ለ30 ዓመታት ሳይሻሻል በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ፣ ከውጭ አካላት ተፅዕኖ ተላቆ በአገር ውስጥ አቅም በጠንካራ መዋቅር ተደግፎ እንዲሻሻል ጥያቄ ቀረበ፡፡
በ1985 ዓ.ም. ፀድቆ በሥራ ላይ ያለው የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ለ30 ዓመታት ያህል ሳይሻሻል ቆይቷል፡፡ መንግሥት ፖሊሲውን ለማሻሻል ሥራ መጀመሩን ከአራት ዓመታት በፊት አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ተጨባጭ እንቅስቃሴ አለመታየቱ ይነገራል፡፡
ፖሊሲውን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ‹‹ኢትዮጵያ ከሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ቱሩፋቶች ለመጠቀም ያላት ዝግጁነት›› በሚል መሪ ቃል የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡
በሥራ ላይ ያለው የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ከደረሰችበት የሕዝብ ቁጥር ብዛት ጋር የሚጣጣምና ለሚፈለገው ልማት መልስ መስጠት የማይቻል በመሆኑ፣ ወቅቱን ያገናዘበ የተጠናቀረ መረጃ እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ባለፉት ዓመታት በአመዛኙ በውጭ የልማትና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ፋይናንስና ሐሳብ ይደገፍ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲሻሻል በሚጠበቀው የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ መንግሥት ጉዳዩን በበላይነት ይዞት፣ ከሥነ ሕዝብ ትሩፋቶች ሊገኙ የሚችሉትን ጥቅሞች ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን ተጠይቋል፡፡
መንግሥት የሥነ ሕዝብ ፖሊሲውን አሻሽሎ ወደ ሥራ ለማስገባት የዳሰሳ ሥራ እያከናወነ መሆኑን፣ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
ዴቪድና ሉሱል ፓካርድ ፋውንዴሽን የተሰኘ ድርጅት የኢትዮጵያ አማካሪ የሆኑት ወ/ሮ የምሥራች በላይነህ፣ አገር ከሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ትሩፋት ተጠቃሚ እንድትሆን ሰፋ ያሉ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ተጨማሪ የሀብት ምንጭ በአገር ውስጥ በማሰባሰብና ከውጭ አካላት ተፅዕኖ የፀዳ በማድረግ፣ ጠንከራ የቤተሰብ ዕቅድና አገልግሎት ፕሮግራምን ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማት ለሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ያስረዱት ወ/ሮ የምሥራች ጥናት፣ አድራጊ ተቋማትም ወቅታዊና አቅጣጫ ጠቋሚ መረጃን በየጊዜው ማቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ባለሙያው አቶ ዘሪሁን አድነው በበኩላቸው፣ የወጣቶች አገር የሆነችው ኢትዮጵያ ያላትን የሰው ኃይል በመረጃ በማደራጀት፣ የሕዝቡን ትሩፋት መለየት ላይ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡ በሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ውስጥ የመንግሥት የልማት ዕቅዶች ግልጽ መነሻ ስለመሆናቸው የተናገሩት አቶ ዘሪሁን፣ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ በአንድ አገር ሕዝብ ላይ መሠረታዊ የሚባሉ የዕድገት ጉዳዮችን ለመለየት የሚጠቅም የመረጃ ቋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ጊዜ ያለፈበት በመሆኑ፣ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታና በሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸውን ጉዳዮች ያካትታል ተብሎ አይታመንም ብለዋል፡፡
አንድ ፖሊሲ በየአምስት ዓመት መሻሻል አለበት ተብሎ ቢታመንም በኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ፣ ዓለም አቀፍ ሁኔታው በፍጥነት እየተቀያየረ፣ በሥነ ሕዝብ ላይ ያሉ አመለካከቶች ከትምህርት፣ ከጤናና ከአጠቃላይ ከልማት አኳያ የመቃኛ መንገዶቹ እየተቀያየሩ ቢሄዱም አሁን እየተተገበረ ያለው ፖሊሲ እነዚህን ሁሉ የማይዳስስና ጊዜው ያለፈበት ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ልማትን ከሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ውጪ ማሰብ ከባድ ስለመሆኑ ያስረዱት አቶ ዘሪሁን፣ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ሲታሰብ አማራጭ የለሌለውና ይደር የማይባልለት ጉዳይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ከውጭ ተፅዕኖ በፀዳ መንገድ የሚዘጋጅ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል፡፡ የውጭ አካላት በሚያደርጉት ድጋፍ በፖሊሲው ላይ የራሳቸውን ፍላጎት በማሳደርና በአንድ አገር ሕዝብ ቁጥር ላይ ተፅዕኖ ማድረግ የሚፈልጉ በመኖራቸው ጥንቃቄ እንደሚያሻ ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ያቀደውን ልማት ለማስኬድ በሚሻሻለው የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ሰነድ ዝግጅት የውጭ ኃይሎች በሚፈልጉት ልክ እንዲቀለብሱት ዕድል መሰጠት የለበትም ያሉት አቶ ዘሪሁን፣ የአገር ውስጥ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ከወዲሁ ቅንጅት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ከባህል፣ ከእምነትና ከበርካታ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ የውጭ ኃይሎች በተለያዩ መንገድ ጣልቃ በመግባት እንዳያበላሹት ጠንካራ መዋቅርና ተቋማዊ ድጋፍ አስፈላጊነትን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
የሥነ ሕዝብ ፖሊሲና የአንድ አገር ልማት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆናቸውን የተናገሩት የሥነ ሕዝብ ባለሙያው እሸቱ ጉርሙ (ፕሮፌሰር)፣ ለአንድ አገር ልማት የሥነ ሕዝብ ትሩፋት አበርክቶ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ላይ ጠንካራ የፖለቲካ ዝግጁነት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡