና የሕዝባችን ግንኙነትና አብሮነት ለከፋ ፈተና እንዳይዳረግ አስቸኳይና አፋጣኝ ዘላቂ የመፍትሔ ዕርምጃ መውሰድና ያለንበትን ሁኔታ መቀልበስ አጠያያቂ አይደለም፤›› ሲሉም ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡

‹‹በመሆኑም ገዥው ፓርቲ ለዚህ ቀና አገር አድን ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት የአገራችን የፖለቲካ አስተሳሰብና ልምድ እንዲሻሻል፣ ካለፈው የመማር ልምድ መሠረት እንዲጣል በማድረግ የፖለቲካ ታሪካችን ላይ በጎ አሻራውን እንዲያሳርፍ፣ የታጠቁ ኃይሎች በሙሉ ለሰላማዊ ዘላቂ መፍትሔ የምናደርገውን ጥሪ በአዎንታዊነት እንዲቀበሉ፣ ትግላቸውም ከሥርዓት ለውጥ አልፎ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ጥቁር አሻራ እንዳያሳርፍ አስፈላጊውን ጥንቃቄና የአብሮነት ማረጋገጫ ዕርምጃ እንዲተገብሩ፤›› ሲሉ ፓርቲዎቹ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...