Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የቁም እንስሳት ኤክስፖርት በመጠንና በገቢ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2015 በጀት ዓመት ወደ ውጭ የተላከ የቁም እንስሳት መጠንና ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ በመጠንም ሆነ ገቢ ቅናሽ ማሳየቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የወጪ ንግድ ዴስክ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ የተላከው የቁም እንስሳት መጠን ከ2014 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በመጠን ከ46 ሺሕ በላይ፣ በገቢ ደግሞ ከ11 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ የተላኩት የቁም እንስሳት መጠን 89,338 እንደሆነ፣ ይህም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን በ46,378 እንደሚያንስ የሚኒስቴሩ የእንስሳትና እንስሳት ተዋፅኦ ወጪ ንግድ ግብይት ዴስክ ኃላፊ አቶ አበበ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩት 89,338 የቁም እንስሳት የተገኘው ገቢ 16.75 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ በ2014 በጀት ዓመት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ11.55 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ እንዳሳየ አስረድተዋል፡፡

የቁም እንስሳቱ የተላኩት ወደ ኦማን፣ ጂቡቲ፣ የመን፣ ሶማሊያ፣ ኩዌትና ሊቢያ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ወደ ውጭ የተላኩት እንስሳት በቁጥር ሲተነተኑ የዳልጋ ከብቶች 18,142፣ በግና ፍየሎች 67,348 እንዲሁም 3,848 ግመሎች እንደሆነ አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ለምን እንደቀነሰ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አበበ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ለቅናሹ በምክንያትነት የተጠቀሱት የሕገወጥ ንግድና ኮትሮባንድ መበራከት፣ የቁም እንስሳት የግብይት አዋጅ በክልሎች ተግባራዊ ያለማድረግ፣ የላኪዎች የፋይናንስ አቅም ውስን መሆንና የመሳሰሉት በዘርፉ የተስተዋሉ ተግዳሮቶች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ተከስቶ በነበረው ድርቅ በርካታ እንስሳት መሞታቸው፣ የአገር ውስጥ ገበያንና የኤክስፖርት ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ እንደሚችል ሚኒስቴሩ ሥጋት እንዳለው ሲገልጽ ነበር፡፡

በድርቁ እንስሳት በመሞታቸው ሳቢያ በወጪ ንግዱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዴት እንደሆነ እንዲያብራሩ የተጠየቁት አቶ አበበ፣ ‹‹ከድርቁ ጋር በተያያዘ ዳታ አላገኘንም፤›› ብለዋል፡፡ በድርቁ እንስሳት መሞታቸው ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ምን ያህል እንደቀነሰ በትክክል ለማወቅ ገና ጥናቱ እንዳልተጠናቀቀ፣ ምን ያህል እንስሳት በድርቁ ምክንያት እንደሞቱ የግብርና ሚኒስቴር እያስጠና መሆኑን፣ ትክክለኛ መረጃ ሲገኝ በድርቁ ሳቢያ እንስሳት መሞታቸው ያሳጣውን የገቢ መጠን እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በተገኘው መረጃ መሠረት 66 ሚሊዮን የዳልጋ ከብቶች፣ 45 ሚሊዮን ፍየሎች፣ 38 ሚሊዮን በጎችና 6.9 ግመሎች እንዳሏት አቶ አበበ አስረድተዋል፡፡

የሕገወጥ ንግድ መበራከት፣ የእንስሳት መኖ መወደድ፣ የትራንስፖርት ችግር ለገቢ መቀነስ መንስዔ መሆናቸውን የቀድሞ እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበር ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሞገስ ኃይሌ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አንዳንዶቹ ላኪዎች ከዘርፉ እያቋረጡ የሚወጡበት ሁኔታ እንዳለ፣ ደላሎች 10 ሺሕ መጫን ሲገባቸው ከ20 እስከ 30 ሺሕ ብር እንደሚያስከፍሉ፣ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ እንዲቀንስ ምክንያት መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ምን ያህል ላኪዎች ከዘርፉ እንደወጡ ለመግለጽ ግን ላኪዎች ገባና ወጣ ስለሚሉ ቁጥሩን በትክክል ለመናገር እንደሚቸገሩ አቶ ሞገስ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች